በወለጋ የንግድ ባንክ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ቅጣት ተጥሎባቸው የነበሩ ግለሰብ ሹመት ተሰጣቸው

0
440

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታኅሣሥ 18/2011 በጊምቢ ቅርንጫፍ ከተፈጸመው የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ያልተገባ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ተብሎ ቅጣት ተጥሎባቸው የነበሩትን ካሳሁን ሽፈራው የኦፕሬቲቭ ሪሌሺንሺፕ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አድርጎ መሾሙ ጥያቄ አስነሳ።

በተለይም ያለ ባንኩ ዋና መስሪያ ቤት እውቅና እንዲሁም ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ዘረፋው በተፈፀመበት ዕለት ጠዋት ላይ የጊምቢ ቅርንጫፍ እንደ ʻኢሹʼ ቅርንጫፍ – ማለትም በአካባቢው ከሚገኙ ቅርንጫፎች ብር ለማሳደር – እንዲያገለግል ትዕዛዝ መስጠታቸው ተረጋግጦ እያለ ሹመት መሰጠቱ ውዝግብን ፈጥሯል።

በተጨማሪ በታጣቂዎች ገንዘቡ በተዘረፈበት ቀን 9 ሰዓት ከ45 ላይ ያለበቂ አጀብ ገንዘቡን አልሰጥም ያሉትን የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ደሳለኝ ረጋሳን በስልክ ገንዘቡን ለዳሌ ቅርንጫፍ እንዲሰጡ ማዘዛቸውን ካሳሁን አምነው ቢቀጡም ተጨማሪ ሹመት መሰጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ ከባንኩ የሰው ሀብት ክፍል ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልፀዋል።

የባንኩ መተዳደሪያ ደንብ ማንኛውም ዓይነት የዲሲፕሊን ቅጣት ያለበት ሰው ለስድስት ወር ምንም ዓይነት ዕድገት አያገኝም ቢልም ካሳሁን ግን በድርጅቱ ከፍተኛው የዲሲፕሊን ቅጣት እያለባቸው ለሹመት መብቃታቸው እንዲሁም በእሳቸው ትእዛዝ ገንዘቡን የሰጡት እና የተቀበሉት ግለሰቦች ከሥራቸው ያለ በቂ ማስጠንቀቂያ መባረራቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የባንኩ አስተዳደር ኮሚቴ በቀን የካቲት 20/2011 ባደረገው ስብሰባ ከቀኑ 2 ሰዓት ላይ በተያዘው ቃለ ጉባኤ ካሳሁን እና ጸጋዬ መገርሳ እያንዳንዳቸው የወር ደመወዛቸው 20 በመቶ እና የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ወስኗል። ኮሚቴው ካሳሁን ላይ ቅጣት የጣለው ያለ ዋና መሥሪያ ቤቱ ፍቃድ እና ዕውቅና ጊምቢ ቅርንጫፍ ነጆ ላይ ያለውን ችግር በመግለፅ 25 ሚሊዮን ብር ከነቀምቴ እንዲጠይቅ በማድረግ እንደ ‘ኢሹ’ ቅርንጫፍ ሥራ እንዲሠራ በቃል ለሥራ አስኪያጁ ማዝዛቸውን አምነው ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

የነጆ ቅርንጫፍ እንደ ኢሹ ቅርንጫፍ ሲያገለገል የቆየ ሲሆን በጥቅምት ወር በታጣቂዎች በተፈጸመ ዝርፊያ ወቅት አንድ ሹፌር መገደሉን እና አራት አጃቢዎች የደረሱበት ባለመታወቁ ፖሊስ አጀብ አልሰጥም በማለቱ ከጊምቢ ገንዘብ ማውጣት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

የዲሲፕሊን ኮሚቴው ከላይ በተጠቀሰው ቀን የጊምቢ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ እና ገንዘቡን ለመቀበል የመጡትን አንዱአለም ደበላ በተመሳሳይ ቅጣት በሙሉ ድምጽ የወሰነ ቢሆንም በማግስቱ በፕሬዝዳንቱ ትእዛዝ እንደገና ተሰብስቦ ሹመት ካገኙት ከካሳሁን ውጪ ሌሎቹ ከሥራ ገበታቸው ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንዲባረሩ ወስኗል።

በባንኩ ፕሬዝዳንት የካቲት 1/2011 በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት በመጋቢት ወር 2011 የተሠራው የውስጥ ኦዲት በታርጋ ቁጥር 44392 ኮድ 03 መኪና ገንዘቡ ተጭኖ መሔዱን የሚያትት ሲሆን አንዱለም ደበላ የተባሉት የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ፣ ዘላለም ገብረ ማሪያም የተባሉ መኪናውን ሲያሽከረክሩ የነበሩ ሹፌር እና ገንዘቡን ያጀቡት በእስራት ላይ የነበሩ ሲሆን በጦላይ ለኹለት ወር ሥልጠና ወስደው ሲመለሱ ክስ መባረራቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ ወደ ዳሌ ቅርንጫፍ ለመድረስ 10 ደቂቃ ሲቀራቸው ቁጥራቸው 20 አካበቢ የሚጠጉ ታጣቂዎች ለአንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከታገቱ በኋላ መለቀቃቸው ይታወቃል።

አንድ ‘ኢሹ’ ቅርንጫፍ ለማቋቋም የብሔራዊ ባንክ ፍቃድ መስጠት ሲኖርበት የፈቃዱ ግልባጭም የቅርንጫፉ ግድግዳ ላይ መሰቀል አለበት። አንድ ባንከ ከፍተኛ መያዝ የሚችለው የገንዘብ ልክ ሲያልፍ በአቅራቢያው ለሚገኘው እና ለተፈቀደለት ቅርንጫፍ (‘ኢሹ’ ቅርንጫፍ) ገንዘቡን የሚያስተላላፍ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊውን ዋስትና ከገባ እና የጥበቃ ሁኔታዎች ከተጠናከሩ በኋላ ነው ፍቃዱ የሚሰጠው። ይሔ ሁሉ ሁኔታ ባልተሟላበት ሁኔታ በካሳሁን ትዕዛዝ ‘ኢሹ’ ቅርንጫፉ መቋቋሙ ለጥርጣሬ ዳርጓል።

በኹለት የወለጋ ዞኖች አካባቢ በኹለት ቀናት ብቻ የተዘረፉት 17 የባንክ ቅርንጫፎች ሲሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተዘረፈበት መንገድ የተለየ መሆኑ የዓይን እማኞች ይናገራሉ። ሌሎቹ ባንኮች በተኩስ እና ባንኮቹን በመስበር ጭምር ዘረፋ ሲደረግ የንግድ ባንክ ግን በተለየ ሁኔታ ተፈጽሟል ተብሏል።

አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የፕሬዘዳንት ጽሕፈት ቤት እና የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጧት በአካልና በስልክ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።

 

ማብራሪያ

መጀመሪያ በታተመው ዜና ላይ ካሳሁን ሽፈራው የሕግ ክፍል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል ተብሎ ነበር። ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here