የኢትዮጵያ ታሪክ ሲባል ምን ማለት ነው? ዕድሜውስ ስንት ነው?

0
623

የኢትዮጵያ የታሪክ አረዳድ ከዘመን ርዝመት እንዲሁም ከትኩረት አቅጣጫ አንጻር ብዙ አጨቃጫቂ ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቀሱት መላኩ አዳል፥ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በሚያግባባ መልኩና ከታሪክ ሽሚያ ተወጥቶ መጻፍ እንዳለበት በማሳሰብ መፍትሔ ይሆናል ያሉትንም ምክረ ሐሳቦች በጽሑፋቸው ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ታሪክ ማለት ከመጀመሪያው እስካለንበት ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ የትም ቦታ የከወነው፤ የእኔ ወይም እንደ አገር የእኛ ብለን የምንቀበልውና ዕውቅና የምንሰጠው የትናንት መጥፎም ጥሩም የተግባር ክንውን ድምር መዝገብ ነው። ነገር ግን ሁሉም የአገሪቱ ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ የሠራው ታሪክ የለም፣ ሊኖርም አይችልም።

የኢትዮጵያ ታሪክ የተለያዩ ጽንፎች ከ100-5000 ዓመታት ያደርሱታል። አንዳንዶች ከኖህ፣ አንዳንዶች ናፓታ/መርዌ፣ አንዳንዶች ከሳባ፤ አንዳንዶች ከዛገዌ፤ አንዳንዶች ከዩክኖ-አምላክ፣ አንዳንዶች ከልብነ-ድንግል፤ አንዳንዶች ከኦሮሞ ፍልሰት፣ አንዳንዶች ከሚኒሊክ የታሪካችን መነሻ አድርገው ሲጽፉ እያየን ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙው አልተፃፈም፣ የተፃፈው በተለያዩ የዘመን ክስተቶች ወድሟል፣ የመሪዎች እንጂ ከሕዝብ አንፃር አልተፃፈም፣ የመሪዎችም ቢሆን ፖለቲካ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ የጎሳ መነፅር ሲጠለቅ የተፈጠረው ችግር ብዙ ሆነ። ለሚቀጥለው ትውልድ የምናቀብለው ታሪክና የታሪክ ቅርፅ አሳሳቢ ነው። የታሪካችንን መነሻ ማወቅ ለጥሩ የታሪካችን መድረሻ ግብዓት ነውና ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋላችን ትተን ለሩቁ በጎ ዓላማ የምንጠቀምበት፣ ታሪካችን በባለሙያዎች ተመርቶ ለሁሉም በሚያግባባ መልኩ የሚዘጋጀው መቼ ይሆን? በአንድ አገር እየኖርንና በአንድ መንግሥት እየተዳደርን፣ ነገር ግን የራሳችን ትርክቶች ይዘን በተለያየ አገር እንደሚኖሩ የማይተዋወቁ ሕዝቦች እየሆንን ነው።

የአማራው ልኂቅ ደሜን አፍስሸ፣ አጥንቴን ከስክሼ በሠራሁት አገር የሚገባኝን ዕውቅና አላገኘሁም፤ እንዲያውም ለአገሬ ያበረከትኩት በጎ ነገር ወደ ጎን ተትቶ፣ ነፍጠኛና ትምክህተኝ እየተባልኩ፣ ከሕገ መንግሥት ማርቀቅ ተገልዬ፣ ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦች በእስር ቤት እንዲማቅቁና እንዲሞቱ ተደርጓል። ሌሎችም በየምክንያቱ በዋሉበት ቀርተዋል። አሁን ያለው የክልል አከላለልም ቢሆን የወሰኖችን አካባቢ ሕዝብ በጎ ፈቃድ ያላገናዘበ፣ የአማራን ሕዝብ ብዝኀነትና ብዛት ለመቀነስ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ይላል። ለዚህ ደግሞ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆቹ ሕውሓትና ኦነግ እጅ አለበት ይላል።

