በአዲስ አበባ ይፋ በተደረገው ፈረቃ ውሃ ማግኘት አልተቻለም

0
704

• የመብራት መቋረጥ ሊከሰት ከቻለ ወረዳዎቹ ለ14 ቀን ውሃ የማግኘት ዕድሉ የላቸውም

በአዲስ አበባ በበርካታ ወረዳዎች የውሃ እጥረት ተከስቷል። በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ 116 ወረዳዎች ውስጥ 91ዱ ውሃ የሚያገኙት በፈረቃ መሆኑ ታውቋል። ከነዚህ ውስጥ በኤሌትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ውሃ የሚቆራረጥባቸው አካባቢዎች ቦሌ ወረዳ 10፣ 15፣ ሰሚት፣ ቦሌ አራብሳ፣ ኤካ አባዶ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11፣ 12፣ 13፣ 14 መሆናቸውን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኀላፊ ሰርካለም ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በጉለሌና የካ ክፍለ ከተማ 16 ወረዳዎች በሳምንት አንድ ቀን ብቻ (እሱንም በምሽት) ውሃ እንደሚያገኙ የነገሩን ሰርካለም፣ በዚህም ቀን የመብራት መቋረጥ ሊከሰት ከቻለ ወረዳዎቹ ለ14 ቀን ውሃ የማግኘት ዕድሉ እንደማይኖራቸው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

29 ወረዳዎች በሳምንት ኹለትና ሦስት ቀን ውሃ የሚያገኙ ሲሆን፥ በሌሎች 46 ወረዳዎች ከ4 እስከ 6 ቀን ውሃ ሲያገኙ፣ 25 ወረዳዎች ደግሞ ሳምንት ሙሉ ውሃ ያገኛሉ። ሳምንት ሙሉ ውሃ የሚያገኙት ወረዳዎች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው የተመቸ በመሆኑ እንደሆነም አክለው ገልጸዋል።

ለአዲስ ማለዳ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ተጠቃሚዎች እንደሚሉት፥ ውሃ የሚመጣበት ጊዜ በሳምንት አንድ ቀን ከመሆኑም ባሻገር የተቆረጠ ቀን የሌለው በመሆኑና ውሃውም ሌሊት ብቻ ስለሚመጣ ያንን ተከታትሎ ለመቅዳት ሦስትና አራት ቀን እንቅልፍ አጥተው ማደር ግድ እንደሆነባቸውና ያም በቀን ሥራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 3 ዓመታት ወደ ምርት የገባ መሠረታዊ የውሃ ፕሮጀክት ባለመኖሩ በውሃ ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለው ክፍተት እየሰፋ መጥቷል።

በመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ስርጭት ረገድ በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ሰፊ ቅሬታ እየተነሳ ሲሆን፣ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሞገስ አርጋው የችግሮቹን መሠረታዊ መነሻ በመረዳት በጊዜያዊነት እና ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት እየሠሩ እንደሆነ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ለመገናኛ ብዙኀን ገልጸዋል።

ከፍተኛ የሆነ የውሃ ፍጆታ የሚጠቀሙ ተቋማት የራሳቸው የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር እንዲገለገሉ ለማድረግ የቴክኒክ እና የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን ዘመናዊ ለማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ እንደሆነም ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here