ወንድም መሆን ማለት…

0
613

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ታሪክ ልንገራችሁ። እንዲህ ነው፤ በቤቱ ለእህቶቹ ኃላፊነት የሚሰማውና እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተል ታላቅየው ወንድም ነው። በዕድሜ ከእህቶቹ ብዙ የሚርቅ ሆኖ ግን አይደለም፤ እህቶቹ አይደሉ? ይወዳቸዋል። “ያንን ልበሱ…ይሔ ጥሩ አይደለም…ይህን አውልቁ” የሚል ተናጋሪ መስታወት ሆኗቸውም ኖራል። እህቶቹም ቢሆኑ ምንም እንኳን የማይዋጥላቸው ብዙ ነገር ቢኖርም ከፍቅሩ እንጂ በክፋት እንዳይደለ በማወቅ ይታዘዙታል፤ ምክሩን ይሰማሉ፤ ጋሻችንም ይሉታል።

ከእህቶቹ መካከል አንዷ…እርሷ ወንድሟ ቤት ባለመኖሩ ከጓደኛዋ ስጦታ የተሰጣትን ልብስ ለብሳ፣ ደማምቃ ከቤት ወጥታለች። መንገድ ጀመረች፤ ቀጠሮ አላትና ለመድረስ ፈጠን ፈጠን እያለች ትራመዳለች። በመንገዷ መካከል ከኋላዋ ኹለት ወጣት ወንዶች የራሳቸውን ወግ ይዘው በምትሔድበት አቅጣጫ ይከተላሉ። በመሃል ግን እርሷን ሲያዩ የያዙትን ጨዋታ ትተው ወደ እሷ አተኮሩ።

“እሙዬ…. ውድድር ላይ ነሽ እንዴ?” አላት አንዱ፤ ዞራ ለመመልከት አልደፈረችም። ወንድሟ እንዲህ ያሉ ሰዎችን በንቀትና በዝምታ ማሳለፍ ጥሩ መልስ እንደሆነ ስለመከራት ዝምታን መረጠች፤ መልስ አልሰጠችም። ብቻ እርምጃዋን እያቀባበለች ፍጥነቷን ጨምራ የውስጥ ለውስጥ መንገዱን ተያያዘችው።

“ለምን አታናግሪንም… ስሚ እንጂ! ነው መኪናዬን ይዣት ልምጣ” አንዱ አሁንም ቀጠለ፤ መልስ ከመስጠት ይልቅ በፍጥነት በመራመድ መራቁን መረጠች። “ባልሰማ መሆኑ ነው!…በሰፈራችንማ ባልተናቅን!!” ሌላው ተናገረ።

የአሁኑ ንግግር አስደነገጣት። እግሯ እየተራመደላት ቢሆንም ብርክርክ አለ። ጭራሽ እንደሰከረ ሰው ሊያደርጋት ፈለገ። ከኋላዋ ያሉትን ኹለት ወንዶች ለማየት ቅንጣት እንኳን ወኔና ድፍረት እንደማይኖራት አረጋገጠች። ጆሮዋን ባታምነው ደስ ይላት ነበር። ለጥቂት ደቂቃዎች “ልዙር አልዙር?” እያለች ከሐሳቧ እየተሟገተች፤ ወንዶቹም ከኋላዋ እየተከተሏትና በቃላት እያደረቋት ወደ ዋናው መንገድ ተቃረቡ።

ኹለተኛው ወንድ ራመድ ብሎ እጇን ይዞ “ወይ ስልክሽን ወይ አድራሻሽን ሳትሰጪማ…” በድንገት መናገር ተሳነው። ፈጠጠ፤ እጇን የያዛት ሴት እህቱ ናት? “ሊነካሽ ቀርቶ ዝንብሽን እሽ የሚለውን አልለቀውም” ያላት እህቱን እጅ ነው የያዘው? አለባበሷ ስለተቀየረ እንጂ እህቱ ነበረች?

“ወንድም ጋሼ” አለች የሞት ሞቷን። “ምን ሆነሽ ነው ሌላ ሴት የመሰልሽው?” ጠየቃት። ተናደደች፤ እንደወትሮው ታላቅ ወንድሟን በአክብሮት አልፈራችውም። “ምን ሆነህ ነው ሌላ ወንድ የመሰልከው?” መለሰችለት። “እስከዛሬ ስትጠብቀኝ የነበረው ከራስህም ጭምር ነው ማለት ነው?” ተቆጣች። “እህቶቻችሁን የምትበሉትና የምታስበሉት ለካ ራሳችሁ ወንድሞች የተባላችሁ ናችሁ?” ጥላው ሔደች።

ወንድም ጋሻው! ለእናትህ ልጅ እህትህ ብቻ አይደለ፤ ስለምን ለሴቶች ሁሉ ወንድም አትሆንም? እስከጊዜው ድረስ የአንተንም እህት በወንድምነት ሌላው ሊጠብቅልህ እንደሚችል ስለምን ልብ አትልም? ወንድም መሆን ማለት ይህ እንጂ ሌላ ምንድን ነው?

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here