“መደመር” እና የነገዋ ኢትዮጵያ

0
857

የለውጥ ተስፋ ከዚያ የመከነ የለውጥ ዕድል ትዝታ ታሪኳን ደጋግሞ የሚጎበኛት ኢትዮጵያ አሁንም የለውጥ ጎዳና ላይ ነች ማለት ይቻላል። ይነገር ጌታቸው ይህንን በማጤን የአሁኑ ለውጥ እና የመደመር ፍልስፍናው አዲስ ሳይሆን ደግመን እየደገምነው ያለነው ታሪካችን ነው በሚል ክፍል አንድ ያስነበቡን ቀጣይ እና የመጨረሻ ክፍል እነኾ ስለ ኢትዮጵያ ነገ!

የክሽፈት አዙሪት
አምስት ያልተሳካ የለውጥ ጅምር ያደረገችው ኢትዮጵያ ፊቷን ወደዛሬ አዙራለች። ይህን ታሪኳን ረስታም ከአሁን ጋር አብራለች። ግን አይቻልም። ትናንት የሔድነበትን መንገድ ሳንፈትሽ ዳግም ጉዞ ብንጀምር መዳረሻችን ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ትናንትን ተውሰን ዛሬን ተንተርሰን ስለነገ ማውራት እንጀምር።

“Ethiopian’s Dailemma: Missed Chances from 1960s to the Present” በሚለው ጥናታቸው ዶናልድ ሌቪን ኢትዮጵያ የለውጥ ሾተላይ የተጠናወታት በሦስት ምክንያት ነው ይላሉ። የመጀመሪያው ሰምና ወርቅ ይባላል። ቀጣዩ ጀግንነት ከሚሉት አገራዊ ትርክት ይቀዳል። የመጨረሻው የውጭ ተፅዕኖ ነው። ሰምና ወርቅ ትውፊታዊውን ሥነ ግጥማችንን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካችንንም ተጨኖታል። ወዳጃም የሚመስሉ ፖለቲከኞች እርስ በርስ አይተማመኑም። ሌቪን ለዚህ ማሳያ እንዲሆናቸው የመንግሥቱ ነዋይን ቁጭት ያነሳሉ። የ1953 መፈንቅለ መንግሥትን የመሩት ሰው ንጉሡን ለማውረድ መወጠናቸውን ለመንግሥት ግልበጣው አጋዥ ለሚሆኑ ወዳጆቻቸው እንኳን ለማካፈል አልሞከሩም ነበር።

ሁሉም ነገር እንዳልሆነ ሁኖ የሞት ፍርድ ፅዋቸውን ሊጎነጩ ቀናት ሲቀራቸው ግን መፈንቀለ መንግሥቱን ያከሸፉት የቀድሞው ወዳጃቸው ጄነራል መርዕድ አላስችል ብሏቸው ሊጠይቋቸው መጡ። በጥይት ተመተው ሆስፒታል አልጋ ላይ የነበሩት ጄነራል መንግሥቱ ለምን ጄነራል መርዕድን ማመን ተሳነኝ ብለው ራሳቸውን ደጋግመው ወቀሱ። ቁጭቱ የግለሰብ ቁጭት አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልኂቃን አሁንም አይተማመኑም። አቆርቋዥና አድኀሪ፣ ትምክህትኛና ጠባብ የሚሉ ከፋፋይ ቃላት የዘመን መልክ ተቀብተው ለውጥ ደጋፊና አደናቃፊ በሚሉ ተተክተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለውጥን ለመጨረስ ያለመታደሉ ሌላው መነሻ ከጀግንነት ፅንሰ ሐሳብ ለመመነን አለመታደሉ ነው።ለውጥ ማለት ማሰር ማሳደድ እስኪመስል ድረስ የአዲስ አመራር የየዕለት ተግባር ይኼው ይሆናል። ወደፊት ከመጓዝ ይልቅ በታሪክ ተብሰልሳይነት ራስን መጥለፍ ተዘውትሯል። ሌቪን ኢትዮጵያዊነት እንኳንስ ሥልጣን ይዘው ተስፋ ቆርጠውም ጀግንነታቸውን ማሳየት ለምዶባቸዋል ይላል። ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ያቀዱት መፈንቅለ መንግሥት እንደከሸፈ ሲገባቸው ያካሔዱት የመጨረሻ ተግባር በእጃቸው የነበሩትን መኳንንት በያዙት መሣሪያ መጨረስ ነበር። መንግሥቱ ኃይለማሪም ፊውዳሊዝም ይውደም ብሎ ወደፊት ከመራመድ ይልቅ በታሪክ ተብሰልሳይነት የንጉሡን ባለሥልጣናት አሰረ። ረሸነ።

