ብዙኀን መገናኛዎች የሁሉንም ድምፅ አካታች እንዲሆኑ

0
548

ብዙኀን መገናኛዎች ብዝኀነትን ማካተታቸው የሚረጋገጠው በሚያስተናግዱት የሐሳብ ብዝኀነትም እና በሥራ በሚያሳትፏቸው ሰዎች ነው የሚሉት ቤተልሔም ነጋሽ፣ ስለ ብዙኀን መገናኛዎች አካታች መኾን እና ሕዝቦቻቸውን መምሠል አስፈላጊነት የሚከተለውን ጽፈዋል።

 

 

“አንድ ነጻ ፕሬስ ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል። ነገርግን ያለነጻነት ፕሬሱ መጥፎ እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም” አልበርት ካሙ

“የሕዝብ የማወቅ መብት አደጋ ላይ ሲወድቅ እና ሐሳብን በነጻነት መግለጽና ነጻ ፕሬስ እንዲሁም ሌሎች መብቶች አደጋ ላይ ይወድቃሉ” ክርስቶፈር ዶድ ሐሳብን በነጻ የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት የነጻነት ሁሉ የመጀመሪያ ተብሎ ሲጠቀስ በተፈጥሮ የተሰጠ ማንም ሊነጥቀው የማይችለው መብት በማለትም ይሞካሻል። አራተኛው መንግሥት የሚባለው ሚዲያ ለሕዝብ ዘብ በመቆምና መንግሥት ለሕዝብ ያለበትን ተጠያቂነት እንዳይስት ይህንንም ረስቶ የሕዝብን ፍላጎት ያላማከለ ሒደት እና ድርጊት ውስጥ እንዳይገባ ቋሚ አስታዋሽ በመሆንም በተለይ ቀደም ባሉት የፕሬስ ዓለም ዐቀፍ ታሪክ የሚታወቅና የሚጠቀስ ነው። ቀደም ሲል ያልኩት መንግሥታት እና ካፒታሊዝም ባመጡበት ጣልቃ ገብነትና ሙስና ተይዞ ችግር የሌለበት በአንፃራዊ መልካም የሚባል እንጂ ወደ ፍፅምና የሚጠጋ ሚዲያ በዓለም ላይ የሌለ በመሆኑ ነው። ነገር ግን በየትኛውም ሁኔታ፣ ከነችግሮቹ ነጻ ፕሬስ የአንድ አገር እጅግ ጠቃሚ ተቋም ነው፡ ይህን ተቋም መጠበቅ የግድ ይላል።

በአገራችን ግን እንደአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ሁሉ ብዙኀን መገናኛዎች ነጻ ወጥተው አስተዋፅዖዋቸው እንዲበረክት ዕድል አልነበረውም። ሙሉ በሙሉ አያስፈልግም ብሎ የሶሻሊስት ፕሮፓጋንዳ ከሚያካሒድና የመንግሥት አፍ ከሆነ ሚዲያ በቀር እንዳይኖር ከተደረገበት ወደ አንፃራዊ ነጻነትና ቀጥሎም ጨርሶ ወደ የማያሠራ ከሕግ ማዕቀፍ በዚህም ምክንያት በጣት ከሚቆጠር ቁጥር እንደ አሸን እስከመፍላትና መልሶ ጥቂት እስከመሆን ድረስ የአገራችን ሚዲያ ብዙ አልፏል።

ቀረብ ወደሚለው ወቅት ስንመጣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ነውጥ ተከትሎ በተከሰተው የሥልጣን ለውጥና የመንግሥት አሠራር መቀየር መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ቀደም ባለው ስርዓት፣ መሪዎች ወይም የፖለቲካ ከባቢ ከደረሰባቸው ግፍ እስርና አፈና ነጻ ከወጡት መካከል ጋዜጠኞች በግለሰብ ደረጃ የፕሬስ ተቋማት ወይም ሚዲያ ይገኙበታል። በአንድ ወቅት በጋዜጠኞችና በአክቲቪስቶች እንዲሁም ሙያቸው ጋዜጠኝነትም ባይሆን በተለያየ ሚዲያ የመብት ጥያቄ ያነሱ ጦማርያንን በማሰር የምትታወቅ አገር ዛሬ “ማንም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት” ወደሚል የተሸጋገረቸውም በዚሁ ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በለውጥ ሥራ ላይ ቢሆኑም አገሪቱ መከተል የሚገባትን መንገድ በሚመለከት የጋራ ሥምምነት አለመኖሩ የሚደረጉትን ለውጦችና ፍጥነትና ጥራታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ እንደሚችል ይገለፃል። ይሄ ለሚዲያውም እውነት ይመስላል።

