በኢትዮጵያ የአደገኛ ዕፆች ዝውውር አሳሳቢ ሆኗል

0
1554
  • በ2011 ግማሽ ዓመት ብቻ ከ123 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ ኮኬይን ሲዘዋወር ተይዟል
  • በሻሸመኔ አካባቢ በ2 ሺሕ 840 ካሬ ሜትር በላይ የካናቢስ ተክል ተገኝቷል

በ2011 ግማሽ ዓመት ብቻ 123,756.31 ኪሎ ግራም የኮኬይን ዕፅ ሲዘዋወር መያዙን የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ዕፆቹ በብዛት የሚዘዋወሩት በሆድ ዕቃ ውስጥ፣ በፓንት፣ በዳይፐር፣ በጸጉር፣ በጫማ፣ በሥጦታ ዕቃዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ስዕሎች፣ በመኪና መለዋወጫዎች ውስጥ በመደበቅ እንደሆነ በተለይ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በሩብ ዓመቱ በቦሌ ዓየር ማረፊያ በኩል 48 ተጠርጣሪዎች ዕፅ ለሳማለፍ ሲሞክሩ የተያዙ ሲሆን፣ በሁሉም ላይ ምርመራ ተጣርቶባቸው ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ከፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በዚህ ዓይነት ወንጀል በብዛት የሚሳተፉት የናይጄሪያና ብራዚል ዜጎች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በ2010 በአጠቃላይ 81 የኹለቱ አገራት ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ ተጣርቶባቸው ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ በማረሚያ እንደሚገኙም ታውቋል።

ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት የጥቂት አገሮችና ሕዝቦች ችግር የነበረው አደንዛዥ ዕፅ በአሁኑ ጊዜ ዓለም ዐቀፋዊ ችግር በመሆኑ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ዕውቅናና ትኩረት ተሰጥቶታል። በ1971 (እ.ኤ.አ.) የፀደቀው የሳይኮትሮፒክ ዕፆች ቃል ኪዳን፣ የናርኮቲክ መድኀኒቶችና የሳይኮትሮፒክ ዕፆች ሕገ ወጥ ዝውውርን ለመቆጣጠር በ1988 (እ.ኤ.አ.) የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል ኪዳንና በ1999 (እ.ኤ.አ.) እንደ አዲስ ተደራጅቶ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመድኀኒት ቁጥጥርና ወንጀል መከላከል ጽሕፈት ቤት (UNODCCP) መቋቋም ለአደንዛዥ ዕፅ የተሰጠውን ዓለም ዐቀፍ ትኩረት ማሳየት ይችላሉ።

የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ምንድን ነው?
የአደገኛ ዕፅና መድኀኒቶች ተጠቃሚነት የሚሰጠዉ ጽንሰ ሐሳብ ትርጓሜ የእንግሊዘኛዉን drugs and substance abuse የሚለዉን አይተረጉመዉም ሆኖም፣ “UNODCCP” በ2000 (እ.ኤ.አ.) በሰጠው የቃላት ፍቺ መሠረት አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት (Drug Abuse) ማለት፣ ዓለም ዐቀፋዊ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሳይኮአክቲቭ ውጤት ያላቸውን ዕፆች ከሕክምና ወይም ሳይንሳዊ ዓላማ ውጪ መጠቀም ነው። የአደገኛ ዕጽና መድኃኒት ተጠቃሚ ማለት አዕምሮን በማነቃቃት በተጠቃሚዉ ላይ የተለየ ባሕሪይ እንዲታይና ድርጊት እንዲፈጽም የሚያደርግ በመርፌ፣ በእንክብል፣ በማሽተትና በማኘክ የሚወሰድ ማንኛዉንም ነገር አዘዉትሮ በመጠቀም የዳበረ ልምድ ወይም ሱስን የሚያካትት ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው የአልኮልና የመድኀኒቶች የቃላት መፍቻ መጽሐፍ (Lexicon) መሠረት፣ ሳይኮአክቲቭ ውጤት ያላቸው ዕፆች የሚባሉት ወደ ሰውነት ሲገቡ የአዕምሮን የአስተሳሰብ ወይም የስሜት ሒደት የሚለውጡ መድኀኒቶች ናቸው። በዚሁ ሰነድ የተሰጠው ሌላ ፍቺ እንደሚያመለክተው ሳይኮትሮፒክ ወይም ሳይኮአክቲቭ ዕፆች የሚባሉት ኬሚካላዊ ይዘታቸው በዋነኝነት በተጠቃሚው ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ መድኀኒቶች ናቸው።