ኢሕአዴግ ሥልጣነ መንበሩን ሲረከብም የፖለቲካ ትውፊታችን አብሮት ነበር። የደርግ ሰዎችን አሰረ፤ አሳደደ። ዛሬ የተያያዝነው ለውጥም የዚህ ልማዳችን ባሪያ ነው። አቶ ለማ መገርሳ ከወራት በፊት ለውጥማ አለ፤ ትናንት ለመክሰስ አይደለም ቀርበን ለማውራት የምንፈራቸውን ሰዎች እኮ ነው ዛሬ እስር ቤት ያስገባነው ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሥልጣን የያዙበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ የቀድሞ አመራሮችን ማሰርን ስኬት አድርገው ነግረውናል። የጀግንነት ፖለቲካ ልማድ የሰፌድ ላይ ሩጫችን አንድ አካል ነው ።

ዶናልድ ሌቨን ባለፈው ግማሽ ምዕተ አመት የጨነገፉ ዕድሎችን ሲያስተውሱ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ያነሳሉ። ኢትዮጵያ በዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ ወሳኝ ቦታ ላይ የምትገኝ አገር ናት። በዚህ የተነሳም የተለያዩ አገራት የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ጉዳያቸው ያደርጋሉ። በታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ አገላለጽ የ1953 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲደረግ ከጀርባ የነበረችው አሜሪካ አሁንም አራት ኪሎ የሚገባው ሰው ያሳስባታል። ታሪካዊ ባላንጣ የምትባለው ግብጽ የአዲስ አበባ ፖለቲካ ያስጨንቃታል። የመካከለኛ ምሥራቅ አገራት የኢትዮጵያ ልብ ትርታ በእነሱ ውስጥ የሚያልፈውን ደም ይረጭ ይመስል ያሳስባቸዋል።

አሌክስ ዳዋል ከዓመታት በፊት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ ጋር ባደረገው ቆይታ አንድ ጥያቄ አንስቶ ነበር። ‘ምን ያስፈራዎታል?’ የሚል። መለስ አፍታም ሳይወስዱ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ሥጋት አረቦቹ ከግብጽ ጋር ማበር ከጀመሩ ነው” ይላሉ። በዚህ ሳያበቁም “ታሪካዊ ባላንጣችን ግብጽ ዶላር ካላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ከተጎዳኘች የአገራችን ፖለቲካ አደገኛ አዝማሚያ ይኖረዋል” ሲሉ ይደመጣሉ። የመለስ ፍርሐት ዛሬ ወደ እውነታ ተቀይሯል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲቆም የምትፈልገው ካይሮ በአቡዳቢ በኩል እጅ ለመጠምዘዝ ደፋ ቀና ማለቱን ተያይዘዋለች። ፋይናንሽያል ታይምስ ከወራት በፊት እንዳስነበበውም የጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ ወዳጅ የሆኑት የተባበሩት አረብ ኤምሬትሱ አልጋወራሽ ቤን ዛይድ በሕዳሴ ግድቡ ላይ ኢትዮጵያ የያዘቸው አቋም እንዲለዝብ አድርገዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በግብፅና በአረቡ ዓለም ዕርዳታ የሚደረግላቸው የፖለቲካ አክቲቪስቶች የአራት ኪሎን ፖለቲካ እንዳሻቸው ፈንጭተውበታል። ይህ ደግሞ በቀደመው ዘመን የለውጥ ውጥናችንን የነጠቀን የውጭ ጣልቃ ገብነት አሁንም የምንጋፈጠው እውነት መሆኑን ያሳያል።

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የመደመር ፖለቲካ ከታሪክ አንፃር ከተመለከትነው የክሽፈት አዙሪት ውስጥ መውደቁን እንገነዘባለን። ይሁን እንጅ ከላይ እንደጠቀስነው ዐቢይ መራሹ መንግሥት በትናንት ብቻ የተተበተበ ሳይሆን የራሱ መልክም ያለው ነው። እንዲህ ያለው እውነት ደግሞ የታሪክ ድሪቶውን ጥሎ በአሁናዊ ጉዳዮች ላይ ተመሥርቶ ወደፊት የመራመድ ዕድል ይኖረው ይሆን?

