ፕላስቲክ አምራቹ ኩባኒያ በከፍተኛ የግብር ስወራ ተከሰሰ

0
569

ኦክስፎርድ ፖሊታይሊን ኢንደስትሪስ ኩባንያ 52 ሚሊዮን ብር ከሚጠጋ የግብር ስወራ ወንጀል ጋር በተየያዘ በቀረበበት ክስ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባስ መሃመድ እና የሺያጭ ኃላፊው የዋስ መብታቸው ተከብሮ እንዲሁም ከአገር ሳይወጡ ክሳቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። ሦስት የማምረቻ ኩባኒዎች ያሉት ኦክስፎርድ ፖሊታይሊን ለእህት ኩባኒያው ኦክስፎርድ አማልጋሜትድ በተጋነነ የዋጋ ቅናሽ ምርቶቹን በተደጋጋሚ በመሸጥ እንዲሁም መርካቶ በሚገኘው የምርት ማከፋፈያው ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በፈጸመው ግዢ ወቅት በተሰወረ ግብር እንዲሁም ያለአግባብ ተመላሽ ጠይቋል በሚል ተጠርጥሯል።

የኩባኒያው ጠቅላላ የግብር እዳ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በ1996 (እ.ኤ.አ) ወደ ኢትዮጵያ የገባው ድርጅቱ እስከ 2013 ድረስ በጥሩ ትርፍ 3600 ሠራተኞች ቀጥሮ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ከገቢዎች ባለሥልጣን ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል። ድርጅቱ ሙስና ተጠይቄአለሁ ብሎ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ማመልከቱም ይታወቃል።

ዐቃቤ ሕግ በገቢ ግብር ሕጉ መሰረት ኹለት ድርጅቶች እህት ኩባኒያ በሆኑ ጊዜ አንዱ ለሌላው ምርቱን መሸጥ የሚችል ቢሆንም ለመደበኛው ገበያ ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር እጅግ የተራራቀ ዋጋ ቅናሽ በማድረግ ግን መንግሥት ከግብይቱ ማግኘት የሚገባውን የተለያዩ ግብሮች ማሳጣት ግብ ስወራ ነው ሲል ድርጅቱን ወንጅሏል። በተጨማሪም ድርጅቱ መርካቶ በሚገኘው ማከፋፈያው ያደረጋቸው የተለያዩ ሺያጮች ላይ በተደረገው ምርመራ የግብር ከፋይ ቁጥራቸው ከማይታወቁ ድርጅቶች ጋር፣ ከተጠቀሰው የሺያጭ መጠን ጋር አቅማቸው ከማይመጣጠን ጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች ጋር የተደረጉ እንዲሁም ከገበያ ዋጋው በጣም ዝቅ ባለ ዋጋ የተደረጉ ሺያጮች ድርጅቱ ግብሩን ሰውሯል እንዲሁም ያለአግባብ ተመላሽ ጠይቋል በሚል እንዲጠረጠር ምክንያት ሆኗል።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሕንድ ኩባኒያ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ አምስት የተለያዩ ፋብሪካዎች እንደነበሩት ታውቋል። ኹለቱ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በቃሊቲና ወለቴ ይገኙ የነበሩት በባንክ ሐራጅ መሸጣቸው ታውቋል። ድርጅቱ አሁንም በተለያዩ የግል ባንኮች እዳ ያለበት ሲሆን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር በጣለበት እግድ ምክንያት እዳውን ሰርቶ መክፈል አለመቻሉን ገልጿል።

በኪሳራ ውስጥ መኖሩን ያስረዳው ድርጅቱ ለግብር ይግባኝ ሰሚ ቅሬታውን ለማስገባት 50 በመቶ ቅድሚያ ለመክፈል አቅሙ ስላልፈቀደ መብቱን መጠቀም አለመቻሉንም አስረድቷል። ከ2007 የጀመረው የመንግስት የግብር ጥያቄ ወለድ እና ቅጣትንም ይጨምራል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በገቢ ግብር በተመሰረተበት ክስ ላይ እንዲከላከል በፈቀደው መሰረት ኹለት መከላከያ ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ለሚያዚያ 11/2011 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here