የኅትመት መገናኛው ጉዞ ውጣ ውረድ

0
1005

ከአንድ ከፍለ ዘመን ጥቂት ዓመታት የዘለለው የኢትዮጵያ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ጉዞ በበርካታ አባጣና ጎርባጣ መንገዶች ላይ ተጉዞ ዛሬ ላይ ደርሷል። የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ዘርፍ በዚህ የጊዜ ርዝመት ያሳለፋቸውን መልካም አጋጣሚዎች እና የተጋረጡበትን ተግዳሮቶች፣ መንግሥት ከሰጠው ትኩረት፣ ተግባር ላይ ከዋሉት ሕጎች እና ከሙያተኞች ሥነ ምግባር አንፃር የዘርፉን ባለድርሻዎች በማነጋገር እና ጥናቶችን በማገላበጥ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ዘመነ ኢሕአዴግ ድረስ በመንግሥታዊ ጭቆና ውስጥ የወደቀና በንስር ዓይን ሥር የኖረ ዘርፍ ነው። በኢትዮጵያ ከአወዳሽ ሚዲያው ውጭ ያለው ፕሬስ እንዳይወቅስ እና እንዳይከስስ፣ ሕዝብን እንዳያነቃና ለመብት ጥያቄ እንዳያነሳሳ፣ መረጃ እንዳያሰራጭና ለውጥ እንዳይፈጥር መንገዱን የእሾህ ጋሬጣ ሲያበጁበት በኖሩት ገዢ መንግሥታት ሳቢያ ከዳዴ ጉዞ ፈቅ ሳይል አንድ ክፍለ ዘመን ይዟል።

በተለይም የኢሕአዴግ መንግሥት በአገሪቱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ በሆነበት ማግስት ሊያብብ የጀመረውን ፕሬስ በክፉ ዱላ ከመታውና ጋዜጠኞችን ማዋከብ የኅልውና ጥያቄ አድርጎ ከተነሳ ወዲህ፣ ይህ የፕሬስ በተለይም የነጻው ፕሬስ ዘርፍ ʻየደፈረ ብቻʼ የሚገባበት ʻቀይ ዞንʼ ሆኖ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል።

የመጀሪያው ጋዜጣ ‘አእምሮ’ ከእጅ ጽሑፍ ወጥቶ በማሽን መታተም ከጀመረ (ከ1902 ወዲህ) እነሆ 109 ዓመታት ሆነዋል። ከዚያ በኋላ ‘ብርሃንና ሰላም’ የተባለው ጋዜጣም የተወሰነ ጊዜ መዝለቅ ችሎ ነበር። እስካሁን ድረስ መዝለቅ የቻለው እና “አዲስ ዘመን” የሚባለው በመንግሥት የሚታተም ጋዜጣ ሆኖ ለአንባቢያን የደረሰው በ1941 ነው። የዐፄ ኃይለሥላሴንና የደርግን ዘመን ተሻግረው አሁን የኢሕአዴግ ዘመን ድረስ የዘለቁትን እነ አዲስ ዘመንን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጦችን ጨምሮ፥ በ1902 አሀዱ ተብሎ በዘመናዊ ኅትመት የተዘጋጀው ጋዜጣ ዕድገት በ2011 መድረስ የቻለበት የብዛት ጣሪያ በጣም ጥቂት ነው።

ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በተገኘ መረጃ መሰረት ከየካቲት 2001 እስከ 2007 ድረስ በየጊዜው የሚወጡት ኅትመት ብዙኀን መገናኛዎች ምዝገባ የምስክር ወረቀት ያገኙ ነጻ የኅትመት ሚዲያዎች ብዛት ጋዜጣ 108፣ መጽሔት 203 የነበሩ ቢሆኑም፥ ሁሉንም ነገር ተቋቁመው እስካሁን መቆየት የቻሉት ግን 12 ነጻ (የግል) ጋዜጦችና 10 መጽሔቶች ብቻ ናቸው ። ኢሕአዴግ በግንቦት 1983 ወደ ሥልጣን ሲመጣ ካደረጋቸው መልካም ነገሮች አንዱ በሐምሌ ወር የሽግግር ቻርተር በማውጣት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ቢያንስ በሕግ ደረጃ ማስፈሩ ነው። ይህንን ተከትሎ የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ሕግ በመነሳቱ የነጻ ፕሬስ መንፈስ እንዲቀሰቀስና መስኩ ብዛት ያላቸው ተዋናዮችን እንዲያሳትፍ መሠረት ጥሏል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ወርቃማ ዘመን
ወደ ገበያው ብቅ ያሉ እንደ ጋዜጣና መጽሔት ያሉት የፕሬስ ውጤቶች ምንም እንኳን በአብዛኛው ሊባል በሚችል መልኩ በባለሙያ የሚሠሩ ባይሆኑም፥ ለአንባቢው ግን በምርጫ ቀርበውለት ነበር። 1985 የፕሬስ አዋጅ ቁጥር 34/85 ሲደነገግ “ወርቃማ ዘመን” ተብሎ የሚጠራው የፕሬስ አብዮት በኢትዮጵያ ፈነዳ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ወርቃማ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ቀደሞም ያልነበረ ኋላም ያልተደገመ የኅትመት ውጤቶች ቁጥር የተመዘገበው በ1985 እና 1986 ነበር።

በ1985 በኢትዮጵያ ውስጥ 28 ጋዜጣና 65 መጽሔቶች የነበሩ ሲሆን፥ በ1986 ደግሞ ይህ ቁጥር አሻቅቦ 79 ጋዜጣና 38 መጽሔቶች በድምሩ 117 የኅትመት ውጤቶች ገበያውን አጥለቀለቁት። በጊዜው የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ የገነነበት፣ ሕዝቡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንጊዜውም በላይ ያገባኛል ያለበት ወቅት ስለነበር፥ አዲስ ከነበረው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ተዳምሮ ዛሬ ላይ መልሶ የሚደገም የማይመስል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተንሰራፋ። ይህን ተገን ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሬስ በተለይም የግሉ ፕሬስ በመንግሥት አሠራሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በማኅበረ ምጣኔ ሀብት ተሳትፎውም የጎላ ድርሻ መያዝ ጀመረ። አሳታሚዎች በተለያየ አቀራረብ ይዘዋቸው ብቅ ከሚሉት የፕሬስ ውጤቶች ከሲሦ በላይ የሆኑት የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ነበሩ። ጊዜው የጋዜጦች ብቻ ሳይሆን የመጽሔቶች አብዮትም የፈነዳበት ነበር።

የመንግሥት ፕሬሶች ጭልጥ ወዳለ አፍቃሬ መንግሥት ግብር ሲገቡና የሕዝቡን ሕይወት ረስተው የፓርቲ ፖለቲካ ማናፈሻ መድረኮች ሲሆኑ፥ በተቃራኒው የግሉ ፕሬስ የመንግሥት ፕሬሶች በማይነኩት ችግሮችና ስህተቶች ላይ ብቻ አተኩሮ ሲሠራ፣ የፕሬስ ‘ተአማኒነት’ ድንበር የቱ ጋ እንደሆነም ለማወቅ እስኪያስቸግር ድረስ ተደባለቀ። ሕዝቡ የሰለቸውን የራዲዮ እና ቴሌቪዠን ፕሮፓጋንዳ ሽሽት በነጻው ፕሬስ መረጃ ጥላ ሥር ራሱን መቅበሩ በአዎንታዊ ጎኑ የማንበብ ባሕልን አዳብሮ የጋዜጣና መጽሔት ኅትመት እንዲሰፋ ቢያደርግም፥ በዚያው ልክ በነጻው ፕሬስ በተቃውሞ እና ክስ ላይ ካላተኮረ በቀር፣ በሚዛናዊነት የሚሠራውን ሥራ የማግለል እና የመፈረጅ ባሕል እንዲሰፍን ምክንያት ሆነ። ቲሞቲ ስፔንስ የሚባል በ1994 እስከ 1998 ድረስ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ትምህርት ይሰጥ የነበረ የጋዜጠኝነት ባለሙያ እንደሚናገረውም የኢትዮጵያ ፕሬስ በኹለት ጫፍ ተይዞ በአንባቢ ምርጫ የሚጎተትና የራሱን አጀንዳ መቅረፅ እንዳይችል ተፅዕኖ ውስጥ የወደቀ ፕሬስ እንዲሆን ምክንያት ሆነ።

