ከ“ሲሊከን ቫሊ’’ በፊት እና በኋላ

በአንድ ወቅት የእርሻ ማዕከል አሁን ደግሞ በዓለማችን ታላቅ የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ማዕከል የሆነውን ሲሊከን ቫሊ ጎብኝተው፥ ለዚህ ትልቅ እመርታ የዩኒቨርሲቲዎች አስተዋፅዖ ጉልህ ነው የሚሉት አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ትምህርት ቢሆን በሚል ያዩትንና የተረዱትን ለአንባቢዎቻችን በዚህ መልኩ ተርከውታል።

የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የምድራችን ትልቁ የፈጠራ ማዕከል መሆን የሚነገርለትን ሲሊከን ቫሊን በተመለከተ በዋነኛነት የሚያወሱት እንደ ጉግል፣ አፕል፣ ፌስቡክ፣ ያሁ እና አዶቤ የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ተቋማት በአንድ ላይ የተሰባሰቡበት ቦታ አድርገው ነው። በዚህ የተነሳም ከሳምንት በፊት ከይፋዊ መጠሪያው ሳንታ ክላራ ቫሊ ይልቅ ሲሊከን ቫሊ በሚሰኘው የቅፅል ሥሙ ተዘውትሮ ወደሚጠራው አካባቢ ሳመራም ከሚዲያዎች ዘገባ ከሰማሁት በመነሳት አንድ ከተማ ውስጥ ሰብሰብ ብለው ይገኛሉ የተባሉትን የቴክኖሎጂ ተቋማት ያለ ብዙ ችግር ዞርዞር ብዬ አያቸዋለሁ የሚል ተስፋን ሰንቄ ነበር። የሲሊከን ቫሊ ዋና ከተማ ተደርጋ በዘልማድ ወደምትጠራው ሳንሆዜ ከደረስኩ በኋላ ያየሁት እውነታ ግን ቀድሞ በመገናኛ ብዙኀን ከሰማሁት በመነሳት ከጠበቅኩት በእጅጉ የተለየ ሆኖብኛል። በመገናኛ ብዙኀን እንደሚያወሱት በአንፃራዊነት የቴክኖሎጂ ተቋማት ስብስብ ብለው መገኘታቸው እውነት ነው። ይሁን እንጂ ትልቁ ጉዳይ ሲሊከን ቫሊ ከግዙፉ የካሊፎርኒያ ግዛት በስተሰሜን ከሳንፍራንሲስኮ ሰርጥ አካባቢ የሚገኙትን እንደ ሳንሆዜ፣ ፓውሎ አልቶ፣ ሳንታ ክላራ፣ ማውንቴን ቪው፣ ሰኒ ቬል እና መንሎ ፓርክ የመሳሰሉትን ከተሞች ያቀፈ መሆኑ ነው። ስለዚሁ የዓለማችን ግዙፍ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ማዕከል እንደዘበት የሚወሳው እና እውነታው በእጅጉ የተለያዩ በመሆናቸው የሲሊከን ቫሊን የተመለከተውን የወፍ በረር ቅኝቴን በማስቀደም ወደ ዋናው ነጥቤ እሸጋገራለሁ።

“ከእርሻ መዲናነት” ወደ “ቴክኖሎጂ የልኅቀት ማዕከልነት”
የሳንታ ክላራ ሸለቆ በተለይ የአየር ሁኔታ ከሌሎች የአሜሪካን ግዛቶች ይቅር እና በረሃነት በብዛት ከሚያጠቃው ከሞቃታማው የደቡብ ካሊፎርኒያ ግዛት አንፃር እንኳን ለኑሮ እጅግ በጣም ተሥማሚ ነው። በክረምት እንደ ፍሪጅ በማይቀዘቅዘው በበጋው እንደሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች እንደ በርሀ ንዳድ ትንፋሽ በማያሳጥረው ምቹ የአየር ንብረቱን መሠረት በማድረግ የሳንታ ክላራ ሸለቆ የተለያዩ የእርሻ ውጤቶች ተመርተው በመላው አሜሪካንም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ይሠራጩበት ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመቶ ሺሕ የሚቆጠረው ሔክታር የእርሻ ቦታ በደረሱ ፍራፍሬዎች እና አበቦች ተሞልቶ ሲታይ የሚሰጠውን የመንፈስ እርካታ መሠረት በማድረግ የልባዊ ደስታ ሸለቆ (‘valley of hearts delight’) የሚለውን መጠሪያ አስገኝቶለታል። በጊዜው የሀብታም ገበሬዎች መናኸሪያ ከነበሩ ጥቂት አካባቢዎች አንዱ ለመሆን በቅቶ ነበር። ይሁን እንጂ በተለይ ታላቁ ድብታ (‘great depression’) በመሰኘት በሚታወቀው የአሜሪካንን ኢኮኖሚ ክፉኛ ባሽመደመደው የዓለም ዐቀፍ የምጣኔ ሀብት ቀውስ የተነሳ የዚህ አካባቢ ገበሬዎች ለከፋ ኪሳራ ሊዳረጉ ችለዋል። የኢኮኖሚ ቀውሱ በሒደትም የገበሬዎቹን ሀብት ከማሳጣትም ባለፈ ራሳቸውን ለመመገብ የሚችሉበትን ገቢ እንዳያገኙ እንቅፋት በመፍጠሩ በርካቶች ሀብትና ንብረትን ካፈሩበት ከዚህ አካባቢ ለመሰደድ ተገደዋል።