በአዎንታዊ ሒደቶችና በለውጡ ውስጥ ምናልባትም ባለው ወሳኝና የማይተካ ሚና ምክንያት ትኩረት ከተደረገባቸውና በአንዳንድ መልኩም ሰለባ ከሆኑት ተቋማት መካከል ሚዲያ አንዱ ነው። ሌሎች ምክንያቶችም ተጨምረው ኢ.ኤን.ኤን. የተሰኘውና ከገበያ ውጪ የሆነው የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ለምሳሌ አላስፈላጊ ትኩረትና ወቀሳ ውስጥ የገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወሳኝና ታሪካዊ ለውጥ እርምጃዎችንና እንቅስቃዎች በአግባቡ ባለመዘገቡ ምክንያት እንደሆነ እና ይህም ለመዘጋቱ እንደምክንያት ሲጠቀስ፥ በሌላ በኩል ሚዲያው የተዘጋው ከለውጡ በፊት በነበረው የመንግሥት ስርዓት ይመደብለት የነበረው በጀት በመቆሙ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል።

መንግሥት እንደሚያምነውና በሚዲያ ላይ የሚያደርገው እያንዳንዱ ገደብና ክልከላ እንዲሁም ክትትል እንደሚያሳየው የሚዲያን ጉልበት አይስተውም። ጉልበቱ ለመንግሥት ድጋፍ ከመሆን አልፎ በጠላትነት የሚፈረጅበትና እንደ አጋላጭና ከሳሽ የሚታይበት (ይህ የሚጠበቅ የሚዲያ ሚና ሆኖ ሳለ) በመንግሥትም ያለው ተቀባይነትና ድጋፍ በእነኝህ ሁኔታዎች ላይ የሚመሠረትበት ሁኔታ ብዙ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመጡ ወዲህ አዳዲስ ሚዲያዎች መከፈታቸው፣ ያሉትም ቢሆኑ ድሮ የመንግሥት አፈቀላጤ ሆነው ይሠሩ የነበሩት አገር ዐቀፍና የክልል ሚዲያዎች ሳይቀር በአንፃራዊነት የተሻለ ዘገባ ወደማቅረብና ብዝኀነት ያላቸውን ሐሳቦችና አመለካከቶች ወደማንፀባረቅ መሔዳቸው ተስፋ ሰጪ ጅምርና ለሚዲያው ደኅና ቀንና የተሻለ ጊዜ መምጣቱን የሚያመላክቱ ናቸው። ሆኖም ይህንኑ ተመልክቶ ሚዲያ ላይ ገደብ ሊጥል የሚችል የፀረ ጥላቻ ሕግ ተረቅቆ ሰሞኑን ለውይይት ቀርቧል። ይሄ ምናልባትም ገና በሥራ ላይ ያለውና በርካታ ችግሮች ያሉበት ሕግ ሳይሻሻልና ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሚያሠራ ሕግ ሳይወጣ መምጣቱ በሙያው ላይ ሥጋት የሚጥል ነው። ከዚህም ሌላ በይፋ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙያውና በሙያተኞች ላይ አንዱን የሚያሞካሽ ሌላውን የሚያጥላላ አስተያየት አልፎ አልፎም ቢሆን ሲሰነዘር መታየቱ ትንሽ መንግሥት ሙያውን በራሱ መንገድ ሔዶ የሚፈለግበትን ኃላፊነት ሙያው በሚጠይቀው ሥነ ምግባር ታግዞ እንዲወጣ አልተወውም ወይም አይተወውም የሚል ሐሳብ ማሳደሩ አይቀርም።