የፕሬስ የቁልቁለት ጉዞ
የፕሬስ የቁልቁለት ጉዞ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር አድጎ የነበረው የኅትመት ውጤቶች ገበያ ማሽቆልቆል የጀመረው ከወረቀት ዋጋ መወደድ እና ከሶሻል ሚዲያው መስፋት፣ እንዲሁም ከአሳታሚዎች አቅም ማነስና ከማስታወቂያ እጦት ጋር በተያያዙ ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያቶች ብቻ አለመሆኑን በተደጋጋሚ መድረኮች የፕሬስ ባለሙያዎቹም ይሁኑ ጉዳዩን የሚያጠኑ ምሁራን የሚገልጹት ሐቅ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ኅትመት ዘርፍ ውስጥ የግልና የመንግሥት ጋዜጦች እና መጽሔቶች ተደምረው ቁጥራቸው ወደ 22 ባሽቆለቆለበት ሁኔታ፣ ብዛት ያላቸው በአገሪቱ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣትና ጤናማ ማኅበረ ፖለቲካ ለመገንባት አቅም የነበራቸው መጽሔቶች ከገበያው እንዲጠፉ ተደርገው የኅትመት ዘርፉ ቀጭጮ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ተከብሯል ብሎ መናገር አባይነት ይሆናል የሚሉት የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዘካሪያስ ስንታየሁ፣ ዘርፉ እየሞተ በዝምታ ማለፍ የሰዎችን የዴሞክራሲ መብት እንደማፈን ይቆጠራል ባይ ናቸው።

መንግሥት የፕሬስ ነጻነትን የሚያረጋግጡ ሕጎች ማውጣቱንና፣ እነዚህ ሕጎች ለብቻቸው በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነት መከበሩን እንደሚያረጋግጡ ደጋግሞ ቢናገርም፥ በተቃራኒው ኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ አፋኝ አገር መሆኗን ʻሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስʼ በተባለ ተቋም በ2018 (እ.ኤ.አ) ዓለም ዐቀፉ የፕሬስ ፍሪደም መዘርዝር ላይ ከ180 አገራት ያገኘችው 150ኛ ያሽቆለቆለ ደረጃ ብቻ አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል። የጥናት ሰነዱ “… [ኢትዮጵያ] ለፕሬስ ነጻነት እና ጋዜጠኞች ከአስቀያሚዎቹ አገራት አንዷ ናት።” ይላል።

በ1987 ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኀን የመረጃ ነጻነት አዋጅ በ2000 ታውጆ በአንፃራዊነትም ፕሬሱ የሕግ ማዕቀፍ ተቀምጦለት ባለበት ሁኔታ፥ ዘርፉን ወደ ቁልቁለት መንገድ የነዳው ምንድነው የሚለውን መጠየቅ ግድ ይሆናል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርና የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር አስተባባሪ የሆኑት ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) የ1997 ምርጫን ተከትሎ በአገሪቱ የተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ኢሕአዴግ ከየትኛውም ነገር በላይ ፕሬስንና ብዕርን እንዲፈራ ስላደረገውና ለዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ መሠረታዊ አነሳሽ ፕሬሱ ነው የሚል ጭፍን ድምዳሜ ላይ ስለደረሰ የተለያዩ አፋኝ ሕጎች በማውጣት የፕሬሱን አቅም ለመሰባበር ሙከራ አድርጓል፤ ተሳክቶለታልም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህንንም ተከትሎም ጋዜጠኞችን በአገር መክዳት ወንጀል ወህኒ መወርወር፣ ፀረ ሽብርተኛነት ሕግ በማውጣት ሐሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሚታትሩና በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ የሕዝብ መደመጥንና ጥቅምን ለማረጋገጥ መረጃን በማዳረስ ሙያዊ ግዴታቸውን የሚወጡ ጋዜጠኞችን በመክሰስ ወደ እስር አውርዷል።