ከክሽፈት አዙሪታችን ማዶ
የኢትየጵያ ፖለቲካ ወቅታዊ ሁኔታ በተሐድሶና ሽግግር መካከል የሚዋልል መሆኑን ቀድመን ተመልክተናል። የእነዚህ ኹለት ቃላት ድንበር ጥሶ መዋሐድም በአገራችን ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለየ አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ይመስላል። ተሐድሷዊ ሽግግር ብለን የጠቀስነው ይህ የመደመር ፍልስፍና ለዘመናት ሕዝቡ ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን የመመለስ ግብ አንግቧል።የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ እንዳለ ከተዋስንም እሳቸው የሚመሩት መንግሥት አሸጋጋሪ ሁኗል – ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚወስድ፣ ካለፉት 27 ዓመታት የጨለማ ዘመን ብርሃን ደጃፍ የሚያደርስ። ይሁን እንጅ አሸጋጋሪ ስርዓት ሁሌም ግቡን ሊመታ አይችልም። ኢታን ኬፒስቲንና ናታን ኮንቨርስ “ለምን የዴሞክራሲ ሽግግር ስኬት ራቀው?” በሚለው ጽሑፋቸው ባለፉት ጥቂት ዓመትት 56 ያህል አገራት ዴሞክራሲን ተመኝተው ጉዞ ቢጀምሩም ስኬት ግን እንደራቃቸው ያብራራሉ።

ይህ ለምን ሆነ የሚለውን ሲመልሱም ሦስት ነገሮችን ይጠቅሳሉ። የመጀመሪያው ምክንያት ዳዴ የሚል ዴሞክራሲን ለማፅናት የሚጥሩ መሪዎች የሚገጥማቸው የሕዝባዊ ቅቡልነት ችግር ነው። በበርካታ አገራት አምባገነናዊ ስርዓቶች ከወደቁ በኋላ ብሔራዊ መግባባት ይርቃቸዋል። የየራስ ጀግና በመፍጠር ለሥልጣን የሚደረገው ትግል ይፋፋማል። ዐቢይ አሕመድ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከዚህ ዓይነቱ ችግር ያመለጠ ቢመስልም በጊዜ ሒደት ሕዝባዊ ቅቡልነቱ እየተናጋ ሔዷል። ከሥልጣን አነሰን ጀምሮ የአዲስ አበባን ጉዳይ ያነገቡ ኃይሎች የመደመር ፖለቲካውን ጥላ እንዲያጠላበት አድርገውታል። ይህም በነገው መንገዳችን ላይ ሥጋት ያጭራል።

ሌላው ምክንያት የተቋማት ደካማ መሆን ነው። ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን ለመመሥረት ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ይህ ግን በአጭር ጊዜ እውን የሚሆን አይደለም። በመሆኑም በተለያዩ አገራት ተስፋ የተጣለበት ለውጥ እንደ ጉም ይተናል። ያለፈው መጋቢት የተጀመረው የአገራችን የፖለቲካ ለውጥ በዚህ መለኪያም ከታየ እጅጉን ወደኋላ የቀረ ነው። የመደመር ፖለቲካ አቀንቃኞች ላይ በስፋት የሚቀርበው ትችትም ለውጡን ተቋማዊ ማድረግ አልቻሉም የሚል ነው። አሁንም በበርካታ የአገሪቱ አከባቢዎች ያለው የመልካም አስተዳደር መጓደል አልተቀረፈም። ዛሬም ለውጡ ቀበሌ ደጃፍ አልደረሰም። ይህ መሆኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ አየር ላይ ያለ እንዲሆን አድርጎታል።

