የዳኞች ምልመላ ከፍርድ አሰጣጥ ጥራትና ከመዝገብ ክምችት አንጻር

0
522

እንዲህም ያሉ የሕግ ባለሙያዎች?!
ሰዓቱ የምሳ፣ ቦታው ደግሞ ምዕራብ ወለጋ ነቀምት አካባቢ ነው። መንገድ ዳር ካለ አንድ ሥጋ ቤት በረንዳ ላይ አረፍ ብለው ምሳቸውን የሚመገቡ ሰዎች አሉ። ከተማዋ ደግሞ የመንገድ ጥበት ካለባቸውና በጋውን በአቧራ፥ ክረምቱን ከጭቃ እምብዛም ከማይርቁት ኢትዮጵያዊያን ከተሞች የምትመደብ ነች።

ታዲያ ምሳቸውን እየበሉ የነበሩት ግለሰቦች ድንገት በአጠገባቸው ባለፈው አይሱዙ የተለየ በደል እንደደረሰባቸው ሆነው ያዙኝ ልቀቁኝ ዓይነት ግብግብ ውስጥ ከመግባት ተሻግረው ወደ ʻሕግ እርምጃʼ መግባታቸው አስገራሚ ነው።

ይኸውም ምሳ ሲመገቡ የነበሩት ግለሰቦች በሥራቸው ዳኞች መሆናቸውን ለአሽርካሪው እንደመበቀያ በመጠቀም ተሽርካሪው አቧራ አቡኖብናል በሚል ሹፌሩን በሕግ እንዲቀጣ አድርገውታል። የተቀጣበት ደግሞ ʻችሎት በመድፈርʼ የሚል መሆኑንም የዛሬ ዓመት ለጋዜጠኞች ስለ ችሎትና ተያያዥ የሕግ ጉዳዮች አዘጋገብ በተሰጠ አጭር ሥልጠና ላይ አንድ ታዋቂ የሕግ ባለሙያ ለሰልጣኞች ተናግረው ነበር።

ይህን መሰሉ የሕግ ባለሙዎች ሥልጣንን ያለአግባብ ለጥጦ የመጠቀምና የግል ጥቅምና ፍላጎትን የማስከበር አካሔድ ከዘርፉ ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ጉድለት ጋር ተያይዞ ሲያስተቻቸው ይስተዋላል።

የፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል የመንግሥት ተነሳሽነት
በኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት አካባቢ የተደረገውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ˝ዜጎች ፍትሕን በገንዘብ ሳይሆን በፍርድ ቤት እንዲያገኙ በፅናት እሰራለሁ፣ ለዚህም ወሳኝ የሚባሉ ማሻሻያዎችንም አደርጋለሁ፣ እያደረግሁም ነው˝ በሚል በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ እንደከረመ ይታወሳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም መንግሥት በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የሚታሰበውን ለውጥ ለማምጣት ይተጋሉ በሚል እምነት የጣለባቸውን መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አድርጎ ማሾሙ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ማሳያዎች አሉ።

ከእነዚህ ውስጥም የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ላይ እየተደረገ ያለውን ማሻሻያ የሚገልጸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማሻሻያው ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ዕጩዎች የሚመለመሉበትን መመርያም የሚመለከት እንደሆነ አሳውቋል።

በዚህም የፌዴራል ዕጩ ዳኞችን ለመመልመልና ወጥ ሥርዓት እንዲዘረጋ ለማስቻል የሚያግዝ መመርያን የማውጣት ሥልጣን ያለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞች የምልመላ መመሪያን አሻሽሏል።
ጉባኤው በአዋጅ ቁጥር 684/2002 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የቃል ፈተና በመስጠት የመለመላቸውን 15 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞች ሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ለትችት አቅርቧል።