መንግሥት በፕሬሱ ላይ ከሰነዘረው ቀጥተኛ ጥቃት ባሻገር ፕሬሱን በኢኮኖሚ እንዳይዳብርና በኪሳራ እንዲከስም ማስታወቂያ የሚሰጡ ድርጅቶችን በማስፈራራት፣ ማተሚያ ቤቶችን እንዳያትሙ በመከልከል፣ የኅትመት እና ወረቀት ዋጋን በማናር እና የመጽሔት እና ጋዜጦችን ስርጭት ለመግታት የኅትመት ውጤቶችን ሰብስቦ እስከማሰር የደረሱ ተግባራትን መከናወናቸውን የሚያስታውሰው ዘካሪያስ፥ ሚዲያው እንደኢንቨስትመንት እየታየ ባለመሆኑም ለአደጋ መጋለጡን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የጋዜጣ ማሳተሚያ ዋጋ
በደካማ አገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ የሚዳክረው አንድ ለእናቱ ማተሚያ ቤት በድንገት እስከ 45 በመቶ የሚደርስ የኅትመት ዋጋ ጭማሪ በዚህ ዓመት አድርጓል። ይህ ጭማሪ በ10 ዓመት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ጭማሪው ወትሮውኑም ከእጅ ወደ አፍ ገቢ ያላቸውን ጋዜጦች በፍጥነት ከገበያ ሊያስወጣ እንደሚችል የሪፖርተሩ ዘካሪያስ በገፊ ምክንያትነት ያነሳሉ።
የጭማሪው ከፍተኛነት የጋዜጣ አሳታሚዎችንና አዘጋጆችን ክፉኛ እንዳሳሰባቸው የገለጹት ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው የኅትመት ዋጋ ምክንያት ጋዜጦች እስካሁን ሲሸጡ የቆዩበትን ዋጋ በራሱ ውድ አድርጐት መቆየቱን አስታውሰው፣ በዚህ ዋጋ ላይ ተጨማሪ ዋጋ መጫን ካለው የኅብረተሰቡ አጠቃላይ የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ለጋዜጦች ኅልውና ስጋት ነው ብለዋል። በተጨማሪም፣ “የግሉ ፕሬስ ራሱን በራሱ እንዲገድል እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል” በማለት አዝማሚያውን ለአዲስ ማለዳ ይገልጹታል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጋዜጦችና መጽሔቶች አከፋፋይ፣ የኅትመት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የአንባቢውም ቁጥር በዛው ልክ መቀነሱን መታዘባቸውንና አንባቢውም የሚፈልገውን ገዝቶ ለማንበብ የአቅም ውስንነት ስላለበት አንድ ብር ከፍሎ አራትና አምስት የሕትመት ውጤቶችን አንብቦ እንደሚሔድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለአንዳንድ ሸቀጦች የሚደረገው ድጐማ ለሚዲያ ኢንዱስትሪው መደረግ እንደነበረበትና በብዙ አገሮችም ለሚዲያ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ʻካፒታልʼ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ግሩም አባተ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። “የኢኮኖሚ ጫና በማድረግና ስልታዊ በሆነ መንገድ እንድናቆም ከሆነ የሚፈለገው የሕዝቡን መረጃ የማግኘት መብትም ችግር ውስጥ ይከተዋል” ሲሉ ስጋታቸውን አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም ባለ 96 ገጽ የእሑዱን ሪፖርተር ባለቀለም ጋዜጣ ለማሳተም 148 ሺሕ ብር ገደማ ይጠይቅ የነበረው የኅትመት ዋጋ በ2003 ተግባራዊ በሆነው አዲስ የዋጋ ተመን መሠረት ወደ 214 ሺሕ ብር ገደማ አሻቅቦ እንደነበር ዘካሪያስ ለአብነት አንስተዋል። ልዩነቱ ከ65 ሺሕ ብር በላይ በመሆኑም ጭማሪውን 44 ነጥብ 4 በመቶ አድርሶታል።

