አባይ 102.9 ኤፍ ኤም ኪሳራ ማወጁን ተከትሎ በሀራጅ ሊሸጥ ነው

0
675

አባይ ኤፍ ኤም የሬዲዮ ጣቢያ በአሁኑ ጊዜ የከሰረና ሥራ ለመቀጠል አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ሊያገኝ ያልቻለ በመሆኑ በንግድ ሕግ መሠረት ኪሳራን በማወጅ ለመዝጋት ሒደት ላይ እንደሆነና በደረሰበት ኪሳራ ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 8 የሐራጅ ሽያጭ ተመን እንደሚያወጣ ተገለፀ።

የ14 ሠራተኞች ከመስከረም እስከ ጥር ያለው የአምስት ወራት ደሞዝ ባለመከፈሉ፣ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እያየው እንደሆነና ˝ድርጅቱ ስለከሰረ ዕቃ ሸጠን እንከፍላችኋለን˝ የሚል በደብዳቤ እንደደረሳቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ዐሥር የሚሆኑ የአባይ ኤፍ ኤም ሠራተኞች በቂርቆስ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ድርጅቱን የከሰሱት ሲሆን ከ3 እስከ አምስት ወር ደሞዛቸውና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞቻቸው ዐሥር የሚሆኑ እንዲከፈላቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል።

ድርጅቱና ሠራተኞቹ ክፍያው እንዲፈፀም ስምምነት ላይ ቢደርሱም እስካሁን ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልተከናወነላቸው ማረጋገጥ ተችሏል።

በተቋሙ ከዐሥር የማይበልጡ ተባባሪ አዘጋጆች የነበሩ ቢሆንም ወደ ገበያው ለማምጣት ተቋሙ ድክመት ያለበት በመሆኑ ተባባበሪ አዘጋጆች ረግተው አለመቀመጥ ችግር እንደነበርና በሥራ ሒደት ወቅት የተደራጀ የሰው ኃይል ባለመኖር ክፍተት እንደነበረ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ገብረጊዮርጊስ አብርሃ ሚዲያው ከስርጭት ሲወጣ እና ያጋጠመውን ችግር በወቅቱ ማሳወቅ ነበረበት፣ ምን ችግር እንዳለ በደብዳቤ ጠይቀናቸው እስካሁን ምላሽ አልሰጡንም፣ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ እንዳላቸው አናውቅም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሕጉ ማንኛውም ብሮድካስት ችግር ሲጋጥመው ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ አለበት የሚል ሲሆን ለ3ኛ ወገን መሸጥም አይችልም ብለዋል።

አባይ ኤፍ ኤም የዛሬ አምስት ዓመት በኤች ኤች እና ቲዋይ ቲ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን የተመሰረተ ሲሆን በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት ከስምንት እስከ ዐሥራ አምስት ፕሮግራሞችን በተለያየ ወቅት ያስተላለፍ ነበር።

በኢትዮጵያ ከ95 በላይ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ሲኖሩ 28 የሚሆኑት የግል ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ጣቢያዎች በገጠማቸው የገቢ መቀነስ ምክንያት ችግር ውስጥ ላይ ናቸው። ለአብነትም ከዓመት በፊት ከመቶ በላይ ሠራተኞች የነበሩት ኢኤን ኤን የነበረው ጣቢያ ከፋይናንስና ሌሎች ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ችግር መዘጋቱ ይታወቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here