ድርሳናት እንደሚገልጹት የአደገኛ ዕፅና መድኀኒቶች ተጠቃሚነት የሰዉ ልጅ ዕድሜ ታሪክ ያለዉ ሲሆን በጥንት ጊዜ የሰዉ ልጅ የተክልን የተለያዩ አካላት/ሥር፣ ቅጠል፣ ግንድና ፍሬ ወዘተ በመጠቀም የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ድርጊቶች ላይ ይጠቀሙ ነበር። ሆኖም ግን ሳይንስና ቴክኖሎጂ እያደገና እየተለወጠ ሲመጣ ሰዎች እነዚህን ዕፆችና መድኀቶችን ለተባለዉ ጉዳይ የመጠቀም ተግባራቸዉ እየቀነሰ መጥቷል።

በተቃራኒዉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ስሜትን ለመቀየር እና አዕምሮን ከጭንቀትና ጫና ለመከላከል አገልግሎት በፍጥነት እየዋሉ መጥተዋል፤ ሆኖም እስከ 1990ዎቹ የአደገኛ ዕጾችና መድኀኒቶችን ለዚህ ጉዳይ በመጠቀም አልተስፋፋም ነበር። በግልጽ የማይታይ (ድብቅና) የመገናኛ ብዙኀንን ቀልብ ያልሳበና በኢንደስትሪ ደረጃ እየተመረተ ትርፍ የሚዛቅበት ችግር አልነበረም። ከተጠቀሰዉ ጊዜ በኋላ ግን ዓለም ዐቀፍ አዘዋዋሪዎች የሚሳተፉበትና የብዙ ሚሊዮን ዶላር ትርፍ የሚገኝበት ንግድ ሆነ።

የተባበሩት መንግሥታት የአደገኛ መድኀኒቶችና ወንጀል ቢሮ ባወጣዉ ሪፖርት ላይ ከ200 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸዉ ከ15 እስከ 64 ዓመት የሆኑ ተጠቃሚዎች አሉ። ይህ ማኅበራዊ ዕፆች የሚባሉትን አልኮል ጫትና ሲጋራን ሳያጠቃልል ነዉ። ይህ የተጠቀሰዉ መረጃ ከቤት አልባ ዜጎች እስከ ከፍተኛ የምንዳ ተካፋይ ባለሙያዎችን የኮሌጅ ተማሪዎች፣ ዝሙት አዳሪዎች፣ ገበሬዎችና የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን ያካትታል። ካናቢስ ተብሎ የሚጠራዉ ዕጽ በዓለማችን በስፋት የሚለማና በብዛት ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ተጠቃሚዎቹም ከ140 ሚሊዮን በላይ ይደርሳሉ።

የአደገኛ ዕፆችና መድኀኒቶች ዝውውርና ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ
አገራችንን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም የሚደረግ የአደገኛ ዕፅ ዝውውርን በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት በብዛት የሚነሳው ከብራዚል ሲሆን፣ ኢትዮጵያን እንደትራንዚት በመጠቀም ወደ ቤይሩት፣ ከዚያም ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ወደ ተለያዩ የአውሮፓና አሜሪካን አገራት እንዲደርስ ይደረጋል።