ፍሬው አበበ የኅትመት ዋጋ ጭማሪውን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ጊዜ በጋዜጦች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ያለው በጊዜ አለመውጣትና የኅትመት ጥራት ችግር መሆኑን ገልጸው፥ ድርጅቱ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ሳይቀርፍ ዋጋ መጨመሩ የኪሳራ ኪሳራ ነው ብለዋል። የጋዜጣ በሰዓቱ አለመውጣት ችግር በገንዘብ የማይተመን መሆኑን የጠቆሙት ፍሬው፥ በዚህ ላይ የኅትመት ዋጋ ጭማሪ ማድረግ ጋዜጦችን ከገበያ ውጭ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ሚዲያውን ጠንካራ የቢዝነስ ኃይል ወይም ኢንዱስትሪ እንዲሆን አላደረገውም የሚሉት ግሩም፥ ሚዲያው ወደ ኢንዱስትሪ ባለመምጣቱ፣ የግል ባለሀብቶች የሚዲያው ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

ሌላው ራሱ ሚዲያው መቀናጀትና ጥምር ኩባንያዎች (‘ጀይንት ቬንቸር’) መፍጠር አለበት ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን መምህሩ መኩሪያ መካሻ (ፕ/ር)። ጥምር ኩባንያዎች በመፍጠር፣ የጋራ ማተሚያ ቤቶችን በማቋቋም፣ የጋራ የሽያጭ ሥራዎችን መሥራትና ማስታወቂያዎችን በማግኘት ተቀናጅተው በመሥራት ብዙ አገሮች ማደጋቸውን በምሣሌነት በማስቀመጥ አንዱ ከመገናኛ ብዙኀን ተቋማትና ከባለሀብቱ በኩል የሚታይ ክፍተት መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግሥትና የሚዲያ ሕጎች
“ትልቁ ነገር የሚጠበቀው ከመንግሥት ነው” የሚሉት መኩሪያ፥ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ክንድ ያለው፣ ፈርጣማ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሕጎች፣ በተለይ ከሚዲያ ጋር የሚተሳሰሩ ሕጎች እጅግ በጣም አሳሪዎች ናቸው። የሚዲያ ሕግ 590/2000ን ብናየው፣ የኢንፎርሜሽን እና መረጃን የማግኘት መብት የሚለው ነገር በራሱ ኹለት የተለያየ ነገር ነው። ያ ነገር በሕዝብ ግንኙነቶች ሥር እንዲወድቅ ነው ያደረገው። ያ ሕግ፣ ጋዜጠኛው ከአርካይቭ መረጃን እደሚያገኝ ዓይነት አድርጎ የሚያስቀምጥ ነው ሲሉ እንከኑን ይጠቁማሉ።

የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የኢትዮጵያ ሕግ የተቀበላቸው ገደቦች፣ የመገናኛ ብዙኀን ሕጎች የተበታተኑ መሆን፣ የተቆጣጣሪ ተቋማት አወቃቀር፣ ፍትሐዊ የማስታወቂያ ክፍፍል ላይ ችግሮች እንደነበሩባቸው መኩሪያ ያስታውሳሉ። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉት ሕጎች መለወጥ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ። ሌሎችም ሕጎች ከኤንጂኦና ከሲቪል ሶሳይቲ፣ ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተጓዳኝ ሕጎች አሉ። እነዚህ ሕጎች መሻሻልና መቀየር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በዚህ ላይ መንግሥት ሕጋዊ መሠረቱን መጣል እንዳለበት የሚያስታውሱት ተሻገር እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱ የሆነ የሚዲያ ፖሊሲ፣ የኮሚዩኒኬሽን ፖሊሲ የለውም። አሁን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቃል በገቡት መሠረት እንደዚህ ዓይነት ለውጦች እንዲኖሩ ያስፈልጋሉ። ይሔ ለውጥ ከመጣ መሠረት ይጥላል የሚል ተስፋ አለ ብለዋል።
መኩሪያ መንግሥት በሚዲያ ላይ የተዘረጉትን ረጅም እጆች ማንሳት እንደሚኖርበተት ገልጸው፥ መገናኛ ብዙኀን የራሳቸው ሕግና መመሪያ አላቸው። ያንን ጠብቀው በነጻነት የመዘገብ፣ መረጃ የማግኘት መብታቸውን ተጠቅመው መጓዝ ይኖርባቸዋል ሲሉም ጠቁመዋል።

