የንግድ ባንክ “ሴት ሠራተኞች ቅርንጫፍ” እና የሴቶች “እኩልነት”

0
465

በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴት ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበትን አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ መክፈቱን መነሻ በማድረግ ቤተልሔም ነጋሽ፥ የዓላማውን አሳማኝነት በማጠየቅ ውጤታማ የሆኑትን ሴት ሠራተኞቹን በሽልማትና በሹመት ወደ ተሻለ ቦታ በማድረስ በሥራ አመራርና ከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉትን ሴቶች ቁጥር መጨመር የተሸለ ይሆን እንደነበር ሲሉ ይሞግታሉ።

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴት ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበትን አዲስ ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ቦሌ አትላስ አካባቢ መፈክቱ ሚያዝያ 7 ከሰማናቸው ዜናዎች አንዱ ነበር። በዕለቱ ማታ ዜና ላይ በቴሌቪዥን ዘገባውን ስመለከት ቀድሞ የታሰበኝ “ዓላማው ምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት የወሬ ጉጉቴን ለማሳካት ለጉዳይ በሔድኩበት የባንኩ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አንዱን መካከለኛ ደረጃ ኃላፊ ብጠይቅ “እኛም አልገባንም እባክሽ፥ እንኳን ዓላማውን ልንረዳ ከአንቺ እኩል ማታ በቴሌቪዥን ነው ዜናውን የሰማነው” አላለም። ከዚያ እርምጃው ትንሽ ከፈረሱ ጋሪው የሚያሰኝ ነገር እንዳለውና ሌላም በኋላ እዚህ የማነሳውን ጨምሮ አንዳንድ ነገር ልለው ሞከርኩ። በፈገግታ ከመመለስ ውጪ ብዙም ውይይቱን የመቀጠል ሐሳብ አላየሁበትምና እዚያው ላይ አቆምኩ።

ቢሮዬ ተመልሼ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ስሞክር የተለያዩ የዜና አውታሮች የዘገቡትን ተመሳሳይ ዘገባ አየሁ። የሳበኝ ምክንያቱ ወይም የሴቶች ብቻ አገልግሎት ሰጪነት ዓላማ ምን እንደሆነ ማወቅ ነበርና ዘገባውን ወደዛ ሳጠብ ሦስት ምንጮች ማለትም ሪፖርተር አማርኛ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ቢቢሲ አማርኛ ስለዓላማው በተመሳሳይ ያስቀመጡትን አገኘሁ። ከዚህ ጋር የተያያዙ ጥቂት ዐረፍተ ነገሮችን ከዜናዎቹ ላይ ላሳይና ወደ ቀጣዩ ሐሳቤ ልለፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
“የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹት፤ ሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበት ቅርጫፍ የተከፈተው ሴቶች ለአገር ዕድገት ላላቸው አበርክቶ እውቅና ለመስጠት ነው።”

“በአገልግለቱ የፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተገንዘበናል’’ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም በዋና ዋና ከተሞች ሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡባቸው ቅርጫፎች ይከፈታሉ ብለዋል።

የቢቢሲ ዜና
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ ሴቶች በአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራቸውም የሚገባቸውን ቦታ ባለማግኘታቸው የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበትና ለማበረታታት ሲባል ቅርንጫፉ እንደተከፈተ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

“ሴቶች ከወንዶች በተሻለ ደንበኞችን በጥሩ እንክብካቤ በማስተናገድ ከደንበኞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሲያጠናክሩ በተግባር አይተናል” የሚሉት አቶ በልሁ በሴቶች ብቻ የተቀላጠፈና የተደራጀ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ማሳየትም ሌላኛው ዓላማው ነው ብለዋል።”

ሦስቱም ምንጮች በጋራ
ቅርንጫፉ ከሌሎች ባንኮች የተለየ አገልግሎት ባይሰጥም የሴቶችን የሥራ ፈጠራና የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር የሴቶች የብድር አገልግሎት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን፣ ሠራተኞቹ ከተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች የተውጣጡ መሆናቸውንና ቅርንጫፉ በኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቅ ድርሻ ባላቸው አንጋፋ የባንክ ባለሙያ አቶ ለይኩን ብርሃኑ መሰየሙን ዘግበዋል።