በተለያዩ ወገኖች የጋራና የተናጥል ጥረት በአንድ ወቅት ነዋሪ ገበሬዎቹን ለመመገብ ተስኖት የነበረው አካባቢ ዛሬ ላይ የዓለማችን ቁንጮ ቢሊየነሮች እና የመቶ ሺሕዎች የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች መናኸሪያ ለመሆን በቅቷል። መሠረቱን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ያደረገው የዚህ አካባቢ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ሌላኛው አንደምታ ይሔው ሲሊከን ቫሊ የሚገኝበትን የካሊፎርኒያ ግዛት የዩናይትድ ኪንግደም ኢኮኖሚ በመብለጥ አምስተኛዋ የምድራችን ታላቅ ኢኮኖሚ መሆኗ ነው። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ትልቁ ጥያቄ “በአንድ ወቅት ለእርሻነት በተለየ ሁኔታ ተመራጭ የነበረውን ይህ ቦታ ከበርካታ አገራት ኢኮኖሚ እንዲበልጥ ያስቻለውን አስገራሚ ሽግግር እንዴት ሊያመጣ ቻለ?” የሚለው ነው።

ሲሊከን ቫሊ – ሦስተኛው ትልቅ የነፍስ ወከፍ ገቢ ባለቤት
ሲሊከን ቫሊ ቀደም ብዬ እንዳወሳሁት ከዐሥራ አንድ በላይ መካከለኛ እና ትልቅ ከተሞች ስብስብ የቴክኖሎጂ ማዕከላት በብዛት የሚገኙበት አካባቢ መሆኑን መረዳቱ ተገቢ ነው። የዚህ አካባቢ ለቴክኖሎጂ መሥፋፋት እያደረገ ያለውን እጅግ ሰፊ የሆነ አስተዋፅዖ መሠረት በማድረግ የዓለማችን የቴክኖሎጂ መዲና (‘tech capital of the world’) የተሰኘውን ቅፅል ሥያሜ የተቸረው ሲሊከን ቫሊ ከ2000 በላይ ግዙፍ እና መካከለኛ የቴክኖሎጂ ተቋማት የሚገኙበት እና ከእነዚህ ተቋማት በተጨማሪም በሺሕ የሚቆጠሩ አዳጊ ካምፓኒዎች መገኛ ነው።

በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከኹለት ዐሥርት ዓመታት ቀደም ብሎ በማደሪያ ክፍላቸው የተመሠረተው ጉግል አስገራሚ ዕድገትን አስመዝግቧል። በአሁኑ ወቅት ይህ ኩባንያ ዋጋው 739 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ ዓመታዊ ገቢውም መቶ ቢሊዮን ዶላርን ሊሻገር በቅቷል። በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳደሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ጉግል ዋና መሥሪያ ቤቱን ማውንቴን ቪው ከተማ አድርጓል። በዚህችው ከተማ በነበረኝ ቆይታ ወደ የትኛውም አቅጣጫ ብጓዝ የጉግል ቢሮ ያልሆነን ሕንፃ ማግኘቱ በጣም አዳጋች ሆኖብኝ ነበር። በአጭሩ ማውንቴን ቪው ከተማ የሚገኙት አብዛኞቹ ሕንፃዎች በጉግል የተያዙ ናቸው ማለቱ ይቀላል። በአሁኑ ወቅት ለ94 ሺሕ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረው ጉግል ይህ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ዩቲዩብን ጨምሮ ከ211 በላይ ካምፓኒዎችን በመግዛት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የቻለ ነው።