ኬፒስቲንና ኮንቨርስ ከምንም በላይ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ሊቀለበስ የሚችልበት ትልቁ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ። ከተራ የዋጋ ግሽበት አንስቶ እስከ ሥራ አጥ ቁጥር ማሻቀብ የሚደርሰው የኢኮኖሚ ጉዳይ የአገራትን የዴሞክራሲ ተስፋ በተደጋጋሚ ሲነጥቅ ተስተውሏል። ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መራሹ መንግሥት ከዚህ አንፃርም አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስላል። በየዓመቱ ኹለት ሚሊዮን ሥራ አጥ የሚፈጠርባት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ቁልቁል እየተንደረደረ ነው። የዓለም ባንክ እንደተነበየውም ባለ ኹለት አሐዝ ዕደገቷ ተገትቶ ወደ 7.7 አሽቆልቁላለች። የውጭ ንግዱ መቀዛቀዝና የምንዛሬ ጥረቱም ከአገራዊ ዕዳዋ ጋር ተዳምሮ ጣሯን አብዝቶታል።

ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ከምንም ነገር በላይ እነዚህን ሦስት ጉዳዮች ማረም ያስፈልጋል። ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መራሹ መንግሥት ሕዝባዊ ቅቡልነቱን ተመልሶ መቆናጠጥ፣ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ስኬትን ማስመዝገብ ካልቻለ የከሽፈት አዙሪታች ቀጣይነት ሳይታለም የተፈታ ይሆናል። አገራችን ዛሬ የተያያዘችው የለውጥ ጉዞ ከታሪክ መማር ያልቻለ ነው። ትናንት ተፈትነው በወደቁበት መሥመር ዛሬም አዲስ ነገር ሳይጨምሩ ለመጓዝ መሞክር ትርፉ ድካም ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ልኂቁ ካለመተማመን ወደ መቀራረብ፣ ከመገፋፋት ወደ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። ሥልጣን የያዘው ኃይል ከጀግንነት አስተሳስብ ካልመነነ፣ አራት ኪሎም ከውጭ ጣልቃ ገብነት ካልተፋታች የመደመር ፖለቲካ ወደቡ ትርጉም አልባ ነው።

12 ወራት የቀዘፈው የለውጥ ጅምር ዛሬ ከከባድ ማዕበል ጋር መጋፈጥ ጀምሯል። በክልል ድንበሮች ይወዛገብ የነበረ ሕዝብ አሁን ከዛም ወርዶ በኮንዶሚንየም ባለቤትነት አተከካራ ውስጥ ገብቷል። በየቦታው ያለው መፈናቀ በሕመም ላይ ሕመም ሆኗል። የፖለቲካ ንግድ በብሔርተኝነት ሰረገላ በየቦታው ገኗል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የዳር አገሩን ፖለቲካ ያገለለው የአራት ኪሎ ግብግብ አገር ጤና ነስቷል። ኢትዮጵያዊነት በጥቂት ብሔሮች ጥላ ሥር ወድቋል። የአንድ የባስኬቶ ተወላጅ መፈናቀልና ሞት ለሌላው ኢትዮጵያዊ ትርጉም ካልሰጠ የአገር ፍቅራችንን መለኪያ ዋጋ ያሳጣዋል።

ወቅታዊው የመደመር ጉዞ ከምንም ነገር በላይ ግን በድኅረ-እውናዊ ፖለቲካ (post truth politics) የሚፈተን ነው። አዕላፍ ወጣቶችን የፌስቡክ ወታደር ያደረጉ አዝማቾች እዚህም እዛም መንግሥትን መገዳደር ቀጥለዋል። የክልሎች ፖለቲካ በማኅበራዊ ድረገጾች መመራት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የክሽፈት ታሪክ ለመላቀቅ ከፈለግን እነዚህን ነገሮች ፈር ማስያዝ ይኖርብናል። ያ ካልሆነ ግን ከመገጋቢት እስከ መጋቢት የተሸከምነውን መፈክር ይዘን ቀኝ ኋላ ልንዞር እንችላለን። ወደኋላ መዞራችን ታዲየ የትናንትን ሕይወት ልንመልስ ሳይሆን የከፋውን ልናዋልድ እንደሆነ አያጠራጥርም። አምስት ደጃፍ የረገጠው የክሽፈት ታሪካችን ዛሬ ስድስተኛው ተብትቦ ይዞታል። ትግሉ ከዚህ ጋር ነው። ትናንትን ረቶ ነግን መሥራት!

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here