የቅርንጫፉ መከፈት ዓላማ መረጃ ካገኘሁ በኋላም በነገሩ ምቾት ስላልተሰማኝ “እኔ ነኝ ወይስ ምንድነው?” ብዬ ከሥራ ፋታ ሳገኝ የሕዝቡን ሙቀት ለመለካት ሁነኛ ማሳያ ወደሚሆነው ማኅባራዊ ሚዲያ ስገባ በተለያዩ ግለሰቦች በተለይም የተሻለ ተከታይ ባላቸው ድርጊቱ ትችት ተዘንዝሮበት በርካታ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ሰጥተው ተመለከትኩ። በቻልኳቸው በተወሰኑት ላይ ሐሳቤን አኑሬ የባንኩን የተረጋገጠ ብዙ መቶሺዎች ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ ከፈትኩ። ባንኩ በቅርንጫፉ ምረቃ ወቅት የተነሱ ፎቶግራፎችን በተለይም ሴቶች ሠራተኞቹ ዩኒፎርም በሚመስል አንድ ዓይነት የባሕል ልብስ አጊጠው የተነሱትን ፎቶ በገፁ የተሰጡት በርካታ አስተያየቶች የሽያጭ ስልትም ይሁን ሌላ ብሎ ባንኩ ያከናወነው ሴት ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡበት የተከፈተው ቅርንጫፍ ነገር አላስፈላጊ አሉታዊ ትኩረት እንደሳበ ተረዳሁ። የእኔን አስተያየት ከመሰንዘሬ በፊት እንደማሳያ ጥቂት አስተያየቶችን ልጥቀስ።

አንድ አስተያየት ሰጪ፣
“አስፈላጊ ነው? እኔ አልታየኝም። የባንክ ሠራተኛ መሆን ለሴቶች የተለመደ ነው። ስለዚህ ወንድ የማይወዱ ሴት ደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ደንበኛ መያዣ መሆኑ ነው።”

ሌላ አስተያየት፣
“ኹለት ቀን አብረው አይሠሩም፤ ወንድ የሌለበት መሥሪያ ቤት የከብቶች በረት ይመስልባችኋል። ጠብቁ ሰላማዊ ሰልፍ ካልወጡ”

ተጨማሪ አስተያየት
“ሴት ልጅ እኮ ሥራ ቦታ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ወንድ ልጅ እጁን ትከሻዋ ላይ ጣል ሲያደርግባት ሥራውን ታሾረዋለች። አሁን ግን ንግድ ባንክ ሴት ብቻ ደርድሮ ሥራውን ይገድለዋል።”

የመጨረሻ አስተያየት
“ይህቺ በሥም ለመነገድ ነው። ይህን ካሰባችሁ ችግረኛ ሴቶችን እርዱ።”
እነኝህ ከተሰጡት በርካታ አስተያየቶች በጣም ጥቂቶቹ ሲሆኑ በአብዛኛው አሉታዊ፣ አንዳንዴም ከፖስቱ ጋር የማይገናኙ ሐሳቦች መቅረባቸው እንዳለ ሆኖ አልፎ አልፎ ድርጊቱን የሚደግፉ አስተያየቶችም ነበሩ። እነኝህን ያነሳሁት ድርጊቱ የሴቶች እኩልነትን ለማስጠበቅ መሠራት ካለባቸው ሥራዎች አንፃር ታስቦበት ካልተሠራ ኅብረተሰቡ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማስፋፋት ረገድ አስተዋጽኦ አለው ለማለት እንጂ እነኝህ ምላሾች ድርጊቱ በራሱ የተሳሳተ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው በማለት አይደለም። ተቃውሞ መቅረቡ የድርጊቱን ተገቢነትና ጠቃሚነት አያሳይምና።

ንግድ ባንክ በቁጥር ቀላል የማይባሉ ሴት ሠራተኞችን የሚቀጥር መሥሪያ ቤት መሆኑ ይታወቃል። ምናልባት እንደ አንድ አንድ በሥራቸው ስኬታማ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች ሴት ሠራተኞችን ችላ ይላል ወይንም በደል እየደረሰባቸው ችግሩን ለመፍታት አልቻለም ተብሎ ላይወቀስ ይችላል። ምናልባት በግሌ እንኳን የማውቃቸው በጎ ልምዶች አሉት። ከእነኝህ መካከል ሴቶችን በመሪነት ለማሰልጠን የተለያዩ ተግባራት ከሚያከናውነው ʻአሶሴሽን ኦፍ ውመን ኢን ቢዝነስʼ ከተባለው ተቋም ጋር በመሆን ሥራቸውን ከመደገፍ ባሻገር ሴት ሠራተኞቹ የማኅበሩ የተለያዩ የአቅም ግንባታና የመረጃ መለዋወጫ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉ ይጠቀሳል።

ነገር ግን ከባንኩ ዕድሜና ትልቅነት እንዲሁም ከሴት ሠራተኞች ብዛት አንፃር ሴቶችን አንድ ላይ ሰብስቦ “የተሻለ ትሠራላችሁ” ከሚል፣ የፆታ እኩልነት ጥያቄ ግብ “ሴቶችን ለይቶ የእነሱን የብቻ ዓለም መመስረት ነው” የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያስፋፋ ሥራ ከሚሠራ፥ ይህን ውጤታማነት በሽልማትና በሹመት ወደ ተሻለ ቦታ በማድረስ በዚህም በሥራ አመራርና ከፍተኛ ቦታ ላይ የሴቶችን ቁጥር በመጨመር ቢገልፀው ባመሰገንን።

ለምሳሌ ባንኩ ዐሥር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሲኖሩት ሴቶች ኹለት ብቻ ናቸው። ፕሬዚዳንቱን ከሚያካትተው ሰባት አባላት ያሉት የባንኩ ከፍተኛ ሥራ አመራርም ሴቶች ኹለት ብቻ ናቸው። እዚህ ላይ ጠንክሮ ቢሠራ እውነትም በሴቶች እኩልነት ያምናል እንለው ነበር።