የመመልመያ መስፈርቱ የእጩውን ማስረጃ የመተንተንና የመመዘን ብቃት፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎችን ጥራት፣ በዳኝነት ሥራ ላይ ያለው ትጋት፣ በሥራ ዘመኑ በሰጣቸው ዳኝነቶች ባለጉዳዩ የረካባቸውና የሚተማመንባቸው መሆን፣ በነፃነት የመዳኘት ቁርጠኝነትና ግለሰባዊ ነፃነታቸውን ማስጠበቅ የሚችሉ፣ ሃቀኛ፣ ከአድልኦ የፀዱ የሚሉትን ትኩረት ይሰጣቸዋል።

የተሻሻለው መመርያ የዕጩ ዳኞች ምልመላ ሒደት የሚጀመረው ከቃል ፈተና መሆኑን ይደነግጋል። በዚህም ጉባዔው በእነዚህ መስፈርቶች መነሻነት መልካም አፈፃፀም አላቸው የተባሉ ባለሙያዎችን በጥናት በመለየት የቃል ፈተና መስጠቱንም አመልክቷል።

በቃል ፈተናውም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን በመምረጥ ሕዝብ ከሰኞ፣ መጋቢት 23 ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ ለአምስት ቀናት አስተያየት አንዲሰጥባቸው የእጩ ዳኞች ሥም ዝርዝር ይፋ ሆኗል። ይህን ተከትሎም ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ሰዎች በእጩዎቹ ላይ ከሥነ ምግባራቸው፣ ከሙያ ብቃታቸው እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ተቀባይነት ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ሰንብተዋል።

ሰሞነኛው የዕጩ ዳኞች ምልመላ
ከዚህ ቀደምም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሾሙ ዕጩ ዳኞች በጉባዔው በኩል ተመልምለው በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሾም ልምድ ነበር።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰለሞን እጅጉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ዕጩ ዳኞችን ማስተቸቱ የተለመደ ተግባር ሲሆን አዲሱ ነገር በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ፈተናው ከቃል መጀመሩ እንዲሁም የመመልመያ መስፈርቶቹ ናቸው። ሰለሞን እንደሚሉት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመለመሉ ዳኞች ቀድመው በሚሰሩባቸው የመጀመሪያና ከፍተኛው ፍርድ ቤቶች ንድፈ ሐሳቡን ስለሚረዱት የጽሑፍ ፈተና መፈተኑ ብቃታቸውን ለመመዘን አዋጭ ባለመሆኑ በየመዋቅሩ ተመልምለው የሚመጡ ዳኞችን መጀመሪያ የቃል ፈተና እንዲወስዱ ማድረጉ የተሻለ መሆኑ ታኖምበታል። በዚህም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የመመልመያ መመሪያውን ማሻሻሉን ያነሳሉ።

አበበ አሳመረ የሕግ ባለሙያ ናቸው፣ ዕጩ ዳኞችን ለሕዝብ ትችት ማቅረቡ በጎ መሆኑን ያምናሉ። ሆኖም አስተያየቱ የመጨረሻ ወሳኝ አለመሆኑን በማስታወስ ግን ደግሞ የሚተቹ ሰዎች በግል ቂምና ቁርሾ ሥማቸው እንዳይጠፋና እንዳይጎዱ ማሰብም ያስፈልጋል ይላሉ።

ማርከሻው ዳምጠው በአማራ ክልል ውስጥ በሰብሳቢ ዳኝነት እያገለገሉ ይገኛሉ። እሳቸው ደግሞ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ˝ነጭ ነጩን አውጥቶ የመናገር ልምድ ባለመዳበሩ˝ ለትችት ማቅረቡ በጎ ቢሆንም የተለየ ነገር ያመጣል ብለው አያምኑም። ሰዎች አስተያየት የሚሰጡት በቅርበት የሚያውቋቸው ላይ መሆኑን የሚናገሩት ሰብሳቢ ዳኛው በዚህም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደመወዝና ደረጃም ከፍ ብሎለት ለሚሔድ ሰው በጎ በጎውን ይናገራሉ እንጂ የሚያውቁት ችግር ቢኖርበት እንኳን የመግለፅ ፍላጎቱ አይኖራቸውምም ይላሉ።

