ከአውሮፕላን አደጋው ባሻገር

0
491

መጋቢት 1/2011 ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ በመነሳት 149 መንገደኞችንና 8 የአየር መንገዱን ሠራተኞች አሳፍሮ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው ቦይንግ 737-ማክስ 8 አውሮፕላን ከተነሳ ከስድስት ደቂቃ በኋላ መከስከሱ ይታወሳል። የአውሮፕላኑን አብራሪ፣ ረዳቱና ሌሎች ሠረተኞችን እንዲሁም ተጓዦችን ጨምሮ 157 ሰዎች በሙሉ የአደጋው ሰለባ ሆነዋል። የአውሮፕላኑን መከስከስ ተከትሎ ዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኀን በርካታ የዜና ሽፋን ሰጥተው ብዙ አዳዲስ መረጃዎችን ለዓለም አድርሰዋል። ከዚህም ባለፈ ታዋቂ ግለሰቦች ሐዘናቸውንና ለአውሮፕላን አምራቹ ኩባንያ ቦይንግ ደግሞ በተመሳሳይ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። ለዚህ ደግሞ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። ፕሬዘዳንቱ በትዊተር ገፃቸው “አዳዲስ የሚመረቱት አውሮፕላኖች ከመዘመነቻው የተነሳ መደበኛ አብራሪዎች ሳይሆኑ ከማሳቹሴት የቴክኖሎጂ ተቋም የተመረቁ ተማሪዎች ናቸው ማብረር የሚኖርባቸው” የሚል እና የኩባንያውን ሥም የመጠበቅ ቅድመ ሁኔታ ተስተውሏል።

ከ8 ከወራት በፊት የኢንዶኔዥያ ላይን ኤር ንብረት የሆነው እና ሁሉም ተሳፋሪዎቹ ያለቁበት አውሮፕላን ጋር ከኢትዮጵያው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ በጊዜው ከአስደንጋጭ የአውሮፕላን አደጋነቱ እና የ189 ሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፉ በዘለለ ጣት መቀሳሰሩ አልነበረም፤ ሌሎች አገራትም በአውሮፕላኑ ላይ ጥርጣሬ አልነበራቸውም ነበር። መጋቢት 1 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት ላይ በደረሰው አደጋ ግን የአውሮፕላኑን ጤናማነት ወደ መጠራጠር፣ ወደ አምራች ኩባንያው ቦይንግ ጣት ቅሰራው ተበራከተ፤ በርካታ የዓለም አገራት የነበሯቸውን 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ አደረጉ። ለእነዚህ እርምጃዎች ግንባር ቀደሟ ቻይና ነበረች። ቻይና 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በገፍ ካሏቸው አገራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ አገር ናት። ነገር ግን ከበረራ ውጭ ከማድረግም ባለፈ “የየትኛውም አገር ንብረት ሆነ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የአየር ክልሌን ከጣሰ መትቼ እጥለዋለሁ” የሚል ቆምጨጭ ያለ ውሳኔዋን ለዓለም ይፋ አደረገች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተፅዕኖ ፈጣሪነት
“በአየር መንገዱ ታሪክ በአብራሪዎች ስህተት የደረሰ አደጋን እኔ አስከማስታውሰው ድረስ የለም በዚህም ምክንያት ተፅዕኖ ፈጣሪ ቢሆን አይገርምም” የሚሉት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረጅም ዓመታት በአብራሪነትና በአሰልጣኝነት ያገለገሉት ካፒቴን አማረ ገብረሐና ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት በብቃት አሰልጥኖ ወደ ሥራ የሚያሠማራቸው አብራሪዎቹ እና የጥገና ባለሙያዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መልካም ሥሙን እንዲተክልና ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ኩራት መሆኑን ይናገራሉ። ካፒቴን አማረ እንደሚሉት ከሆነ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረረ መንገደኛን፥ ʻምርጫው ለምን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሆነ ብትጠይቀውʼ፥ ከአብራሪዎች ችሎታ ጋር የተያያዘ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል በማለት ያስረዳሉ። እያንዳንዱ በአየር መንገዱ የሚጠቀም መንገደኛ ወደ አራቱም የዓለም አቅጣጫ ሲጓዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወኪል ወይም አምባሳደር እስኪሆኑ ድረስ ነው በአየር መንገዱ የሚተማመኑት፤ ይህ ደግሞ አየር መንገዱ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ያጎላዋል ይላሉ ካፒቴኑ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታሪኩ ካጋጠሙት አደጋዎች በተቃራኒው በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት የቻለ እና በየጊዜው ዓለም ዐቀፍ መዳረሻዎቹን እያሳደገ መምጣቱ ለተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም ይላሉ ካፒቴኑ። የካፒቴን አማረን አስተያየት የሚያጠናክርልን ደግሞ የመጋቢት 1/2011 አደጋውን ተከትሎ ሁሉም የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተጠቃሚ አገራት ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፋቸው ነው። ከዚህም በመነሳት ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ 8 ላይ ያለውን ምርት እንዲቀንስ ሆኗል።