በተጨማሪ ከላይ በጠቀስኩት የዜናው የመጨረሻ ክፍል እንደተመለከተው ጥናት ለሴቶች ከባንክ ብድር ማግኘት በተለያዩ ምክንያቶች የበለጠ ከባድ መሆኑን ስላረጋገጠ፥ ይህን ችግር ለመፍታት ሴቶች ብድር የሚያገኙበትን መንገድ አመቻችቶ በዜና ቢመጣ የተሻለ ነበር።

ሌላው ደግሞ አጠቃላይ ኹነቱ ከላይ በታዩት የፌስቡክ አስተያየቶች ማየት እንደሚቻለው በሴቶች እኩልነት ጥያቄ መልስ ማግኘት ላይ የተሳሳተውን እሳቤ ከማሳየቱ ሌላ “ሴቶች የበለጡ ናቸው” የምትለዋን አፍ ማዘጊያም የምታስታውስ ናት።
በተለያየ ቦታ ሴቶች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሊረጋገጥላቸው ይገባል የሚል ሐሳብና ምናልባት እኩል ያልታዩበትን ሁኔታ ለማሳየት ሐሳብ ስናቀርብ የሚገጥመን “ሴቶች ለምን ራሳችሁን ከወንዶች ጋር ታወዳድራላችሁ? በጣም ትበልጣላችሁ” የሚል ነው። ሌላው ሽንገላ “ልጅ መውለድን ያህል ፀጋ ታድላችሁ፥ እንዴት አነስን ትላላችሁ?” የምትል ነች። ከላይ የባንኩ ፕሬዚዳንትም ሴቶች የተሻለ አገልጋዩች ናቸው ብለውናል። መልሳችን “የተሻለች ቦታ፣ መብለጥ ትቅርብን፤ ግዴለም እኩል እንሁን” ነው።

ቬራ ናዛሪያን የተባለች የሴቶች መብት ተሟጋች አባባል ሐሳቤን የተሻለ ስለምትገልፀው ልጥቀሳት። “ሴት ሰው ናት። የተሻለች፣ የበለጠ ብልህ፣ የበለጠ ጠንካራ፣ የበለጠ አዋቂ፣ የበለጠ በፈጠራ ሥራ የተሻለችና ከወንዶች የበለጠ ኃላፊነት የሚሰማት አይደለችም። እንደዚሁ ያነሰችም አይደለችም። እኩልነት በተፈጥሮ የተሰጠ ነው። ሴት ሰው ነች።” ሲቀጥል ደግሞ ሴት በሥራዋ የተሻለች ብትሆን እዛ ለመድረስ ከወንድ የበለጠ ስለሚፈጅባት ስለምታውቅ፣ ለልፋቷ ዋጋ ስለምትሰጥ ነው። የተሻለ ኃላፊነት ብትወስድ ከአስተዳደጓ፣ ከቤተሰብ ኃላፊነት እንድትወስድ ተደርጋ ስለምታድግ ነው። የተለየ ደምና ዘረ መል ስላላት አይደለም።

መፍትሔ ወደሚመስል መደምደሚያ ስመጣ፤
ታዋቂዋ አሜሪካዊት የሴቶች መብት ተሟጋች ግሎሪያ ስቴነም “ሴት ልጆቻችንን ወንዶችን እናሳድግበት በነበረው መልኩ ማሳደግ ጀምረናል። ወንዶች ልጆቻችንን ሴቶች ያድጉበት በነበረው መንገድ ለማሳደግ ብርታት ያለን ግን ጥቂቶች ነን” የሚል ተጠቃሽ አባባል አላት ። በተወሰነ መልኩ በተለይ በከተማ ላለን ተምረናል ለምንል ኢትዮጵያውያን ይህ እውነት ነው። ቁጥራችን ያድጋል ብለን ተስፋ የምናደርገው በአገራችን ያለው የሰፋ የፆታ እኩልነት ሚዛን መዛባት የሚስተካከለው ከታች ከሕፃናት ልጆች ላይ በሚሠራ ሥራ ነው ብለን ስለምናምንም ነው። ካልሆነ አብዛኛው በአሁኑ ወቅት አዋቂ የሚባል ዕድሜ ላይ ያለው ሰው እኛን ሴቶችን ጨምሮ ተጣሞ ያደገና በኋላ በፆታ እኩልነት ላይ የተሻለ የሆነው እንደ አራዶቹ አባባል “ብዙ ማገዶ ፈጅቶ” ነው። ሙቀቱ ያልዘለቀው፣ አሁንም የፆታ እኩልነት ጉዳይ ኒኩሊየር ሳይንስ የሆነበትም አለ። ሌላው አውቆ አጥፊ ነው።
ከላይ በንግድ ባንክ አስተያየት ሰጪዎች ምሳሌ ለመረዳት ይቻላል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here