ሚንስቴሩ እሳቱ ጠፍቷል መባሉ አዘናግቶኛል አለ

0
868

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከተነሳ የሰነበተው የእሳት ቃጠሎ አደጋ በመሐል ጠፍቷል መባሉ አዘናግቶኛል ሲል የባሕልና ቱሪዝም ሚንስቴር ገለፀ።

ሚንስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) እሳቱ በተነሳበት ወቅት ለማጥፋት እንዲቻል ከውጭ አገራት የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ድጋፍ ጥየቃን ጨምሮ የተጀመሩ ዝግጅቶች እንደነበሩ ገልፀው ነገር ግን በመሐል እሳቱ ጠፍቷል መባሉ እንዳዘናጋቸው ተናግረዋል።

ከሰሞኑ ጠፍቷል የተባለው እሳት ማገርሸቱን ተከትሎም ሚንስቴሩ ከኬንያና ደቡብ አፍሪካ የሄሊኮፕተር ድጋፍ ለማግኘት ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ ስለመሆኑ ምንስትሯ አክለዋል።

አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት እትሟ በፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለውን የእሳት አደጋ ፈጥኖ ለመቆጣጠር እንዲመች የባሕልና ቱሪዝም ሚንስቴር የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሮች እንዲገዙለት ስለመጠየቁ መዘገቧ ይታወሳል።

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በጥቅምት 2011 ቃለ ምልልስ የነበራቸው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ብሔራዊ ፓርኮችን ጨምሮ ከዋና መስመር ውጭ በሆኑ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የእሳትና ሌሎችም አደጋዎች ቢከሰቱ መንግሥት ፈጥኖ መድረስና አደጋውን መቆጣጠር የሚያስችለው እንደሄሊኮፕተር ያሉ ዘመናዊ ማሽኖች እንደሌሉት በመግለፅ ሊታሰብበት ይገባል ማለታቸውን አስነብበን ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here