ዝም አይባል!

0
485

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ፊቷ ቀልቷል፤ እንደተናደደች ያስታውቃል። ቤተሰቡ በተሰበሰበበት ምን እንደሆነች አልናገርም ስላለች ብቻዋን እስካገኛት ድረስ ጠበቅሁ። ወደመኝታ ክፍሏ ስትገባ ተከተልኳት፤ “ምን ሆነሽ ነው? የተፈጠረ ችግር አለ? ሥራ ቦታ አናደውሽ ነው?…” ብዙ ጥያቄ ደረደርኩ።

ዝም አላለችኝም፤ በመጀመሪያ የተወሰኑ የስድብ ቃላትን ወረወረች። በንግግሯ ውስጥ እልህ፣ ቁጣና ንዴት አሉ። “ከታክሲ ከወረድኩ ጀምሮ ሲከተለኝ ነበር። ያውም በስርዓቱ ነው’ኮ ʻአላናግርህም ዞር በልልኝʼ ያልኩት። ጭራሽ መቀመጫዬን እንዴት አድርጎ እንደመታኝ….” ድርጊቱ አሁንም የተደገመ ያህል አንቀጠቀጣት። ያናድዳል! ስሜቷን ተረዳሁት፤ እልኸኛዋ እህቴ አሳዘነችኝ።

“በቃ አትናደጂ! እና ግን ዝም አልሽው ወይስ…” ጠየቅሁ፤ “ታድያ ምን አማራጭ ነበረኝ፤ ደግሞ እንዲህ ገጥሞኝ አያውቅም። በዛ ላይ ተሳቀቅሁ…ብዙ ሰው በአካባቢው ነበር። ይሔ….” ቀጥላ ሌሎች የስድብ ቃላትን ወረወረች። እህቴ ደፋርና እልኸኛ መሆኗን ስለማውቅ የንዴቷን ጥንካሬ ተረድቻለሁ።

እኔም የመጀመሪያ ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ ወንዶች መትተውኝ አልፈው ሲሳሳቁ፤ ከእርሷ ባላነሰ መናደዴንና ምንም ላደርግ የማልችል መሆኔ ሲሰማኝ ደግሞ ማልቀሴን አስታውሳለሁ። “አትናደጂ…አንዴ ሆኖ የለ?» አልኳት ላጽናናት። በእንቅልፍ ካልሆነ በሌላ ንዴቷ አይበርድምና በተቀመጠችበት ወደ ጎን ጋለል ብላ ፊቷን በትራስ ሸፈነች።

ድምፄን አጥፍቼ ከአጠገቧ ቆየሁ። ሴት በመሆኔ ብቻ የሚደርስብኝን ባውቅም በሕይወቴ አንድም ቀን ʻምን አለ ወንድ ሆኜ በተፈጠርኩ ኖሮʼ ብዬ አላውቅም። ግን ጉልበታምና ተደባዳቢ ብሆን ተመኝቻለሁ። ሊነካኝ የሚቀርበውን ወይም በጉልበቱ ታብዮ እንደልቡ የሚናገረውን በአንዳች ኃይል በጉልበት ብቀጣው አምሮኝ ያውቃል። ጉልበት ባላቸውና ራሳቸውን ለመከላከል በሚችሉ ሰዎች ቀንቻለሁ።

የበለጠ የሚያናድደኝ እንዲህ ተማትቶና ተላክፎ ላለፈው ዱርዬ መልሼ የምሳቀቀው፤ ሰው አየኝ አላየኝ የምለው እኔው መሆኔ ነው። እህቴን አየኋት! ለእኔ የነገረችኝን ለቤተሰብ እንኳን ለማውራት አፍራለች። ለምን? የመታት ሰው የከፋውን በደል የፈጸመ ነውና ጮክ ብላ ተናግራ ልታዋርደው አይገባም ነበር? በአካባቢው ያለው ሰውስ ʻአንተ አታርፍም!ʼ ማለት አልነበረበት?
ማን ነው መሸማቀቅ ያለበት? አስገድዶ የደፈረ ወይስ የተደፈረችው? መንገድ ዘግቶ አላሳልፍሽም ያለው ወይስ የተባለችው? የፈላ ውሃና አሲድ የደፋው ወይስ የተደፋባት? ማነው በድርጊቱ አፍሮ አንገቱን መድፋት ያለበት? የቱንስ ነው ማኅበረሰቡ መገሰጽ የሚገባው? ማን ነው መጸጸት የሚያስፈልገው? ጠየቅሁ።

እናም ጥቃት ከሚፈጽሙ የአስተሳሰብ ድኩማን በላይ አጥፊውን ከፍ አድርጎ የተበደለውን አንገት የሚያስደፋው ማኅበረሰብ አበሳጨኝ። ለምንድን ነው ዝም ያልነው? ተበድለሽም የምትሸማቀቂው ስለምን ነው? እባክሽ እህቴ ዝም አንበል! እህቴን ቀስቅሼ ተስተካክላ እንድትተኛ ነገርኳት።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here