ለንግድ እና የጭነት መኪኖች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ሊገጠምላቸው ነው

0
608

የፌደራል የትራንስፖርት ባለሥልጣን ለንግድ እና ለጭነት ተሸከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲገጠሙ መወሰኑን እና አቅራቢ ድርጅቶችም መርጦ መጨረሱን አስታወቀ።

በአገሪቱ እሰካለፈው መጋቢት ድረስ 9 መቶ 77 ሺሕ 3 መቶ 49 ተሸከርካሪዎች ተመዝግበው ያሉ ሲሆን የንግድ እና የጭነት

አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያውን በመግጠም ፍጥነታቸውን በ80 ኪሎ ሜትር በሰዓት የተገደበ ያደርገዋል። መሣሪያው የፍጥነት መቆጣጠሪያ የሚገጠምላቸው ተሽከርካሪዎችን ከዚህ ፍጥነት በላይ መሔድ እንዳይችሉ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም ስለ መኪናዎቹ ሙሉ መረጃ ዋና መሥሪያ ቤት ወደሚገኘው የመረጃ ቋት መረጃዎችን ይልካል።

በተሸከርካሪዎቹም የሚገጠመው የተቀናጀ የተሸከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ከዓለም ዐቀፍ ስርዓት አቅጣጫ (GPS) የተጣመረ በመሆኑ ባለቤቶች መኪኖቻቸው ቢጠፋም እንኳን የት እንደሚገኝ ማወቅ ይችላሉ። ተሽከርካሪዎቹም ከተወሰነላቸው ፍጥነት በታች እንዲቀንሱ በሚገደዱበት ሁኔታ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያው ተሸከርካሪው ከፈጠነ በድምፅ ወይም በምልክት ፍጥነቱን እንዲቀንስ ለአሽከርካሪው የሚያስጠነቅቅ እና ወደ መደበኛው ፍጥነት የሚመልስ ነው።
መመሪያው ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እንዲሁም የሚመረቱ መኪኖች የፍጥነት መገደቢያውን የመግጠም ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን መሣሪውን ያልገጠሙ ወይም ከተጠቀሰው ጥራት በታች የሆነ መሣሪያ የገጠሙ መኪኖች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተደንግጓል።

የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ብቃት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ያቆብ በላይ ለአዲስ ማለዳ እደገለፁት በአገራችን የመንገድ ትራፊክ አደጋ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ የሚባል የመኪና ብዛት ቢኖራትም ከፍተኛ የሆነ የሰው ሞት፣ የንብረት መውደም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው። ለዚህም ዋና ዋና የሚባሉ 30 ዓይነት የአደጋ መንሥኤዎች ሲሆኑ ከነዚህም የአንደኝነት ደረጃውን የያዘው የተሽከርካሪ ፍጥነት እንደሆነ ታውቋል። አገሪቱ ባለፈው የበጀት ዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ በትራፊክ አደጋ ያጣች ሲሆን ከ5100 ሰው በላይ ሕይወት አልፏል 7700 ሰዎች ላይም ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያዎቹ እንዲገጠምላቸው የተወሰኑት ተሸከርካሪዎችም መሣሪያውን ማስገጠም ግዴታቸው ከመሆኑም ባሻገር ይህን የማያደርግ ማንኛውም አሽከርካሪ ዓመታዊ የተሸከርካሪ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደማያገኝ ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።

በአብዛኛው ተሞክሮ ያላቸው አገሮች ውስጥ ያሉ የሕዝብ መንገዶች አብዛኛውን ጊዜ ካልተፈቀዱ በስተቀር በሁሉም መንገዶች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መንገዶች ተፈፃሚ ሲሆኑ አብዛኞቹ የመንገድ መብራቶች ወይንም በመንገድ ላይ አካላዊ አቀማመጦቹን በመጠቀም አደጋን ይከላከላሉ። ለምሳሌ በቅርቡ ኬንያ ይህንን መቆጣጠሪያ ተግባራዊ በማድረጓ 30% አደጋውን መቀነሷ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here