የትግሬው ልኂቅ ደግሞ የታላቋ አገር ሥልጣኔና ምሥረታ መሰረት ብንሆንም፤ ለብዙ ዘመናት ከሥልጣንና ተያያዥ ጥቅሞች በሸዋ ነገሥታት እንድንርቅ ተደርገናል። እንዲያውም በሸዋ ነገሥታት ተንኮል እኛን ለማዳከም ትግራይና ኤርትራ ተብለን እንድንከፈል ሁነናል። ስለዚህም አማራ ጠላቴ ነው። በምችለው ሁሉ ወደ ሥልጣን እንዳይመጣና ተሳታፊ እንዳይሆን ጥረናል። ፓርቲ መስርቶ እንዳይንቀሳቀስ የራሳችን ሰዎች አስርገን በማስገባትና ነፃ ባልሆነው ምርጫ ቦርድ ተጠቅምን አፍርሰነዋል ይላሉ። ይህም ማለት በዚሁ ማኅበረሰብ አካላት የሚቀነቀነው ጠላትነት ከገዥነት ፉክክር ጋር የሚያያዝ ነው። በተጨማሪም ያኔ ጣሊያን አማራው ለአገሩ ቀናኢ ሆኖ በታላቅ የአርበኝነተ ተጋድሎ ሲመክተው አማራውን ማጥላላት፣ ማስጠላት ጀመረ፣ ሌሎችን በተለይ የተወሰኑ ትግሬዎችን በባንዳነት መልምሎ በአማራው ላይ እንዲዘምቱ አደረገ። ስለዚህ ከትገሬው ማኅበረሰብ መሃል ለአማራው ጠላት የሆነ የልሂኂቃን ቡድን ተፈጠረ። ከጣሊያን ወረራ ጋር ታሪኩ የሚያያዘው የኤርትራ ጉዳይም ኢትዮጵያን እንደ ቅኝ ገዥ አስቆጠረ፣ ይህኛው አስተሳሳብ በኦሮሞው በኩልም ከአፄ ምንሊክ አገርን የማረጋጋት እርምጃ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ ይንፀባረቃል።

የ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ከአሕመድ ግራኝ የጦርነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ መዳከሟን ተከትሎ የተከሰተው የኦሮሞ ተስፋፊነት አፄ ምንሊክን መልሶ በተስፋፊነትና ጨፍጫፊነት ይከሳል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ግዛት እንደ መሪው ጠንካራነትና ደካማነት ሲሰፋም ሲጠብም የነበረ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያን ታሪክን ከ16 ክፍለ ዘመን በመጀመር፣ አንዳንዶቹ የአፄ ሚኒሊክ የአገር ምስረታውን እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን የብሔረ ምስረታው በእኩልነትና አሳታፊነት ባለመካሔዱ ተጨቁነናል፣ ተበድለናል፣ የሚገባንን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ አላገኝንም ሲሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ የአፄ ሚኒሊክ አገር ምስረታ የቀኝ ግዛት ጉዳይ ነው፣ ለዚህም ማስረጃ የሌለው የሞተ ሰው ቁጥርና የጡት መቁረጥ ሃውልት አቁመዋል። የሚገባንን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ አላገኝንም ይላሉ። የኦሮሞውን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ይክዳሉ፤ ወይም እኛን አይወክልም ይላሉ።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት የተሠሩ ስህተቶች፡-
1/ የተሳሳተ ርእዮትና ጠላትነት፥ ሳይንሳዊ ያልሆነና የኢትጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ሶሻሊስታዊ ርዕዮት፣ እሱንም ተከትሎ የመጣው የብሔር ሕገ መንግሥቱና ፌዴራሊዝም ስርዓቱ፤ በእኛና እነሱ ፖለቲካ፣ የብሔር ጭቆና ነበር ትርክት፣ አማራን በጠላትነት የመፈረጅ ሒደት ተጠናከሮ መተግበሩ አንድ ትልቅ ስህተት ነበር። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እሥር ቤት፣ አማራ ጨቋኝ፣ ገዥ መደብ፣ ቅኝ ገዥ፣ ጠቅላይ አግላይ፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ ወዘተ ተባለ። አሁንም አማራ የጠቅላይ አንድነት ስርዓት ሊያመጣብህ ነዉ፣ አኀዳዊ ስርዓት ሊያመጣብህ ነዉ፣ በአንድነት ሥም ሊጨፈልቅህ ነዉ፤ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባሕል፣ አንድ ሃይማኖት ሊጭንብህ ይፈልጋል፤ ጠቅላይ አግላይ ነዉ፤ ፌዴራላዊ ስርዓት አይፈልግም የሚሉ የሐሰት ትርክቶች ይተርካሉ።

