የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ 540 ሚሊዮን ብር ከሰረ

0
360

• ማቀነባበሪያው በ2007 ሥራውን የጀመረ ሲሆን በዓመት 500 ሺሕ ኩንታል የማምረት አቅም ነበረው

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ለማደበሪያ ማቀነባበሪያ ላስገነባቸው ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን ጥሬ ዕቃ ከውጭ አገር ማስገባቱን ተከትሎ በአምስት የኢትዮጵያ ክልሎች ላይ አራት ዓይነት ግብዓቶች በመጋዘን ለብዙ ጊዜ በመቀመጣቸው ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል።

ፋብሪካዎቹ በቱሉ ቦሎ፣ ነቀምት፣ መቀሌ፣ ባሕር ዳርና ወራቤ የሚገኙ ሲሆን 15 ሺሕ 52 ኩንታል ቦሮን፣ 117 ሺሕ 639 ነጥብ 5 ኩንታል ፖታሺየም፣ 5 ሺሕ 965 ነጥብ 25 ኩንታል ዚንክ እና 338 ነጥብ 6 ኩንታል ፈርቲኮት ለረዥም ዓመታት በክልሎቹ በመጋዘን ውስጥ ተከማችተው በሥራ ላይ ባለመዋላቸው ምክንያት በጠቅላላው 142 ሺሕ 42 ነጥብ 75 ኩንታል ብክነት እንደገጠማቸው የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የግብዓትና አቅርቦት ስርጭት አስተባባሪ የሆኑት ሙሉጌታ ተፈራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ብክነቱም በብር ሲተመን 539 ሚሊዮን 768 ሺሕ 745 ብር መሆኑ ተገልጿል።

ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በመጋቢት ወር 2007 ሥራውን ጀምሮ የነበረና በዓመት እስከ 500 ሺሕ ኩንታል የማምረት አቅም የነበረው ሲሆን ለፋብሪካው የተፈለገው ግብዓት ግብርና ሚኒስቴር ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ATA) ጋር በጋራ በመሆን በተደረገ ግዢ መሠረት የሚፈለገው ጠጣር ግብዓት ባለመቅረቡና ዱቄት በማስመጣታቸው ምክንያት ፋብሪካው ብልሽት እንዲያጋጥመው ምክንያት ሆኗል፣ በዚህ ግብዓት የተመረተው ማዳበሪያ ለገበሬዎች ሲቀርብ ምርት አልባ ሆነው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ግብርና ሚኒስቴር ግብዓቶቹን አስመልክቶ አሜሪካን አገር ናሙና ተልኮ ምንም ዓይነት የጥራት ችግር የለባቸውም ቢልም የኅብረት ሥራ ኤንጀንሲዎች በሁሉም ክልሎች የሚገኙ በተለይም በትግራይ ክልል ያለው ክምችት ችግር እንዳለበትና ለምርታማነት እንደማይቀርብ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ገልጧል።

ከኹለት ዓመት በፊት ከኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ጋር በመሆን ኮሚቴ በማዋቀር እንዲጣራና መፍትሔ እንዲመጣ ቢሠራም፥ ፋብሪካው ሥራ ከጀመረበት 2007 አንስቶ ክጥቂት ወራት በኋላ ሥራውን ያቆመ ሲሆን ያከናወነው ሥራ የሌለ እና እስከ አሁን የሠራተኛ ደሞዝ፣ የመጋዘን ኪራይ፣ ለጉልበት ሠራተኛና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ በጥቅሉ 176 ሚሊዮን 931 ሺሕ 858 ብር ሥራ ባልተሠራበት ሁኔታ ወጪ እንደተደረገ ተገልጧል። ፋብሪካዎቹ በዓመት 100 ሺሕ ቶን የማቀነባበር አቅም የነበራቸው ሲሆን ለእያንዳንዳቸው ከ35 እስከ 54 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ተነግሯል።

ከ2004 ጀምሮ የአፈር ለምነት ዳሰሳ ጥናት ከተካሔደ በኋላ 12 የማዳበሪያ ዓይነቶችን በመለየት ፋብሪካዎቹን ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርና ሚኒስቴር በመረከብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ግንባታውን ተጠናቆ የነበረ ሲሆን በዓመት 100 ሺሕ ቶን የማቀነባበር አቅም ነበረው።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ፋብሪካውን የሞሮኮ ኩባንያ ለሆነው ለOCP በማስረከብ እነዚህ የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የኅብረት ሥራ ማኅበራት OCP ከተሰኘው የሞሮኮ ኩባንያ ጋር የ15 ዓመት የሊዝ ኪራይ ሥምምነት ፈፅመዋል። ሥምምነቱ ፋብሪካው ይዞ የሚገኛቸውን ንብቶች እንዲሁም ሠራተኞቹን ጭምር ያጠቃለለ መሆኑም ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here