በ2011 ግማሽ ዓመት ብቻ 123,756,31 ኪሎ ግራም የኮኬይን ዕፅ ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ያስታወቀው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ ዕፆቹ በብዛት የሚተላለፉት በሆድ ውስጥ አድርጎ በማሳለፍ፣ በፓንት፣ በዳይፐር፣ በጸጉር፣ በጫማ፣ በስጦታ ዕቃዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ስዕሎች፣ በመኪና መለዋወጫ ዕቃ በመደበቅ እንደሆነ ገልጸውልናል።
በመሆኑም በሩብ ዓመቱ በቦሌ ኤርፖርት በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ 48 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን፣ በሁሉም ላይ ምርመራ ተጣርቶባቸው ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ከፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአገራችን የተከለከሉ መድኀኒቶች እና አልኮልን የመጠቀም ባሕሪይ እየተስፋፋ መምጣቱ እንደ ከፍተኛ ስጋት እየተገለጸ ነው። ከዚህም አንፃር የችግሩ ገጽታ በዋናነት አገሪቷን እንደ ማስተላለፊያ ወይም እንደ መሸጋገሪያ መጠቀም መቻሉ ይታወቃል። በሌላ በኩል የአልኮል እና የሲጋራ ሱሰኝነት፣ የጫትና ካናቢስ ተክልን በስፋት የማልማት፣ የመነገድ፣ እንዲሁም ሄሮይንና ኮኬይንን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በመርፌ መልክ መወሰዳቸዉ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸዉን የፌደራል የመድኀኒትና ምግብ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ብሔራዊ የመድኀኒት ቁጥጥር ስትራቴጂ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀሎች ዘገባ ሰነዶች ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል የአደገኛ ዕፆችና መድኀኒቶች ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታን ስንመለከት በ3 ዓምት ዉስጥ ብቻ 543.439 ኪሎ ግራም ካናቢስ፣ 208.172 ኪሎ ግራም ኮኬይን፣ 4.09 ኪሎ ግራም ሄሮይን፣ 6.300 ኪሎ ግራም ሜታ ኢፍታሚን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ተግባሩን የፈጸሙ 42 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው 46 ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ከ2003-2005 ባሉት ዓመታት ብቻ ከዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ 1363 ሰዎች ላይ 1095 ክስ መመስረቱን አስታዉቋል።

በአገራችን የአደገኛ ዕጽና መድኀኒቶች ተጠቃሚ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ የመጣ ችግር መሆኑን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ እያሳተመ የሚያወጣዉ አዲስ ምዕራፍ መጽሔት ያቀረበ ሲሆን፣ በጽሁፉም ታዳጊዎችና ወጣቶች የዚህ ችግር ዋነኛ ተጠቂዎች ሲሆኑ እነዚህ ታዳጊዎች ለዚህ ችግር ተጋላጭ የሆኑት ገና 15 ዓመት ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸዉ በፊት መሆኑን ይጠቁማል።

የአደገኛ ዕፅና መድኀኒቶች ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት በ2018 (እ.ኤ.አ.) የተካሔደ ሲሆን ይህም 25 ከተሞችን የሸፈነ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም መሰረት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጫት፣ አልኮል፣ ትንባሆ፣ ሐሺሺ (ካናቢስ) እንደሚወስዱ በተለያዩ መንገዶች ተረጋግጧል። በአነስተኛ ደረጃ ሄሮይንና ኮኬይን የተባሉት ዉድ መድኀኒቶች ጥቅም ላይ እንደሚዉሉ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ጥናቱ የተካሔደው በነጋዴዎችና ቤተሰቦቻቸዉ፣ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት፣ ተማሪዎች፣ ዝሙት አዳሪዎች፣ ወጣት እና የገጠር ሙስሊም ማኅበረሰቦች አባላት ላይ ነው።

የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መረጃ መሰረት፣ በዚህ ወንጀል በብዛት የሚሳተፉት የናይጄሪያና ብራዚል ዜጎች ናቸው። በ2010 81 የኹለቱ አገራት ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን፣ በሁሉም ላይ ምርመራ ተጣርቶባቸው ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ በማረሚያ ይገኛሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአደገኛ ዕጾች ተጠቃሚ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በሕፃናት እና በሴቶች ላይ የሚደረሰውም ጉዳት ጨምሯል። የተወካዮች ምክር ቤት በ2008 የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት ማስታወስ ይቻላል።

