የአደንዛዥና አነቃቂ ዕፆች ዝውውር ሳይቃጠል በቅጠል

0
711

ጥናቶች የአደገኛ ዕፅና መድኀኒቶች ተጠቃሚነት ከሰው ልጅ ዕድሜ ታሪክ እና ጋር አቻ እንደሆነ ይጠቁማሉ። በጥንት ጊዜ የሰው ልጅ የተክሎችን የተለያዩ አካላት ማለትም እንደ ሥር፣ ቅጠል፣ ግንድና ፍሬ በመጠቀም የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ድርጊቶች ላይ ይጠቀሙ ነበር። ሆኖም ግን ሳይንስና ቴክኖሎጂ እያደገና እየተለወጠ ሲመጣ ሰዎች እነዚህን ዕፆችና መድኀቶችን ለተባለው ጉዳይ የመጠቀም ተግባራቸው እየቀነሰ መጥቷል። ነገር ግን በአደንዛዥ ወይም አነቃቂ ዕፆች መልኩ መልሰው መጠቀማቸው የዘመናችን አዲስ እውነታ ሆኗል።

ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት የጥቂት አገሮችና ሕዝቦች ችግር የነበረው አደንዛዥ/አነቃቂ ዕፅ ተጠቃሚነት፥ በአሁኑ ወቅት ዓለም ዐቀፋዊ ችግር በመሆኑ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ዕውቅናና ትኩረት ተሰጥቶታል። አደንዛዥ/አነቃቂ ዕፅ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት ስለማግኘቱ ለአብነት ከሚጠቀሱት መካከል በ1971 (እ.ኤ.አ.) የፀደቀው የሳይኮትሮፒክ ዕፆች ቃል ኪዳን፣ የናርኮቲክ መድኀኒቶችና የሳይኮትሮፒክ ዕፆች ሕገ ወጥ ዝውውርን ለመቆጣጠር በ1988 (እ.ኤ.አ.) የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል ኪዳንና በ1999 (እ.ኤ.አ.) እንደ አዲስ ተደራጅቶ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመድኀኒቶች ቁጥጥርና ወንጀል መከላከል ጽሕፈት ቤት (UNODCCP) መቋቋም ይገኙበታል።

የመንግሥታት የመድኀኒቶች ቁጥጥርና ወንጀል መከላከል ጽሕፈት ቤት በ2017 (እ.ኤ.አ) መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከ200 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸዉ ከ15-64 ዓመት የሆኑ ተጠቃሚዎች አሉ። ይህ ማኅበራዊ ዕፆች የሚባሉትን አልኮል፣ ጫትና ሲጋራን ሳያጠቃልል ማለት ነው። ሪፖርቱ የተጠቃሚዎችን ማኅበራዊ ዳራ በተመለከተ ከቤት አልባ ዜጎች እስከ ከፍተኛ የምንዳ ተከፋይ ባለሙያዎችን፣ የኮሌጅ ተማሪዎች፣ በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ፣ ገበሬዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንደሚያካትት ጠቁሟል። ከአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች መጨመር ጋር በተያያዘ በተለይ በሕፃናትና በሴቶች ላይ የሚደረሰውም ጉዳት በዛው ልክ መጨመሩን ነው ሪፖርቱ ያመላክታል።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል የአደገኛ ዕፆችና መድኀኒቶች ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታን ስንመለከት በ3 ዓመት ውስጥ ብቻ 543 ሺሕ 439 ኪሎ ግራም ካናቢስ፣ 208 ሺሕ 172 ኪሎ ግራም ኮኬይን፣ 4 ሺሕ 09 ኪሎ ግራም ሄሮይን፣ 6 ሺሕ 300 ኪሎ ግራም ሜታ ኢፍታሚን በአገራችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ተግባሩን የፈፀሙ 42 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው 46 ክስ እንደተመሠረተባቸው ይታወቃል።

በ2011 ግማሽ ዓመት ብቻ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ሲል የተያዘው 123 ሺሕ 756 ነጥብ 31 ኪሎ ግራም የኮኬይን ዕፅ ሲንቀሳቀሱ መያዛቸው እንዲሁም፣ ዕፆቹ በብዛት የሚተላለፉት በሆድ ውስጥ መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያሳያል።

ካናቢስ በማምረት አደገኛ ተብለው የተፈረጁት ቦታዎች ኦሮምያ፣ ደቡብ ፣ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች መሆናቸው ደግሞ የአገሪቱን ከግማሽ በላይ ሕዝብ ያለበትን አካባቢ ተጠቂ እንዳያደርግ ያሰጋል። ካናቢስ ተብሎ የሚጠራው ዕፅ በዓለማችን በስፋት የሚለማና በብዛት ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ተጠቃሚዎቹም ከ140 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርሱ በጉዳዩ ላይ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ትልቁ ችግር በአገራችን የተከለከሉ መድኀኒቶች እና አልኮልን የመጠቀም ባሕሪይ እየተስፋፋ መምጣቱ እንደ ከፍተኛ ሥጋት እየተገለጸ ነው። ከዚህም አንፃር የችግሩ ገጽታ በዋናነት አገሪቷን እንደ ማስተላለፊያ ወይም እንደመሸጋገሪያ መጠቀም መቻሉ ይታወቃል። በሌላ በኩል የአልኮል እና የሲጋራ ሱሰኝነት፣ የጫትና ካናቢስ ተክልን በሥፋት የማልማት፣ የመነገድ፣ እንዲሁም ሄሮይንና ኮኬይንን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በመርፌ መልክ መወሰዳቸው ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው።

የፖሊስ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ ወጣቶቹ ወደዚህ ወንጀል የሚገቡት ዕፆቹ የሚያመጡትን ጉዳት ባለማወቅ፣ በጓደኞች ግፊት፣ ዕፆችንና መድኀኒቶችን በቀላሉ በማግኘት ነው። የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መጨመር፣ ከሥራ እና ከትምህርት ቤት ውጪ ወጣቶች የሚያሳልፉባቸው የመዝናኛ ቦታዎች በብዛት አለመኖር ወጣቶችን ለአደገኛ ሱሶች እንደሚዳርጋቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

በተጨማሪም በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው የወሲብ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱንም መረጃዎቹ ያሳያሉ። ʻኢትዮጵያን ጆርናል ኦፍ ሄልዝ ዴቨሎፕመንትʼ የተባለው መጽሔት በ2008 ባወጣው ሪፖርት ለወንድ ሕፃናትና ወጣቶች መደፈር በምክንያትነት ከቀረቡት መካከል አንዱ የዕፅ ተጠቃሚነት ነው። ሀብታሞችና አዛውንቶች አደገኛ ዕፅ በመጠቀም በጎዳና ተዳዳሪ ወንድ ሕፃናት ላይ ጥቃት በማድረስ ግንባር ቀደም መሆናቸው በጥናቱ ተጠቅሷል።

የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርና ተጠቃሚነት በአገር ላይ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በማስመልከት አዲስ ማለዳ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመሆን ከፍተኛ ሥራ መሥራት ካልቻሉ አገርን ከባድ ፈተና ላይ እንደሚጠል ልብ ሊሉ ይገባል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here