የሙያተኞቹና የሚዲያው ሚና
መኩሪያ ሙያተኞቹ ዝም ብለው በመንግሥት ቦይ ውስጥ፣ ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ ብቻ የሚራመዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ጋዜጠኛው ቀድሞ መሔድ፣ መገኘት ነው ያለበት። ቀድሞ ሔዶ ሕዝቡን ለአንድ ለውጥ፣ ዴሞክራሲያዊ ዕድገት ማድረስ መቻል ይኖርበታል ሲሉ ይመክራሉ።

ሚዲያው ተቺ መሆን አለበት። ዝም ብሎ ከፀሐይዋ ወጣችና አወዳሽ ዓይነት ጋዜጠኝነት ወጥቶ ተቺ፣ አስተማሪና መካሪ ከመሆን ባሻገር የወደፊቱ አቅጣጫ ማመላከት ይጠበቅበታል ያሉት መኩሪያ፥ ይህም ተደራሲዎቹ እንዲበዙ በማድረግ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ እንዲችል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ተፅዕኖ ውስጥ መውደቁን የሚናገሩት ተሻገር በበኩላቸው፣ ይሄንን ተፅዕኖ አልፎ መሔድ መቻል እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። “እርግጥ ተጓዳኝ የሆኑ፣ ለምሳሌ የማተሚያ ቤት ችግሮች አሉ። የስርጭት ችግሮች አሉ። እነዚህ መፈታት መቻል አለባቸው” ሲሉም ያስታውቃሉ።

በ1984 ይወጡ የነበሩ ካርቱኖች አሁንም እየወጡ መሆናቸውን የሚያስረዱት ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) “ከትዝታዎቻችን መፋታት አልቻልንም። የፖለቲካ አቋማችን ሁሉ እንደነበረ ነው። ወገንተኝነታችን በጣም ይታያል። ሚዛናዊነት በጣም ይጎለናል። እና አሁን መገናኛ ብዙኃን ብዙም ስለማይታገዱ፣ ተከሰው ፍርድ ቤት ስለማይቀርቡ ሁሉም ነገር የተሻለ ይመስለናል እንጂ፣ ሙያዊ ጋዜጠኝነት ለማካሔድ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ይመስለኛል” ሲሉ ሚዲያው ያለበትን ቁመና ያሳያሉ።
ሁሉም በየወገኑ የሚዲያ ውይይት እንደሚያካሒድ የታዘቡት መኩሪያ ለምሳሌ የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉና፣ የተወሰነ አካባቢ ፍላጎትን እናራምዳለን የሚሉት ለየብቻቸው ቁጭ ብለው በየራሳቸው እንደሚወያዩ አመላክተዋለል።

ከአንባቢው፣ ስርጭትና ሽያጩ ያሉበት ጫና
አራት ኪሎ አካባቢ በሳምንት አንድ ቀን እየመጡ የማንበብ የ19 ዓመት ልምድ እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ የነገሩት በየነ በትረ (ሻለቃ)፣ በ90ዎቹ አንድ ጋዜጣ ከአንድ ብር እስከ ኹለት ብር ስለነበር በዐሥር ብር ቆንጆ ነው ያልነውን አምስትና ስድስት ጋዜጣ ገዝተን ቤታችን እንገባ ነበር ይላሉ። ይሁን እንጂ ከ1997 በኋላ ጋዜጦችና መጽሔቶች በለመድነውና በምንፈልገው መልኩ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው የማንበብ ፍላጎታችንን እያዳከሙት መጡ፤ ዋጋቸውም ዕለት ከዕለት እየጨመረ ሲመጣ ከመግዛት ወደ ተከራይቶ ማንበብ ተሻግረናል ብለዋል።