ካናቢስ በማምረት አደገኛ ተብለው የተፈረጁት ቦታዎች ኦሮምያ፣ ደቡብ ፣ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ናቸው። በኦሮምያ በሻሸመኔ አካባቢ ከ2 ሺ 840 ካሬ ሜትር በላይ የካናቢስ ተክል ተገኝቷል።

በአደገኛ ዕፆች የተጠቁት ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሲሆኑ፣ ፖሊስ እንደሚለው ወጣቶቹ ወደዚህ ወንጀል የሚገቡት ዕፆቹ የሚያመጡትን ጉዳት ባለማወቅ፣ በጓደኞች ግፊት፣ ዕፆችንና መድኀኒቶችን በቀላሉ በማግኘት ነው። የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መጨመር፣ ከሥራ እና ከትምህርት ቤት ውጭ ወጣቶች የሚያሳልፉባቸው የመዝናኛ ቦታዎች በብዛት አለመኖር ወጣቶችን ለአደገኛ ሱሶች እንደሚዳርጋቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

አንዳንድ የፖሊስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአደገኛ ዕፆች ዝውውር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ጸጥታ አስከባሪዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ይገኙበታል።

ተከትሎ የሚመጣው ጥቃት
የፌደራል ፖሊስ መረጃ አደገኛ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች በሴቶች፣ በወንድ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ የሚያደርሱት ወሲባዊ ጥቃት ጨምሯል። ከሦስት ዓመት በፊት በ520 ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት 14 በመቶ የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው አስገድዶ መድፈር አጋጥሞአቸዋል። 26 በመቶው የመደፈር ሙኩራ፣ 25 በመቶው በአስገድዶ መድፈር ለአልተፈለገ እርግዝና ተዳርገዋል።

በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው የወሲብ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱንም መረጃዎቹ ያሳያሉ። ኢትዮጵያን ጆርናል ኦፍ ሄልዝ ዴቨሎፕመንት የተባለው መጽሔት ባወጣው ሪፖርት ለወንድ ሕፃናትና ወጣቶች መደፈር በምክንያትነት ከቀረቡት መካከል አንዱ የዕፅ ተጠቃሚነት ነው። ሀብታሞችና አዛውንቶች አደገኛ ዕፅ በመጠቀም በጎዳና ተዳዳሪ ወንድ ሕፃናት ላይ ጥቃት በማድረስ ግንባር ቀደም መሆናቸው በጥናቱ ተጠቅሷል።

በጥናቱ አስደንጋጭ ሆኖ የቀረበው ፖሊሶችና ሌሎች ባለሙያዎች በጥቃቱ ተሳታፊ መሆናቸው፤ እንዲሁም የምርመራው ሒደት ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጽዕኖ ማድረጋቸው የሚለው ክፍል ነው። አንድ የፖሊስ መኮንን ”በጉዳዩ ጥቂት ደረጃ ላይ እንደደረስክ ርቀህ እንዳትሔድ በአንዳንድ ኃላፊዎች ትከላከላለህ። ከተወሰነ ደረጃ በኋላም ክትትል እንድታቆም ትታዘዛለህ” ሲል ለአጥኚዎች ተናግሯል።