በቅርቡ የዓለም ባንክን መረጃ መሠረት በማድረግ በተደረገ ጥናት መሠረት ግዙፉ የቴክኖሎጂ ካምፓኒ አፕል ዋጋ ከ16 አገራት በቀር ቀሪዎችን የዓለም አገራት ኢኮኖሚ መብለጡ ተገልጿል። አፕል በስቲቭ ጃቭ እና አጋሮቹ በ1976 (እ.ኤ.አ) የተመሠረተበትን አነስተኛ ጋራዥ (የመኪና መቆሚያ) በብዛት ከሚጐበኙ የሲሊከን ቫሊ የቱሪስት መስህቦች መካከል አንዱ ነው። የአፕልን ዋና መሥሪያ ቤት ተመልክቼ ይሄንኑ መነሻው የነበረውን ጋራዥ ስጐበኝ ለማመን የሚከብደውን የካምፓኒውን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ዕድገት ከመዘርዘሩ ይልቅ በቀጣይ አንድ ምሳሌ ብቻ ማጠቃለሉን መርጫለሁ። የአፕል ስቶክ ዋጋ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በ50 ሺሕ በመቶ እጥፍ በማደግ የላቀ ስኬትን ለማስመዝገብ በቅቷል። በአጭሩ በ1997 10 ሺሕ ዶላር ኢንቨስት አድርገው ቢሆን አሁን ያለዎት ዋጋ 2.1 ሚሊዮን ዶላር በደረሰ ነበር። ታዲያ ይኸው ካምፓኒ ከሲልከን ቫሊ አስደናቂ ስኬቶች አንዱ ለመሆን መብቃቱ አንዳለ ሆኖ ዋና መሥሪያ ቤቱን መገኛው ባደረገበት ኩፐርቲኖ ካስገነበው የጠፈር መንኩራኩር ከሚመስለው ክብ ሕንፃ ውስጥ ካለው ቦታ ውስጥ 80 በመቶው ድርቅን መቋቋም በሚችሉ አረንጓዴ ዛፎች እና በሰው ሰራሽ ማራኪ ኩሬ የተሞላ ነው።

በእያንዳንዱ ኩባንያ ዙሪያ ዳሰሳ ለማቅረብ በጭራሽ በውስን ጊዜ የማይሞከር መሆኑ ሳይዘነጋ በአሁኑ ወቅት ይህ አካባቢ በቆዳ ስፋቱ ከመላው አሜሪካ ይቅር እና ከካሊፎርኒያ ግዛት አንፃር እንኳን በጣም አነስተኛ ቢሆንም ሲሊከን ቫሊ ብቻውን የ3 ትሪሊየን ዶላር ዋጋ ያለውን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ይህም ከመቶ ሰባ በላይ አገራት ምጣኔ ሀብት የሚልቅ ነው። በሌላ በኩል ለማስቀመጥ ይህ የሳንፍራንሲስኮ ሰርጥ (ሲሊከን ቫሊ) እንደ አገር ተቆጥሮ ከሌሎች አገራት ኢኮኖሚ ጋር ቢወዳደር ከኔዘርላንድስ ቀጥሎ 19ኛ ደረጃ ይኖረዋል። በነገራችን ላይ በነፍስ ወከፍ ምርት (GDP per capital) ከተወሰደ ሲሊከን ቫሊ ሦስተኛው ትልቅ የነፍስ ወከፍ ምርት ባለቤት በመሆን ከዓለም የሦስተኛ ደረጃን እንዲይዝ ያስችለዋል።

የሲሊከን ቫሊ ምሥረታ ወደ ታሪካዊ የስኬት ታሪክ እንዲሸጋገር የበርካታ ተቋማትንና ግለሰቦችን የጋራ ጥረት መጠየቁ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ይሄንኑ አካባቢ የምድራችን ታላቋ የቴክኖሎጂ መዲና በማሰኘቱ ረገድ ድርሻውን በእጅጉ የላቀ ተቋማት እና ግለሰቦች የተለየ ቦታ ማግኘታቸው አልቀረም። በዚህ ረገድ በተለይ የትራንዚስተር ፈጠራ ባለቤት እና የኖቤል የፊዚክስ ተሸላሚ ዊሊያም ሸክሌ አንዱ ተጠቃሽ ነው። በተለይም በተቋም ደረጃ የሥመ ጥሩው የስታንፈርድ ዩኒቨርስቲም ለተግባራዊ ምርምር የላቀ ቦታን ከሚቸረው የትምህርት ክፍሉ ብቃት እና ችሎታ ያላቸውን በብዛት እንዲመረቁ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ለዚህ አካባቢ ማደግ የላቀ አስተዋፅዖ አበርክቷል። የተቋሙ አበርክቶት አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ሲሆን የጉግል መሥራቾች ቢሊየነሮች፣ የሄውሌት ፓካርድ (HP) የኮምፒዩተር እና የፕሪንተር አምራቾችን ፈጣሪዎች ጨምሮ ይህ ዩኒቨርስቲ ከሰባ በላይ ቢሊየነሮችን በሺሕ የሚቆጠሩ የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎችን ለማፍራት የቻለ ነው።

