በኢትዮጵያ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተወቀሱ

0
582
  • ዓለም ዐቀፉ የሠራተኞች መብት ተሟጋች ኩባንያዎቹን በዝቅተኛ ክፍያ፣ በማይመች የሥራ ሁኔታ፣ ነፍሰ ጡር ሴቶችን በማግለልና ሌሎች የመብቶች ጥሰት ከሷቸዋል

ሰሜን አሜሪካን መሰረቱን ያደረገው Workers Rights Consortium (WRC) የተባለው የሠራተኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ኢትዮጵያን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ታዋቂዎቹ እና ዓለም ዐቀፍ የአልባሳት አምራቾች የተለያዩ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት እንደሚያደርሱ አስታወቀ። ባለ 35 ገጹ ሪፖርት እንደሚያመላክተው ድርጅቶቹ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከሚያስተዋውቁት የሞራል መርሖቻቸው ጋራ የማይጣጣም መሆኑን አስታውቋል።

ሪፖርቱ ካነሳቸው የመብት ጥሰጦች መካካል እጅግ ዝቅጠኛ የሆነ ክፍያ አንደኛው ሲሆን በሰዓት 12 የአሜሪካን ሳንቲም ድረስ የሚከፍሉ ኩባንያዎች መኖራቸውንም ጠቅሷል። የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የኢትዮጵያ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች “ርካሽ የሰው ኃይል” ያላት አገር በማለት አልሚዎችን ሲጋብዙ እንደነበረ እና ቻይና ለተመሳሳይ ሥራ ከምትከፍለው 1/7ኛውን እንዲሁም ከባንግላዲሽ 1/2ኛውን በሚያክል ክፍያ የሰው ኃይል ቃል ሲገቡ እንደነበርም ሪፖርቱ አትቷል።

በአራት የጨርቃጨርቅ ኩባኒያዎች ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳይው አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ደሞዝ መቁረጥ፣ የቃላት ጥቃቶች መሰንዘር፣ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ማግለል እንዲሁም ብዙ ሠራተኞች ራሳቸውን እየሳቱ ሥራ እንደሚያቋርጡም ተገልጻል።

የሪፖርቱን መውጣት ተከትሎም ፒቪኤች የተሰኘው ዓለም ዐቀፍ የጨርቃጨርቅ እና የአልባሳት አምራች ኩባኒያ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎቹ ላይ የሚነሱ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቋል። የታዋቂዎቹ ቶሚ እና ከልቨን ከላየን ብራንዶች ባለቤት የሆነው ኩባኒያ ከአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በ2010 መስከረም ወር በኢትዮጵያ ባለው ኢንቨስትመንት የተቋማዊ ልኅቀት ሽልማት ማግኘቱ ይታወሳል።

የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ስለሚገኙ ፋብሪካዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በፓርኮቹ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ከሥራ የመልቀቅ ምጣኔ መኖሩንና ለዚህም ምክንያቱ ዝቅተኛ የሆነ ክፍያ፣ የማይመች የሥራ ሁኔታ፣ የግዴታ ትርፍ ሰዓት ሥራ እና ሌሎችም መኖራቸውን ለዓመታት ሲጠቅሱ ቆይተዋል።

በተጨማሪም ኤች ኤንድ ኤም (H&M) እና ዋልማርት (WALMART) የተባሉት ዓለም ዐቀፍ ኩባኒያዎችም ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እንደታዩባቸው ጥናቱ አመልክቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here