2/ የሐሰት የታሪከ ትርክት፥ የጠባብ ብሔርተኞች የታሪክ ትርክት ታሪክን መፍጠር ላይ የተንጠለጠለ ነው። ፖለቲከኛ የታሪክ ፀሐፊዎች የጎሳ መነፅራቸውን አጥልቀው የተፃፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ ማየትና ለእነሱ ጠባብ የጎሳ ፖለቲካ የማይሆነውን የደብተራ ታሪክ ነው ማለት ጀመሩ። የጎሳ ፖለቲከኞች አደገኛና ቀስቃሽ አሉባልታ በታሪክ ድርሰቶች ለተከታዮቻቸው ሰብከዋል። በዚህም የአገሪቱ ታሪክ በእጅጉ ተፋልሷል።

3/ የጋራ ጥሩ እሴቶችን መናድ፥ መለስ ዜናዊ “አክሱም ኃውልት ለወላይታው ምኑ ነው” ብሎናል። የኢትዮጵያ እናቶች ጥጥ ዳምጠውና አሳስተው የሚሠሩትን የሸማ ጥበብ ነፍጠኛው በሌላው ላይ የጫነው ነው ተብለናል። ቋንቋ ከመግባቢያ መሣሪያነት አልፎ ደም ነው የሚል ሰው ተፈጥሯል። እንደ ኢትዮጵያዊነት፣ የኢትዮጵያን ዳር ደንበር መጠበቅና ማስከበር፣ ሀገር ወዳድነት፣ ሀገራዊ እይታ፣ ባለታሪክነት፣ ኩራት፣ ሀገራዊ ድል፣ የአማርኛ ቋንቋ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንድነት፣ ሀገርና ህዝብ አፍቃሪነት፣ ጀግንነት፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ እኛነት፣ ፍትህ አዋቂነት፣ ነፃ ህዝብነት፣ ህግ አክባሪነት፣ መንግስትንና መሪን ማመን፣ አስተዳደር አዋቂነት፣ ባሕል አከባሪነት፣ እንግዳ አክባሪነትና ተቀባይነት፣ ሃይማኖተኛነት ያሉ ጠንካራ የማኅበረሰብ እሴቶችን መናድና እንደ ማጥቂያ መጠቀም ታይቷል።

4/ የምሁራን ተሳትፎ መቀነስ፥ የሕዝባቸዉን ውለታና አደራ መርሳት፤ በሚሰሙትና በሚተገበረዉ መካካል ያለዉን ልዩነትና አንድነት ያለማስተዋል፤ ምኞትንና እውነታን መደባለቅ፣ በሐሳብ ላይ ብቻ መንጠልጠልና እዉነታን አለማየት፤ ከነባራዊ ሁኔታ መራቅ፤ የሌሎችን አስተሳሰብ፣ እይታና አቋም አለማወቅ፤ ነገሮችን ከጊዜ ከቦታና ሁኔታ አንጻር በአግባቡ አለመመዘን፤ ምሁራዊ ቁሞ ቀርነት፤ የፖለቲካ ዓላማ፣ ግብ፣ ስትራቴጅና ታክቲክ አለመለየትና መቀላቀል፤ መልካም አጋጣሚዎችንና አደጋዎችን አለመለየትና በአግባቡ አለማስተናገድ፤ ቸልተኝነት፣ ግድ የለሽነት፣ ራስ ወዳድነት፣ አድር ባይነትና አጎብዳጅነት የመሳሰሉት ተስተውለዋል።