የምጣኔ ሀብታዊ ድቀት
በአንድ ሀገር አምራችና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሚባለው ከ15 እስከ 64 ዕድሜ ድረስ ያለው የሰው ኃይል ሲሆን፣ ከ65 ዓመት በላይ የሚገኙ አረጋውያንና ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናት ደግሞ ጥገኛ ወይም በኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሌላቸው እንደሆኑ የሥነ-ምጣኔ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ስለዚህ የአንድ አገር አምራች ኃይል ሲታመምና በሞት ሲለይ፣ በሱስ ሲጠመድ፣ የምርት መጠን የሚቀንስና ተተኪ የሰው ኃይል እስኪዘጋጅ ድረስ ኢኮኖሚው እንደሚናጋ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሃቢስ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት፣ ለ40 ሺሕ ያህል ታማሚዎች ወይም በሥራ ገበታቸው ላይ ላልተገኙ ለሱስ አገጋሚ ሠራተኞቹ ማስታመሚያ በዓመት 12 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ የሚናገሩት ሃቢስ፥ ከእነዚህም ውስጥ በአመዛኙ የሚሞቱ ናቸው ብለዋል። እንግዲህ የበለጸገችዋን አሜሪካን ችግሩ ይህን ያህል ከነቀነቃት ኢትዮጵያንና ሌሎች ደሀ አገራትንማ እንዴት ይምራቸዋል ሲሉ በምሳሌ ያስረዳሉ።

ዕፅ ተጠቃሚዎች ከሚገጥማቸዉ የጤና ችግር ባሻገር በዕለት ተግባራቸዉ ላይ ማከናወን የሚገባቸዉን ያህል ሳያከናዉኑ የሚቀሩ ሲሆኑ ማኅበራዊ ቀዉሱም ከፍተኛ ነዉ። ትምህርት ከመቋረጥ አንስቶ የቤት ዉስጥ ጥቃት ምጣኔ ሀብታዊ ጫናና ደኅንነትን ማጣት ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ። በመሆኑም ማኅበራዊ አስተሳሰብን ለመለወጥ እንደአገር በስፋት መሠራት አለበት እንደምጣኔ ሀብት ባለሙያው አስተያየት።

የአዕምሮ ሕመም
ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች ሰዎች የተለየ የአዕምሮ ሕመም እንደሚያጋጥማቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል። ስለ ዐመፃ ተግባራቸው፣ በቤተሰቦቻቸውና ኅብረተሰቡ ስለሚገለሉ በታናሽነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከባድ ለሆነ የአዕምሮ ሕመም ይዳረጋሉ። የጥፋተኝነት መንፈስ፣ ፍርሃት፣ ድብርት፣ ብስጭት፣ ራስን ለማጥፋት መነሣሣት ወዘተ ዓይነቶቹ ስሜት በሱሰኝነት የሚመጡ ናቸው።

በጥፋተኝነት ስሜት ደግሞ ሁሉም አብዛኞቹን ራስን በራስ እስከ ማጥፋት ግዴለሾች ናቸው። የአንድ ዕፅ ተጠቃሚ ዕድሜ ከአንድ ጤነኛ ሰው በ24 ዓመት ያህል ያነሰ እንደሚሆን ጥናቶች ያሳያሉ። በሚያድርባቸው ክፉ መንፈስ የተነሣ ሰዎችን የመጥላት፣ የመተናኮል፣ የመበቀልና ለማናቸውም ግጭቶች በቀላሉ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

በዓለማችን ከሚሠራጨው የአደንዛዥ ዕፅ ምርት ሰፊውን ድርሻ የያዙት ኮሎምቢያና ሜክሲኮ ውስጥ የሚገኙ የአደንዛዥ ዕፅ አብቃይ፣ አከፋፋይና ተጠቃሚ ቡድኖች (Drug Cartels) የአገራቸውን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን በሥልጣን ላይ ካሉ መንግሥቶቻቸው የላቀ ተፅዕኖ ማሳደር ችለዋል። እነዚህ አገሮች የአደንዛዥ ዕፅ ምርትን፣ ሥርጭትንና ተጠቃሚነትን ለመቆጣጠር ለዘመናት ቢለፉም በቀላሉ የማይወጡት ቀጥ ያለ ዳገት ሆኖባቸዋል። በዚህ የተነሳም ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞቻቸውና የመንግሥት አመራሮቻቸው ሳይቀሩ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምና ማሠራጨትን ሕጋዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በኢትዮጵያም እንዲህ ዓይነቱ ዘመቻ ይካሔድ ዘንድ የሚወተውቱ በርካቶች ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here