ኹለቱ የሕግ ባለሙያዎች ከዳኞች ምልመላ ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የክልሎች ተዋፅኦ ሳይሆን የዳኖቹ ብቃት መሆን አለበት ይላሉ። ሥራው የፖለቲካ ጉዳይ ባለመሆኑም ዳኞችን ከየክልሉ እንደፖለቲካ ሹመት በብሔር ለመመልመል የሚኬድ ከሆነ አደጋ መሆኑን ያሰምሩበታል። የዳኝነት መስፈርት ብሔሩ ሳይሆን በሙያው ያለው ብቃት ነው የሚሉት ማርከሻው ከአመልካቾቹ ውስጥ በጣም ጠንካራ ተብለው የሚለዩት በአጋጣሚ ከአንድ ክልል ቢሆኑም እንኳን የፍርድ ሒደቱን ገለልተኛና ተዓማኒ ማድረግ እስከቻሉ ድረስ የግድ ከየክልሉ ይውጣጡ የሚባልበት መንገድ መኖር የለበትም ይላሉ።

የዳኝነት ጥራት ከወዴት ይመጣል?
እንደ አበበ እምነት ዳኞች ሲመለመሉ ጨዋነታቸው ወይም ሀቀኝነታቸውን ማረጋገጡ እንዳለ ሆኖ ችሎታን በትኩረት መመልከቱ ይበጃል። ችሎታ ቋንቋንም ይመለከታል የሚሉት አበበ በተለይም የኢትዮጵያ ሕጎች ከውጭ አገራት የተቀዱ በመሆናቸው፥ የዳኞች የእንግሊዝኛና አማርኛ ቋንቋ እውቀት ከፍታ ላይ የደረሰ መሆኑ የግድ ነው ይላሉ። ይግባኝ የሚጠየቅባቸውና የሰበር ጉዳዮች ተደራጅተው የሚቀርቡት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑ እሙን ነው። ስለሆነም እዚህ እርከን ላይ ካሉት ዳኞች የሚጠበቀው ችሎታ አንድም በቋንቋ ኹለትም በሕግ እውቀት መምጠቅን የሚጠይቅ ስለመሆኑ አበበ ያነሳሉ። በሕግ እውቀት ሲባልም የዳኛው የመተንተን ብቃትና ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የመመልከትን አቅም ይመለከታል። አበበ የፍርድ ውሳኔ ጥራት የእነዚህ ድምር ውጤት ነው ይላሉ።

የአበበን ሐሳብ የሚጋሩት ማርከሻው የቃል ፈተናው የተወሰነ ድርሻ ቢኖረውም ዋነኛ ትኩረት መሆን የሚገባው የዳኛው ክህሎት ነው የሚል አቋም አላቸው። ይህም ዕጩው ከዚህ ቀደም ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ምን ያክል ጥራት እንደነበራቸው፤ በሌላ አገላለፅ ምን ያክሉ ይግባኝ ተጠይቆባቸው ተሻሩ ወይም ፀኑ የሚለው እና መሰል የብቃት መመዘኛዎች ብዙ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው ማርከሻው የሚያምኑት።