የተጠቆሙ መፍትሔዎች፦
1) የአገራችን የታሪክ ተመራማሪዎች ʻበእኔ እበልጥ፥ በእኔ እበልጥʼ በተቃርኖ ውስጥ ሆነው እያቃረኑን ነውና እነሱን ሳይንሳዊ በሆነ መስመር ላይ መቃኘት ያስፈልጋል፤

2) የታሪክ ምሁራኖቻችን የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል ወጥ የሆነ ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ የጋራ ሳይንሳዊ የታሪክ ጥናት ዘርፍ መመስረት ያስፈልጋል፣

3) ምሁራንን በማሰባሰብ መድረክ መፍቀድ/ማመቻቸት፣ የሚያስፈልገው የኢኮኖሚና ቁሳቁስ ድጋፍ መስጠት፣ ብሎም የታሪክ ዝግጅቱን በነፃነት ለባለሙያዎቹ መተውና የውጭ ተፅዕኖ ማስወገድ፣

4) የታሪክ ተመራማሪዎች የቋንቋ ጥናት፣ የአርኪዎሎጂ ምርምር፣ የጆኦግራፊዊ ጥናቶችን መሰረት ያደረጉ ወጥ የታሪክ መረጃዎችን እንዲቀርቡ ማደረግ፤ ይህም ታሪክን ለማጥራት ይጠቅማል፣

5) የታሪክ አታያይና አረዳዳችንን የሚቃኙ ወጥ የሆነ የጋራ ግንዛቤ በትምህርት ማዕከሎቻችን እዲሰጥ ማድረግ፣ በተለይም የታሪክ ትምህርት እንደዋና ትምህርት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ መስጠት፣

6) ታሪካችን አሁን እንደሚጣፈው የፖለቲካ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የማኅበራዊ ታሪኮቻችን ያካተተ እንዲሆን ማድረግ፣ ይህም የሕዝብ ታሪከ ወደ መሆን ሊያደርሰው ስለሚችል ተቀባይነቱን ይጨምራ፤

7) የእኛ ዜጎች ግዴታ ደግሞ አገራችንን ያለታሪክ ፍርድ ሳንናቆር በጋራ የራሳችንን ታሪክ መኖር ነው።

ማጠቃልያ
የተባልው ሁሉ የሚያሳየን የጋራ የሆነ ርዕዮተ ዓለም እንዲኖረን እንዳልሥራን፣ ማኅበራዊ በሆነው ትስስርና የብሃረ-ምስረታው እንዳልገፋን፣ የታሪክና የጥቅም ሽሚያው ላይ ሁሉንም ኃይላችን እያዋልንው መሆኑንና የትናንቱ መጥፎ ታሪክ ለነገ እንዲተላለፍ እያደረግን መሆናችንን ነው። ስለዚህ ይህ ትውልድ፣ ታሪክም ልማትም አገርም ሕዝብም የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት እንጂ በአንድ ጀምበር የተፈጠረ ባለመሆኑ ትላንትና ዛሬን አስታርቀን የጎደለውን ሞልተን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት በእጃችን ነው። ስለዚህም ከታሪክና ሥልጣን ሽሚያው ወጥተን፤ አገራዊ ነፃ ተቋማትን ገንብተን፤ በጠራ ርዕዮተ ዓለም ብቻ የምትመራ የሁላችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ። ለዚህም ግፊት እናድርግ፤ አሊያ ግን በጊዜያዊ ጉልበት ብቻ ሥልጣን የሚያዝባት፣ የተወሰነ ቡድን የሚጠቀምባት እና ብዙኀኑ የሚጎዳባት ኢትዮጵያ እንዳትሆን አሁንም እሰጋለሁ።

መላኩ አዳል የዶክትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በመሥራት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here