ብዙ ጊዜ መንግሥት በሚዲያው ሥራና ከባቢ ጋዜጠኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ እንቅፋት በመሆንና በጣልቃገብነት ሲጠቀስ፥ አንድ የሚመጣ የመከላከያ መልስ ጋዜጠኞች ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ ወገንተኛ፣ የራሳቸውን ሐሳብና ፍላጎት ለማንፀባረቅ ብለው ሚዲያ ከፍተው የሚሠሩ መሆናቸው ነው። ይሄ በተወሰነ መልኩ እውነትነት ያለው ሐሳብ መሆኑን ጠቅሼ በግሌ ሚዲያ ከሚወቀስባቸው ነጥቦች አንዱ የሆነውን የውክልና ጉዳይ አንስቼ ጽሑፌን አበቃለሁ።

በሚዲያ ጉልበትና የሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ ጥናት ካደረጉ ዓለም አቀፍ ተጠቃሸ ምሁራን አንዲ ኪያራን ማክኩላን በሚዲያ የምናያቸው ምሥሎችና ትዕምርታዊ ምልክቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላላቸው ተፅዕኖ ሲጠቅስ፦ “ማኅበራዊ እውነታን በሚመለከት ያለን ሥዕልና ዕውቀት የሚገነባው ሚዲያ በሚያሳየን ምሥልና መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው። ሚዲያ የሚያሳየን ምሥል የተመረጠና ቁንፅል ብቻ ከሆነ የሚኖረን ምሥልና መረጃም እንዲሁ የተወሰነና ቁንፅል ይሆናል” ይላል። ስለሆነም በየትኛው ዓይነት ተረክ በሚዲያ ጎልቶ የሚወጣ ሐሳብ የሚዲያው ተከታታዮች ዘንድ ሰርፆ ያንን እንደ ብቸኛና ተለምዷዊ እውነትና ዘይቤ አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ የሚታየው።

ከዚህም በላይ ሚዲያ የማኅበረሰብን ዕይታና አመለካከት ለመለወጥ ከፍተኛ ጉልበት እንዳለው ይታወቃል። ጅምላ ፍረጃዎችንም ይሁን የተሳሳቱ አስተሳሰብና አመለካከቶችን ለመለወጥም ጥቅም ላይ ውሎ ውጤት ማስመዝገቡ የሚዲያ ዕድገት ታሪክ እምብዛም አኩሪ ባልሆነባት በአገራችን ጭምር የታየ ነው። የተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍሎች በፆታ፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በአካል ጉዳተኝነት በሌሎችም የማንነትን ማንፀባረቂያ መንገዶችና መለያዎች ሁሉ ውክልና ማግኘት አለባቸው የምንለውም ለዚሁ ነው። ዴሞክራሲዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት የአንዲት አገር ሁሉም ሕዝቦች በየመልካቸውና ምሥላቸው መወከል አለባቸው፣ መንግሥትም በሥልጣንና በሥራ ረገድ ሕዝቡን የሚመሥል መሆን አለበት ይህም የዲሞክራሲ መገለጫ ነው የምንለውም ለዚሁ ነው።