መጀመሪያ ላይ አውሮፕላኖቻችን እጅግ የተራቀቁ እና ባለምጡቅ አእምሮ ብቻ ነው ሊያበራቸው የሚገባው ሲሉ የቆዩት ፕሬዘዳንት ትራምፕ ወደ መለሳለስ ገቡ። በርካታ ማስተባበያዎችን በማውጣት ቦይንግ ከደሙ ንፁህ ነኝ ሲል ቢቆይም የኋላ ኋላ ግን በይፋ ጥፋቱን በማመን ይቅርታ ጠይቋል። ቦይንግ ይቅርታውን በአደባባይ ይጠይቅ እንጂ የተሔደበት መንገድ ቀላል አልነበረም። ኢቲ 737 ማክስ 8 ከተከሰከሰ በቀጣይ ቀናት ውስጥ የመረጃ ሳጥኑ ላይ ምርመራ ለማድረግ ከቦይንግ ኩባንያ ባለሙያዎች አዲስ አበባ ገብተው ነበር። ይህም በዓለም ዐቀፍ የአቪየሽን ሕግ መሰረት አንድ አውሮፕላን አደጋ ሲደርስበት፥ የአውሮፕላኑ ባለቤት አገር፣ አምራች ኩባንያው እና አደጋው የተከሰተበት አገር በጋራ የሚሰሩበት አግባብ መኖሩን ተከትሎ ነው። ከቦይንግ ኩባንያ ተወክለው ከመጡት ባለሙያዎች የመረጃ ሳጥኑን ወደ አገረ አሜሪካ ወስደው መረጃውን የመመርመርና የአደጋውን መንስኤ የመለየት ሥራ እንዲሠራ ሐሳባቸውን አቅርበው ነበር። በተደረገው ድርድር ወደ ፈረንሳይ አገር እንዲወሰድና የመረጃ ምርመራ ጥናቱም በዛው እንዲጠና ተደርጓል።

የመረጃ ሳጥኑ ምርመራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ መረጃውን ይፋ ለማድረግ የአንድ ዓመት ጊዜ እንደሚፈጅ የሚታወቅ ቢሆንም መጋቢት 27/2011 በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ሆኗል። በዚህም ሪፖርት ላይ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በረራውን ማካሔድ የሚያስችል ብቃት ላይ እንደነበሩ እና በተደጋጋሚ የአሰራር ቅደም ተከተሎችን መከተላቸው ይፋ ተደርጓል። በዚሁ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ʻሲስተምʼ በአምራች ኩባንያው እንደገና ማሻሻያ እንዲደረግበት ተጠቁሟል።

የምሕንድስና ስህተት ወይስ ግዴለሽ?
ከመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያ የቦይንግ ኩባንያን መግለጫ ምንም ፋይዳ የሌለው ነገር ነው ሲል ይጀምራል። አውሮፕላኑ የተሰራበት የፋይበር መሳሪያ ቀላል ቢሆንም የሞተሩ ጉልበት ግን በብረት ለተሰራ አውሮፕላን የሚሆን ከፍተኛ ጉልበት አለው። ሲል ሙያዊ ትንታኔውን ይሰጣል ። ቀጥሎም ባለሙያው ሲናገር በሞተሩ ጉልበት እና በአውሮፕላኑ የአካል ክብደት አለመመጣጠን የተነሳ ከምድር በሚለቅበት ወቅት ጤናማ ያልሆነ ፍጥነት ወይም ከመደበኛው ፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ነው። በዚህም የተነሳ አውሮፕላኑን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አዳጋች ያደርገዋል። ባለሙያው ይህን ብሎ ቦይንግ እንደዚህ አይነት ቀላል የምሕንድስና ስህተት ይሰራል ብሎ እንደማያምንና ከግዴለሽነት እንደሚመድበው ያስረዳል።

የቦይንግ መፃኢ ዕድል
የግዙፉ ቦይንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሜሊንበርግ በሲኤንኤን ቢዝነስ ዘጋቢ መርሃ ግብር ላይ ቀርበው ኩባንያው በወር 52 ቦይንግ 737 ማክስ 8 ያመርት እንደነበር አውስተው፥ በቅርቡ በኢትዮጵያ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በጊዜያዊነት በወር 44 ቦይንግ 737 ማክስ 8 ወደ ማምረት ዝቅ እንዳለ ተናግረዋል።

ቦይንግ ኩባንያ በአራት ወራት ውስጥ ኹለት አሰቃቂ አደጋዎች በተመመሳሳይ ምርቶቹ መድረሱን ተከትሎ በድምሩ ለ346 ሰዎች ኅልፈት ተጠያቂ መሆኑ ተረጋግጧል። በዚህ ብቻ ሳያበቃ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖችን ከበረራ ውጪ ላደረጉ አገራት ካሳ መክፈል እንደሚኖርበትም ካፒቴን አማረ ይናገራሉ። እንደምክንያት የሚያስቀምጡት ደግሞ ከበረራ ውጪ የሆኑት አውሮፕላኖች ከፍተኛ ጫና በሌሎች አውሮፕላኖች ላይ ከማሳደሩም በላይ ትልቅ መጨናነቅ በደንበኞች ላይ ይፈጥራል። ይህ ደግሞ አየር መንገዱ ለተገልጋዮቹ ለሚሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት መጓደልን ያስከትላል ብለዋል።
ቦይንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 የደረሰውን አደጋ ተከትሎ የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ትልቅ መቀዛቀዝ ደርሶበታል። ከዚህም በመነሳት የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች ለኪሳራ መዳረጋቸውን በርካታ የዜና አውታሮች እያራገቡት ይገኛሉ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ቦይንግ ኩባንያ በደረሱት ኹለት አደጋዎች ለደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት ካሳ እንደሚከፍልም ይጠበቃል። ይህ ደግሞ በኩባንያው ላይ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ጫና እንደሚያሳድርና ለማንሰራራትም ከባድ እንደሆነ የዘርፉ ሙሁራን ትንታኔ ይሰጣሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here