የሰሊከን ቫሊ በምስረታ ወቅት በተለይ ተማሪዎች ተመርቀው ከመቀጠር ይልቅ የራሳቸውን ድርጅት ይመሰርቱ ዘንድ በእጅጉ ይጥር እና ያበረታታ የነበረው የስታንፈርድ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ፍሬድ ሪክተርማን ‹‹የሰሊከን ቫሊ አባት›› በመባል ስሙ በበጎ ጎኑ ይወሳል።በተለይ በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የኢንዱስትሪያል ፓርክ በማቋቋም የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪውን ከዩኒቨርስቲው ጥናት እና ምርምር ጋር በማስተሳሰሩ ዓለማችንን እስከወዲያኛው የቀየሩ እና የዲጂታል አብዮት መሰረት የሆኑ በርካታ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ እንዲሁም እንደ አፕል፣ ጉግል፣ ሲስኮ ፌስቡክ የመሳሰሉት ተቋማት የስታንፈርድ መገኛ አካባቢን ዋነኛ መቀመጫቸው እንዲያደርጉ መሰረት በመጣል ለተቋሙ፣ ለሐገሩ ሆነ ለዓለማችን የላቀ አስተዋፅዖን አበርክቷል። በግሉም በርካታ የቴክኖሎጂ ተማሪዎችን ለላቀ ስኬት ከማብቃቱ ጐን ለጐን የ36 ሳይንስ ፈጠራ ባለቤት ለመሆን የቻለ ነበር።

የቤት ሥራችን እና መጪው ዘመን
ዓለማችን በተለይ በእንግሊዝ በ1780 ከተነሳው የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት ተነስቶ አሁን ላይ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ላይ ደርሷል። ይሁን እንጂ በአገራችን ያለው ኢኮኖሚ ገና ከጥማድ በሬ እርሻ አለመላቀቁ እሙን ነው። በመሆኑም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ቀርቶ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ተወዳዳሪ ለመሆን ብዙ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቃል። ይሄ እንዳለ ሆኖ ግን በተለይ በአንፃራዊነት በፍጥነት ለማደግ ቴክኖሎጂ የላቀ ሚና ያለው በመሆኑ – መንግሥት ሊሰጠው ከሚገባው ትኩረት እና ድጋፍ ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው ለፈጠራ ይተጉ ዘንድ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በበርካታ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ተመራማሪዎቻቸውን ለውጤት የሚያበቁባቸው የሳይንስ ፓርክ ወይንም የጥናት እና ምርምር ፓርክ አላቸው። በኢትዮጵያ የቱ ዩኒቨርስቲ ይሄንን ሞክሮ ያውቃል? እነዚህ ማዕከላት በተለይ ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሥራ ፈጣሪዎች፣ ለግል ተቋማት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ የላቀ ችሎታ ላላቸው ግለሰቦች ጭምር አገልግሎት በመስጠት የዕውቀት እና ምርምር እንዲስፋፋ በማስቻል የፈጠራ ውጤቶች በፍጥነት ለውጤት የሚበቁበትን መላ በመቀየስ የሚታወቁ ናቸው። በመሆኑም በተለይ ለህንፃ ግንባታ ብቻ የላቀ ትኩረት በመቸር የትምህርት ጥራቱ የቀነሰበትን ሁኔታ ከመለወጡ ጐን ለጐን በየዩኒቨርስቲው የሳይንስ ፓርኮችን በሚገባ ማስፋፋቱ ተገቢ ነው። በዚሁ አጋጣሚ የስታንፈርዱ ዩንቨርስቲ የሳይንስ ፓርክ አፕልን ጨምሮ ለበርካታ ዓለማችንን ለለወጡ የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መነሻ መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ነው።

ከሞላ ጐደል ካላቸው ውስን ካፒታልም ላይ ቢሆን የላቀ የፈጠራ ችሎታ ላላቸው ወገኖች የተመጠነ የመነሻ ካፒታልን ለመስጠት የሚደፍሩ ኢንቨስተሮች እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የመንግሥት ፖሊሲና የትኩረት አቅጣጫም የዲጂታል (የመረጃ) ዘመን ሊያስገኝ የሚችለውን የላቀ አቅም በአግባቡ አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ የአሠራር ሁኔታዎችን የሚያዳብሩበት እና የሚያስፋፉበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ሊያተኩር ያሻዋል። ይህንን በማድረግም ሲሊከን ቫሊ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሰፊ አስተዋፅዖን እያደረጉ ያሉን ኢትዮጵያውያን የሥራ እና የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የመሰሉ የቴክኖሎጂ አዋቂዎች በብዛት በአገር ውስጥ ከማፍራት የሚያግደን ነገር አይኖርም።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here