የአርበኞች ግንቦት 7 አለመክሰም ጥያቄ አስነሳ

0
580

የአርበኞች ግንቦት 7 አለመክሰም አብረውት በመሥራት ላይ ከሚገኙትና ሥማቸው እንዲጠቀስ ካልፈለጉ ፖለቲከኞች ቅሬታ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል። የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው፥ ንቀናቄው ከአምስት ሳምንት በኋላ እንደሚከስም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ሌሎች ፓርቲዎችን እያከሰመ፣ እርሱ ግን በየክልሎች በሥሙ ቅስቀሳ እያደረገና እያደራጀ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ፖለቲከኞቹ፣ ውኅደቱን የመፍጠር እንቅስቃሴውን ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ ያለው እርሱ እንደመሆኑ መጠን፣ መጀመሪያ ራሱን አክስሞ መጀመር እንደነበረበት ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ወደ የፓርቲዎች እየሔደ እንዲዋሐዱና ራሳቸውን እንዲያከስሙ መወትወቱን ቀጥሏል ሲሉ ተግባሩን ይቃወማሉ።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ እንደሚሉት አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች አምስት ፓርቲዎች ጋር ውሕደት ላይ ቢሆንም፣ አሁንም በተለያዩ ክልሎች ቅስቀሳ እያደረገ ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ “ሁሉም ፓርቲዎች የሚከስሙ ከሆነና በጋራ ለመሥራት ዕቅድ ካላቸው ለምን በግሉ ይንቀሳቀሳል?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ፓርቲዎች እንዲከስሙ በተደጋጋሚ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ራሱ አርዓያ መሆን እንደነበረበት በመጠቆም።

ለቀረበው ቅሬታ ኤፍሬም በሰጡት ምላሽ፥ በየቦታው ስብሰባ የምናደርገው አገሪቱን የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት እንጂ ለምረጡኝ ቅስቀሳ አይደለም ብለዋል። የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ሆን ብለው የሚሰሩ ኃይሎች በመኖራቸው የአገሪቱ ሕዝቦች የእነሱን አካሔድ እንዲረዱት ለማድረግና ለማስተማር እንደሆነም መልሰዋል።

እኛ አንድም ቀን ፓርቲዎችን ʻክሰሙ፥ አትክሰሙʼ ብለን አናውቅም የሚሉት ኤፍሬም ይህ መሰረተ ቢስ ወሬ ነው ሲሉ የተነሱባቸውን ቅሬታዎች አጣጥለውታል።

አክለውም አርበኞች ግንቦት 7 ፓርቲ ሳይሆን ንቅናቄ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበራዊ ፍትሕ መኖር አለበት የሚል ርዕዮተ ዓለም ይዘን ነው የምንንቀሳቀሰው ያሉት ኤፍሬም “በዜግነት ላይ የተመሰረተና አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ብቻ በእኩልነት የሚታይበት አገር ለመመስረት ነው የምንታገለው። የምንመሰርተውም ውሕደት ርዕዮተ ዓለምም እሱን ማዕከል ያደረገ ይሆናል” ብለዋል።

በአምስት ሳምንት ውስጥ ንቅናቄው ጠቅላላ ጉባኤውን በመጥራት እንደሚከስም ታውቋል። ይህንን ለማድረግ ግን ኤፍሬም እንደገለጹት በመላው ዓለም የሚገኙ አባሎቻቸውን መጥራት ስለሚኖርባቸው ዝግጅቱ ጊዜ እንደወሰደባቸው በመጠቆም፣ አሁን ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉባኤው እንደሚካሔድና ንቅናቄውም በይፋ እንደሚከስም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሚሰነዘሩባቸው ነቀፌታዎችና በዕውነት ላይ ያልተመሰረቱ ክሶች መታረም እንዳለባቸው በመጠቆም፣ ችግሮች ካሉም እንደሰለጠነ ሰው በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here