የዳኝነት ውሳኔው ጥራት አንድ መለኪያ የሚሆነውም ዳኛው በፍርድ ክርክሩ ሒደት የነበረው ሚና (ግልፅነትና ለፍትሕ መቆም) በመጨረሻ አሸናፊውን ብቻ ሳይሆን ተሸናፊውንም የማሳመን ወይም የማስደሰት አቅም እንደሆነም ማርከሻው ያስገነዝባሉ።
የመዝገብና የዳኞች ቁጥጥር ምጥጥኑ በፍርድ ውሳኔ ጥራት ላይ ከፍ ያለ ድርሻ እንዳው የሕግ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ። በፍርድ ቤቶች ላይ ተደጋግመው ከሚነሱ ቅሬታዎች መካከል ዋነኛው የፍርድ መዘግት ወይም ተደጋጋሚ ቀጠሮ በመስጠት ለውሳኔ መዘግየት ነው። ይህ ችግር የሚፈጠረው በዳኞች እጥረት መሆኑን የሚያነሱት ማርከሻው በኢትዮጵያ በዳኞች ቁጥርና በመዝገብ ክምችት መካከል የሰፋ ልዩነት መኖሩን ያስታውሳሉ። ስለሆነም የዳኖችን ቁጥር ማበርከት ለፍርድ ጥራት ወሳኙ ጉዳይ እንደሆነ ይገልፃሉ። በአማራ ክልል የወረዳ ፍርድ ቤት ላይ አንድ ዳኛ በዓመት 385 መዝገቦችን እንዲያይ ደረጃ መኖሩን የሚገልፁት ሰብሳቢ ዳኛው እሳቸው በሚሰሩበት ወረዳ በዓመት አንድ ዳኛ በአማካይ ከ600 በላይ መዝገቦችን እንደሚያይም ያክላሉ። በዚህ ሒደት ዳኛው በርካታ መዝገቦችን በማየት የተሻለ አፈፃፀም ያለው ሆኖ ለመገኘት በመሻትም ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ ለማትኮር እንደሚገደድም ያነሳሉ። ስለሆነም በኢትዮጵያ በዳኝነት ዘርፍ ጥራት ያለው ሥራ ለመከወን ከበዙት መዝገቦች ጋር የሚመጣጠኑ በርካታ ዳኞች እንደሚያስፈልጉም ይመክራሉ።

በኬንያ አንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በሳምንት ከ3 መዝገቦች በላይ አያይም የሚሉት አበበ ‹‹በኢትዮጵያ ግን 50 እና 100›› መዝገብ እንደሚደራረብ በመግለፅ እንደሀኪም እጥረቱ ሁሉ የዳኞች እጥረቱም ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ። አንድ ዳኛ የሚያያቸው መዝገቦች ሲበዙ የውሳኔ ጥራቱ እየቀነሰ እንደሚመጣ በመጠቆም ይታሰብበት ሲሉ ያክላሉ።
ሰለሞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሁን ላይ እልባት ሳያገኙ የሚገኙት መዝገቦች ዕድሜ ከአንድ ዓመት በታች መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ይህ የሆነው አሁን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉት 36 ዳኞች የእረፍት ጊዜያቸውን ሰውተው በመሥራታቸው ነው የሚሉት ሰለሞን አሁን የሚጨመሩት 15 ዳኞች መዝገቦችን በማቃለልና የፍርድ ውሳኔ ጥራትን ከፍ በማድረግ ላይ በጎ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተስፋ አድርገዋል።

አበበ የተሻለ የፍርድ ሥርዓትን ለመፍጠር የሚያግዘው ዳኞችን ውጥረት ውስጥ በማስገባት በርካታ መዝገቦችን እንዲያዩ በማድረግ አይደለም ይላሉ። ይልቁንም በየሕግ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤትና በጎ ስብዕና ያላቸውን እየመለመሉ ወደዳኝነት ስርዓቱ ማምጣትን እንደአንድ ዘላቂ መፍትሔ አቅርበዋል። ተያይዞም የሕግ ጉዳይ ፈርጀ ብዙ በመሆኑ በንግድ፣ በቤተሰብ፣ በወንጀል ወዘተ የሕግ ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን እያላቁ (ʻስፔሻላይዝʼ እያደረጉ) የሚመጡ ባለሙያዎችን በብዛት ማፍራትም እንደሚገባ ያላቸውን ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

የሕግ ባለሙያዎቹ የፍርድ ቤት ነፃነት እየተረጋገጠና ውጤቱም ተዓማኒ (የጥራት መለኪያው የውሳኔዎች ተዓማኒነትና ገለልተኛ መሆኑን ልብ ይሏል) እየሆነ የሚሔደው ግን ጊዜያዊ በሆኑ የእጩዎች ምልመላና ማስተቸት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት በሚገነባ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሆነም ይስማማሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here