የይድረስ ይድረስ የሚታተሙ በርካታ የኅትመት ውጤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት በየነ፣ በእነሱ ምክንያት ለሦስት ዓመት ጋዜጣና መጽሔት ማንበብ አቁመው እንደነበር በማስታወስ የኅትመቶች የጥራት ደረጃ የአንባቢውን ቁጥር በእጅጉ ቀንሶታል ብለው እንዲገምቱ አድርጓቸዋል።

ኅብረተሰቡ ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ የሚነግረን ጋዜጣና መጽሔት በማዞር ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ግሩም የትነህ፣ በርካታ አንባቢዎች ጋዜጦችንና መጽሔቶችን አንብበው ከመመዘን ይልቅ ሥም ያላቸውን ብቻ እንደሚገዙና እንደሚያነቡ ያስረዳል። በርካታ ጥራት ያላቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች በተጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚቆሙ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳው ግሩም፣ ተነባቢ የኅትመት ውጤቶች በዚህ ምክንያት ከገበያ መውጣታቸውን ይናገራል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ አከፋፋዮች የራሳቸው መጽሔት ያላቸው በመሆኑና የነርሱን ብቻ በብዛት እንድንሸጥላቸው ስለሚፈልጉ አዳዲስ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን በብዛት እንዳንይዝ ጫና ያደርጉብናል ሲል ሌላውን የችግር ምንጭ ያሳያል። “አንዳንድ ሰው የሱን ብቻ ለቅሶ እንድታለቅስለት ይፈልጋል” ያሉት መኩሪያ፥ ይህም ጋዜጠኛውን ተጎታች እንዲሆን እንደሚያደርገው ገልጸው፣ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ለመቅረፍ ደግሞ ጋዜጠኛው ቀድሞ መገኘት እንዳለበት ይናገራሉ፤ “ኅብረተሰቡም ሚዲያውን በተጓዳኝ መርዳት መቻል አለበት” ሲሉም ይመክራሉ።

ሌላው ችግር የማንበብ ባሕላችን ደካማ መሆን ነው። አሁን ደግሞ የሶሻል ሚዲያው በላዩ ላይ ተጨምሮ፣ ያለው ጫና ብዙ ነው። ስለዚህ እነዚህ በጣም ውጥንቅጥ የሆኑ ችግሮች፣ በእነዚህ ጥልፍልፍ ጉዳዮች የታሰረ ሚዲያ እንዳለን የሚያወሱት ተሻገር ይህም ሚዲያ በተረጋጋ መልኩ እንዲንቀሳቀስ፣ የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ተቋማትን፣ የመንግሥት አካላትን፣ ባለሙያንና ማኅበረሰብን እንደሚፈልግ ይጠቁማሉ።

ምን ይደረግ?
በአሁን ሰዓት መገናኛ ብዙኀን ኹለት ፅንፍ ያላቸውን አንድ ላይ በማወያየት፤ ቅራኔያቸው እርስ በርስ የሚታረቅ ነው? ወይስ ምን የጋራ ትርጉም ልናመጣ እንችላለን? በሚለው ላይ መወያየት እንዳለባቸው መኩሪያ ይመክራሉ። አሁን ሁሉም በየወገኑ ነው ውይይት የሚያካሒደው፤ ያ ደግሞ ውይይት አይደለም። በአንድ ጉዳይ ላይ ልዩነት ሳይኖረን ቀርበን ካልተከራከርን የምናመጣው ብዙም ልዩነት አይኖርም። እርስ በርስ ግን በተለያየ ጎራ ውስጥ ነን የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች ተሰብስበው ሲወያዩ፣ አንደኛ ልዩነታቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣሉ፤ በልዩነታቸው ውስጥ ደግሞ የጋራ የሚያደርጋቸውስ ነገር ምንድን ነው? ያን የጋራ ትርጉም እንዴት አስፍተን እንዴት በጋራ መፍታት እንችላለን? የሚል ነው በማለት መፍትሔውን ያስቀምጣሉ። መገናኛ ብዙኃን ኅብረት ከሌላቸው ማደግ እንደማይችሉም ያሳስባሉ።

