ለመስተዳድሩ ሠራተኞች ቤት ለመገንባት ምዝገባ እየተካሔደ ነው

0
459
  • ከአንድ ሺሕ በላይ ቤቶች ባለድለኞችን እየተጠባበቁ ነው

አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ለመንግሥት ሠራተኞች የኪራይ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ሰርቶ ሊያስረክብ እንደሆነ አስታወቀ።

የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የቤት ርክክብና ማስተላለፍ ኃላፊ በድሉ ሌሊሳ እንደገለፁት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተጋረጡ ፈተናዎች መካከል ትልቁ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እንደመሆኑ መጠን መንግሥት ቤት ፈላጊ ለሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ማዳረስ ባይቻልም አብዛኞቹን በተመጣጣኝ ዋጋ የቤት ኪራይ እንዲያገኙ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታዎች እየተጀመሩ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

በከተማዋም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት ከሆኑት ይልቅ ገና በመጠባበቅ ላይ ያሉት በእጥፍ ስለሚበልጡ መንግሥት ሁሉንም የቤት ባለቤት ማድረግ አይችልም። ሆኖም ግን በአሁኑ ሰዓት የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ አነስተኛ በመሆኑ፣ እንዲሁም ሠራተኞች በሥራቸው ላይ ውጤታማ ሆነው እንዲሠሩ ለማበረታታት የተጀመረ ፕሮጀክት ሲሆን በከተማዋ በብዛት የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ለመንግሥት ሠራተኞች ቅድሚያ ተሰጥቶ ግንባታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አክለው ገልፀዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ምን ያህል ቤት ፈላጊ እንዳሉ ከተረጋገጠ በኋላ በፍጥነት የማጣራት ሥራው ተጠናቆ ቤታቸውን ይረከባሉም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በኩል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው 5 ሺሕ የመንግሥት ሠራተኞች በ3 መቶ 16 ብር የኪራይ ቤት ባለቤት ማድረጉ እንዳለ ሆኖ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስተላለፍ ዕጣ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች 20 በመቶ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ ይታወሳል።

የከተማ አስተዳደሩ በ2009 በስድስት ክፍለ ከተሞች ላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በኩል ለመምህራን ካስተላለፋቸው 5 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የቤት ባለቤት የሆኑት አራት ሺሕ 920 ሲሆኑ የተቀሩት ቤቶች እስከአሁን ክፍት መሆናቸው ይታወቃል።

በተያያዘም ከዚህ በፊት 10/90 ለተመዘገቡት የከተማዋ ነዋሪዎች ከተዘጋጁት 24 ሺሕ ቤቶች ውስጥ የቤት ባለቤት የሆኑት 18 ሺሕ ብቻ ናቸው ሆኖም ክፍት ከሆኑት 6 ሺሕ ቤቶች ውስጥ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞች 5 ሺሕ ቤቶችን ማስረከቡ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ሺሕ በላይ ቤቶች ክፍት ሆነው ባለቤታቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here