የገናሌ ግድብ በመዘግየቱ ነገሌ ቦረና እና ሌሎች 7 ወረዳዎች ለሦስት ወራት ተጠምተዋል

0
748

የበጋ ወቅት መግባቱን እና የዝናብ እጥረቱን ተከትሎ ጉጂ ዞን ዋና ከተማ ሆነችውን ነጌሌ ቦረናን እና ሌሎች የገጠር ከተሞች የመጠጥ ውሃ የሚያቀርበው ግድብ መድረቁን ተከትሎ በከተማዋ ላለፉት ሦስት ወራት ውሃ አለመኖሩን ነዋሪዎች ገለጹ። የዞኑ የውሃና ፍሳሽ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ግድቡ ቢደርቅም ከሦስት የተለያዩ የውሃ ጉድጉዶች ውሃ በፈረቃ ለነጌሌ ቦርና ከተማ እየደረሰ መሆኑን እና ለተለዩ የሕዝብ ተቋማትም የጭነት መኪና የክልሉ መንግሥት ተከራይቶ ውሃ ካለባቸው ሌሎች ውረዳዎች በየቀኑ እየቀረበ መሆኑን የዞኑ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሥራ ሒደት ኃላፊ መሳይ ገረመው ተናገረዋል።

ዓመታትን ያስቆጠረው የውሃ ችግር የገናሌ የመጠጥ ውሃ ግድብ ሲጠናቀቅ ችግሩን ይፈታዋል ተብሎ ቢጠበቅም ግድቡ እስካሁን ከ80 በመቶ አለማለፉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ነጌሌ ቦርና ወደ 60ሺሕ ገደማ የሚገመት ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ስትሆን በሳምንት በየቀበሌው በሦስት ሺፍት ውሃ እየተዳረሰ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዎቹ ውሃ የማይደርስባችው አካባቢወች መኖራቸውን ግን አምነዋል። በጭነት መኪኖች የሚከፋፈለው ውሃ ለሆስፒታሎች፣ ማረሚያ ቤት እና ለመሳሰሉት ተቋማት ሲሆን ለገጠር ወርዳዎችም አንድ አንድ መኪና ተመድቦ የመጠጥ ውሃ የማዳረስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

ሊበን፣ ጉሚ ኢሊዳዶ፣ ጎሮ ዳላ፣ ዋደራ፣ ሳባ ቦሩ፣ አጋ ዋዩ ከወርዳዎቹ መካከል ሲሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አርብቶ አደሮች የሚገኙበት አካባቢዎች ናቸው። ገናሌ ግድብ ሲጠናቀቅ የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር ከመፍታት ባለፈ ለወረዳዎቹ የውሃ አቅርቦት ለውጥ እንደማይኖር ኃላፊዎቹ ተናገረዋል። ለገጠር ከተሞቹ የተቆፈሩ ʻፎልድʼ በመባል ሚታውቁት የውሃ ኩሬቆች ለእንስሳት ውሃ ለማቅረብ ሲውሉ የነበረ ሲሆን በመድረቃቸው ሳቢያ ለእንስሳት የሚሆን ውሃ ችግር መከሰቱ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here