ለምሳሌ የአንድነት ፖለቲካን የሚያራምዱት፣ የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የለበትም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አሉ። ይሄ እውነታ ከሌለ እንዴት ችግሩ ኖረ? አንዱ የሌላውን ሕልውና በመካድ፣ የጋራ መግባባት መፍጠር አይቻልም። በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኀን ገና በሙያዊ ነጻነት፣ ከፖለቲካ አቋም ነጻ ሆነው፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ወገኖች ማወያየት የሚችሉና፣ የጋራ ትርጉም መፍጠር የሚችሉ ሲሆኑ ነው ሚናቸውን ተወጡ የሚባለው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ደግሞ ተሻገር ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ የመንግሥትና የግል የምንላቸው መገናኛ ብዙኃን በሙያዊ ነጻነት እየሠሩ ነው ልንል አንችልም። አንደኛ ነጻነቱ የተገፈፈው ከውጭ ብቻ ሳይሆን በውስጥም ስለሆነ ነው። የሙያተኝነት ሥነ ልቦናችን በጣም ብዙ ጉድለት አለው። ራሳችንን ችለን የመሥራት ዝንባሌ የለንም። ምክንያቱም ያለፍንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ስለነበረ ነው። እና በመንግሥትም ሆነ በግል መገናኛ ብዙኀን ይሄ በረጅም ጊዜ የሚመጣ ነው የሚሆነው።

እንዲህ ዓይነቱ ሒደት በሕንድም ታይቷል። …የወገንተኛ ጋዜጠኝነት ፀባይ ያንፀባርቁ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ አሁን ያሉት የኛ መገናኛ ብዙኀኖች፣ አንዳንድ የፖለቲካ ሪፎርሞች ቢኖሩም፣ ሙያዊ ነጻነት አግኝተው የመሥራቱ ነገር የብዙ ጊዜ ተሞክሮ ወደፊት የሚጠብቃቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም ከውስጥ ያለው ነገር ወሳኝ ነው። በሙያ ባሕል እየዳበረ ሔዶ የሚስተካከል፤ እንደ ባህል የሚያድግ ነው እንጂ፣ የሙያ ነጻነትን በአንድ ቀን አዳር ልናረጋግጠው የምንችለው ነገር አይደለም።

ሚዲያው ፋይናንስ እንደሚፈልግ የጠቆሙት የካፒታል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ግሩም፣ ስለዚህ ወደ ሚዲያው ገንዘብ ይዘው የሚመጡ ባለሀብቶች እንደሚያስፈልጉ ይጠቁማሉ። “ለምሳሌ አጠቃላይ የሚዲያን ገጽታ በምንመለከትበት ጊዜ፣ በአብዛኛው የብሮድካስቱ ሚዲያ የመንግሥት ኃይል ትልቅ ሆኖ ይታይበታል። የኅትመት ዘርፉን ስናይ ደግሞ ጎልቶ የመጣበትን ሁኔታ እናያለን። ነገር ግን የኅትመት ሚዲያው የጎላ ይምሰል እንጂ፣ አሁን ብዛቱ እየጨመረ ይምጣ እንጂ ደካማ ነው። በተለይ ከፋይናንስ አቅሙ አኳያ በጣም ደካማ ነው። ለወደፊቱ ይሄ መለወጥ መቻል አለበት” ሲሉ ያክላሉ። የኢትዮጵያን ጋዜጠኝነት ለማሳደግ እነዚህ ሁሉ መሰናክሎች መፈታት መቻል ይኖርባቸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here