በነዳጅ እና ነዳጅ ውጤቶች ላይ የትርፍ ሕዳግ የሚያወጣና ዲፖዎችን የሚገነባ አዲስ ባለሥልጣን ሊቋቋም ነው

0
702

ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች ላይ የዋጋ ተመን በማውጣት የትርፍ ሕዳግ የሚተምን እና ለማከማቻነት በሚውሉ ዲፖዎች ግንባታ ላይ ድጋፍ የሚያደርግ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በሚል ሥያሜ የሚቋቋመው ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እና በንግድ ሚኒስቴር ሥር ይከናነወኑ ነበሩ ኃላፊነቶችን እንደሚጠቀልል ለመረዳት ተችሏል።

በማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተብራራው አዲሱ ባለሥልጣን የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች እንዲሁም የፋብሪካዎችና የተሸከርካሪዎች ዘይትና ቅባቶችን የጅምላና ችርቻሮ መሸጫ ወጋዎችን እንዲሁም የነዳጅ ማጓጓዣ ታሪፎችን እንደሁኔታው በማሻሻል የውሳኔ ሐሳብ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለንግድ ሚኒስቴር ያቀርባል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ውሳኔ በመመርኮዝ ተግባራዊነቱን እና ተፈፃሚነቱን የመቆጣጠር ሥልጣን እንደሚኖረውም ተገልጿል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች በተደጋጋሚ በሚያጋጥመውን የቤንዚን እጥረት ወቅት የመአድን ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር እና የየከተማ አስተዳደሮቹ የቁጥጥር ሥራዎችን አንዱ ወደሌላው ሲያንከባልል ቆይቷል።

የተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ መቋቋም በአገር ውስጥ በተገቢው መንገድ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም ግብይት እንዲኖር እና እነዚህን የቁጥጥር መበታተን ሰብስቦ በመፈጸም ዋነኛው የባለሥልጣኑ የመቋቋሚያ ምክንያት እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሚንስቴሮች ሥር የነበረው የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች ስርጭት በርካታ ክፍተቶችና የመልካም አስተዳደር እጦት ይስተዋልበት እንደነበር የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ኃላፊ ታደሰ ኃይለማሪያም ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አያይዘውም አዲስ በመቋቋም ላይ የሚገኘው ባለሥልጣን ጋር አብረው በቅንጅት እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ታደሰ ሲቀጥሉ ነዳጅ ከውጭ መግዛቱን ኃላፊነት የአቅራቢ ድርጅቱ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ ከወደብ ተረክቦ ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና በማከፋፈል የሚደረገው ሒደት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ኃላፊነት ይሆናል ብለዋል። በአሁኑ ሰዓት ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ ፣ ኬሮሲን፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ ተናግረው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ከኹለት እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በዓመት ወጪ እንደምታደርግ አክለዋል።

ባለሥልጣኑ በነዳጅ እና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ሥራ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን ከስርጭትና አቅርቦት ጋር በተገናኘ ሕጋዊ ባልሆነ ተግባር ሲሳተፉ ተገቢውን የቅጣት እርምጃ በራሱ መውሰድ እና ማስወሰድ ኃላፊነት አለው። ከዚህም ጋር ተያይዞም ባለሥልጣኑ የነዳጅ የመጠባበቂያ ክምችት መጠን በዓይነት እንዲወሰን ማድረግ ስልጣን ይኖረዋል።

የነዳጅ ዋጋ ቁጥጥር የሚደረግበትና በየወሩም ክለሳ የሚደረግበት ሲሆን አግባብ ባላቸው ሕጎች መሰረት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን ከመስጠት ባሻገር የተሰጡ ሥራ ፈቃዶችን ለተገቢው ዓላማ መዋላቸውን የሚቆጣጠረው የሚቋቋመው አዲስ ባለሥልጣን ሲሆን ተጠሪነቱም ለንግድ ሚኒስቴር ይሆናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here