የኢኤምኤስ ደንበኞች በዝርፊያ ተማረሩ

0
627

በኢኤም ኤስ ከተለያዩ የዓለም አገራት እና ከአገር ውስጥ የሚላኩላቸውን እቃዎች እየተዘረፉ መቸገራቸውን ተገልጋዮች አስታወቁ። ከኹለት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ፖሰታ አገልግሎት ቅጥር ግቢ ውስጥ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ከተላከልን እቃ ጎድሎ ተሰጥቶናል በማለት አማረዋል።

አንድ ተገልጋይም ከውጪ አገር ከተላኩለት ኹለት ሻንጣዎች አንዱ ጠፍቷል ተብሎ እንደነበር እና ከብዙ መመላላስ በኋላ እንደሰጡት፤ ነገር ግን ሻንጣው ግማሽ ሆኖ እንደተሰጠው ተናግሯል። ያጋጠመውን ችግርም እደላውን ለምትሰራው ግለሰብ ቢያሳውቅም እቃውን ሲረከብ ከተላከለት ኪሎ ጋር በማነጻጻር መቀበል እንደነበረበት እና ከዚህ በኋላ ልትረዳው እንደማችል ገልጻለታለች።

በተጨማሪ ከ20 ቀናት በላይ እቃቸው ሳይላክ የቆየባቸው ግለሰቦችም ከመደበኛው የፖስታ ዋጋ ብዙ እጥፍ ከፍለው የሚጠቀሙት ለፍጥነቱ ቢሆንም ግልጋሎቱ ተቃራኒ እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ችግሮቹን ከሚያባብሱት ምክኒያቶች መካከልም የየቅርንጫፎቹ ስራ አሰኪያጆች ለቅሬታ ቅርብ ካለመሆናቸው ባሸገር በቢሮ ውስጥም አይገኙም።
ዝርፊያው ስልታዊ መሆኑን የሚናገሩት ደንበኞቹ ከተላከላቸው እቃ ጋር ተመሳሳይ ኪሎ ባለው እቃ በመቀየርም ለአቤቱታ የማይመች በማደረግ ዝርፊያዊቹ እንደሚከናወኑ ይናገራሉ።

ለምርቃቷ በአንድ ወቅት ከእስራኤል አገር አልባሳት ተልኮላት እንደነበረ የምትናገረው ወጣትም የተላኩላትን ልብሶች በቀለም እና በቅርጽ በሚመሳሰሉ ያረጁ ልብሶች ተቀይረው እንደደረሷት ትናገራለች። ይህንን ስልታዊ የእምነት ማጉደል ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ጭምር አስባ እንደነበር ጭምር የምትናገረው ወጣት ነገር ግን ጉዳዩ ማስረጃ የማይገኝለት በመሆኑ ሐሳቧን መቀየሯን ትናገራለች።

ሌላው ወሳኝ የሆኑ ዶክመንቶች እና ፎቶዎች እንደጠፉበት የሚናገረው ጎልማሳም ደጋግሞ ቢመላለስም መፍትሔ ለማግኘት መቸገሩን ገልጾ ጥፋቱ ከዝርፊያ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን ከተዝረከረከ አሰራር ጋርም እንደሚያያዝ ይገልፃል።
አዲስ ማለዳ በዋና መሥሪያ ቤቱ ባደረገችው ቅኝትም መልዕክቶች ከመጋዘን ወደ ማከፋፈያ መኪኖች በሚጫኑበት ወቅት ከርቀት በመወርወር የሚደረግ መሆኑን ታዝባለች። እጅግ በተዝረከረከው መጋዘን ውስጥም የተቀመጡት ትልልቅ መልዕክቶች መካከልም ማሸጊያቸው የተቀደዱ መልዕክቶች ይታያሉ። የድርጅቱ ሠራተኞችም አንድም ማሸጊያቸው የላላባቸውን ለማጠንከር እና የተከፈቱትን መልሶ ለመዝጋት በፕላሰተር ሲያጠብቁ ይታያሉ።

በፖስታ ቤቱ ዋና መስሪያ ቤት በቋሚነት ከሚላኩ እቃዎች መካከልም የጫት ምርት ዋናው ሲሆን ምርቱን የሚያሽጉ ብዛት ያላቸው ወጣቶችን በዋናው መላኪያ አዳራሽ ወለል ላይ መመልከት የተለመደ ነው። በዓለም ላይ የአየር ትራንስፖረት መቀላጠፍ እንዲሁም ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂ መሻሻል ጋር በተያያዘ ፋይዳው እተየተዳከመ የመጣወው የፖስታ አገልግሎት በተለይ ለንግድ ዓላማዎች እና ሰነዶችን ለመቀያየር አሁንም መተኪያ ያልተገኘለት አማራጭ መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ማለዳ ከላይ ያለው ዘገባ ከተሠራ በኋላ ባደረገቸው ቅኝት በዋና መስሪያ ቤቱ የኢኤም አስ ዴስክ ላይ ያሉ ሠራተኞቹን በሙሉ በአዳዲስ እና ወጣት ሠራተኞች መተካታቸውን ተመልክታለች። ይህንንም ተከትሎ ቅኝቱ በተደረገ ቀን እንደተመለከተችው ቅሬታ ያላቸውን ግለሰቦች ቁጥር የቀነሰ ሲሆን ለዘርፉ ቅርበት እንዳላቸው ሰዎች አስተያየት ግን እንዲህ ዓይነት ሪፎር ሞች ዘላቂ ለውጥ እንደማያመጡ ይናገራሉ።

አዳዲሶቹ ሠራተኞች ከነባሮቹ የማጭበርበር ስልቶቹን እስኪማሩ የሚዘልቅ ሲሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥብቅ ቁጥጥር እና ጠንካራ የዲሲፕሊን እርምጃዎች እስካልተወሰዱ ዝፊያው በጥቂጥ ጊዜ ውስጥ እንደሚያገረሽ ይናገራሉ።
የድርጅቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊን በቢሯቸው ማግኘት አልተቻለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here