የሚዲያ ውክልና በኹለት መንገድ የሚሠራ ሲሆን፣ ይኸውም አንደኛ በሚዲያ ውጤቶች ላይ በሥራ በመሳተፍ እና ኹለተኛው ተሳትፏቸው ኖረም አልኖረ ሁሉንም ኅብረተሰብ የሚወክሉ ጉዳዮች እንዲዳሰሱ በማድረግ ነው። በሚዲያ ሥራ ላይ የሚሠማሩ ሰዎች በፆታ፣ በእምነት፣ በአመለካከት፣ በተቻለ መልኩ ብዝኀነት ያላቸውና በሚቻል መጠን ማኅበረሰቡን እንዲመስሉ ማድረግ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል አስተሳሰቡና ያለፈበት ልምድና ተግዳሮት በራሱ ዕይታ እንዲቀርብ ያስችላል። በተለይ የፆታንና አካል ጉዳተኝነትን ጉዳይ በሚመለከት ሌሎች የማኅበረሰቡ ክፍሎች ከሚያልፉበት በተለየ የሚታለፍበት በመሆኑ የተለየ መነፅር ያሻዋል። አንዳንዱን ሴቶች በማኅበረሰቡ ያላቸውን ሥር የሰደደ ዝቅ ያለ ሥፍራና ያልተገባ አተያይ ለመመልከት፣ ተቆርቋሪም ሆኑ በትክክለኛ መልኩ ለማሳየት ሴት መሆንን ይጠይቃል። ከዚህም ሌላ እንደ አካል ጉዳተኛ ያሉ የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተነሱትን ድምፅ መልሰው እንዲያገኙ ራሳቸው ስለራሳቸው እንዲወያወሩ እነሱን በሚመስል ሰው ውክልና ሊያገኙ የግድ ይላል።

በሚዲያው የምናየው ግን፣ እዚህ ግባ የማይባል ዕድገቱ እንዳለ ሆኖ፣ በርካታ የፖለቲካ አመለካከት ያለው የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር የተለያየ ባህል ያለው ሕዝብ ቢኖረንም የምናገለግለው ግን የተወሰነውን ሐሳብ ቋንቋ አመለካለትና ባሕል ነው። በሚዲያው በቋንቋ ብዝኀነት ረገድ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ከመንግሥት ውጪ ያሉ ከአማርኛ ሌላ በሌሎች ቋንቋዎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች የሉንም። የሚነሱት ሐሳቦችም ከተማ ለሚኖረው ጥቂት ምሁር እንጂ ቢያንስ ማንበብ ለሚችለው ለሰፊው ሕዝብ የሚሆን አይደለም። ወጣቶች ከፍተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ቢይዙም የእነሱን አስተሳሰብ ለመቅረፅ አልሞ እነሱን ትኩረት አድርጎ ቢቻል በእነሱው የሚዘጋጅ የተሻለ ረብ ያለው ጋዜጣም ሆነ መጽሔት የለም።
በፆታ ረገድም ቢሆን ጥናት እንደሚሳየው በሚዲያ፣ በመረጃ ምንጭነት ከሚያገለግሉት ሰዎች 90 በመቶው ወንዶች ናቸው። ሴቶች እንደ ተጎጂና ተጠቂ ካልሆነ ኤክስፐርት ሆነው አይቀርቡም። በሴቶች ጉዳዮች ሳይቀር የሚያወሩት ወንዶች ናቸው። ሴቶች በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች (ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ድራማ) የሚወከሉትም ጅምላ ፍረጃውና አሉታዊ አመለካከቱ ተመርጦ ነው።

ሴቶችና ከተለያዩ ማኅበረሰቦችና አካል ጉዳት ካለባቸው ወገኖች የተውጣጡ የተለያዩ አመለካከትና አስተሳሰቦችን የሚወክሉ ባለሙዎችን ለመቅጠር ሚዲያዎች የድጋፍ እርምጃ አስፈላጊ ከሆነ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል። ያሏቸውም ጋዜጠኝነት ውክልናና የሐሳብ ብዝኀነትን ማካተት መብትም ጭምር መሆኑን አውቀው በዘገባቸው ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች መወከልና ማካተትን ሁሌም ከግምት ውስጥ ሊያስገቡና ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ለሚዲያው የተሻለ የሥራ ከባቢና የሚያሠራ፣ የሚደግፍ ሕግና መዋቅር ስንጠይቅ መጀመሪያ ሚዲያውን ሥነ ምግባሩን ጠብቆ የሚሠራ ኃላፊነት የሚሠማውና እምነት የሚጣልበት የማድረግ ሥራ መሥራት ይገባናል። የሌላውን ጉድፍ ለማውጣት መጀመሪያ ምሰሷችንን ከራሳችን ዓይን ውስጥ ማውጣት ተገቢ ነው።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here