በመልሶ ማቋቋም የደቡብ ክልል 18 ሕጻናትን ወሰደ

0
440
  • 13 የዲግሪ፣ 3 የዲፕሎማና 1 የሰርተፊኬት ምሩቃን በመልሶ ማቋቋሙ ከታቀፉት ውስጥ ይገኙበታል

በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በጎዳና የሚኖሩ ዜጎችን በማንሳትና ለመልሶ ማቋቋም ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ክልሎች እንዲወስዱ ጥያቄ ቀርቦላቸው ጥያቄውን ተቀብሎ 18ቱን የክልሉ ተወላጆች ደቡብ ክልል መውሰዱን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደሻው አበራ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ከጎዳና ልጆች ጋር ባደረግነው ውይይት “ያለምንም ዝግጅት ከጎዳና ተነሱ ካላችሁን እንነሳለን፤ ቀጣዩ ዕድላችን ከዚህ የባሰ ነው የሚሆነው” ብለውናል ያሉት እንደሻው፣ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍ ፖሊሲ መዘጋጀቱንና በቅርቡም ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አስተዳደሩ አብዛኞቹን ተቋቋሚዎች ወደ ክልል ለመመለስ ለሁሉም ክልሎች ጥያቄ ቢያቀርብም ክልሎች ለመቀበል ባለመፍቀዳቸው ውዝግብ ውስጥ እየገቡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ማስነበቧ ይታወሳል።

ከወር በፊት ከአዲስ አበባ ጎዳና አዳሪዎችን ማንሳት የተጀመረው በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስተባባሪነትም ጭምር ተነሽዎቹ እስከ 45 ቀናት በማዕከል አገግመው ወደ የተወለዱበት ክልል እንዲሔዱ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር የነገሩን እንደሻው፣ በአንዳንድ ክልሎች አካባቢ የተፈናቃዮች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ከእኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ላለመስጠት ማነቆ ሆኖባቸዋል ብለዋል። እስካሁን በተካሔደው ዘመቻ ትግራይ 26 እና ደቡብ 18 ሰዎችን ወስደዋል።

በዚህም 50 ሺሕ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማንሳት ያቀደው ከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያ ዙር እስከ አምስት ሺሕ ለማንሳት እቅድም ይዞ ነበር። በዚህም ሥራው በተጀመረ በቀናት ውስጥ ይነሳሉ ተብሎ የታቀደው 2 ሺሕ የጎዳና አዳሪዎች ቢሆንም ቁጥሩ ወደ 3 ሺሕ አሻቅቧል። ይህም ሆኖ ተነሽዎቹን በማዕከላት ይዞ የሚገኘው አስተዳደሩ ወደ ክልሎች መመለስ ያለባቸውን ሰዎች ለመላክ ለክልሎች በደብዳቤ ቢጠይቅም አዎንታዊ ምላሽ ያገኘው በኹለቱ ክልሎች መሆኑን አስታውቋል።

ከእነዚህ ሦስት ሺሕ ተቋቋሚዎች ውስጥ በእድሜ መግፋት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት የማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና ሕጻናት ወደ ክልሎች እንደማይላኩ ለአዲስ ማለዳ ያሳወቁት እንደሻው፣ በአረጋውያንና ሴቶችና ሕጻናት ዙሪያ ከሚሰሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ተነጋግረው አንዲወስዷቸው ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች የነበሩና አሁን በመልሶ ማቋቋም ውስጥ የተሳተፉ ወጣቶች አሉ ወይ? በማለት አዲስ ማለዳ ላቀረበችላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት እንደሻው፣ 13 የዲግሪ፣ 3 የዲፕሎማና 11 የሰርተፊኬት ምሩቆች መኖራቸውን ነግረውናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here