የሕግ ኩባኒያዎችን ማቋቋም ሊፈቀድ ነው

0
669

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጠበቆች በሙያቸው ተደራጅተው የሕግ ኩባኒያዎችን እንዲያቋቁሙ የሚፈቅደውን አዋጅ በሚመጣው አምስት ወር ውስጥ እንዲጸድቅ እንደሚሠሩ ተናገሩ። ላለፉት 18 ዓመታት ሳይለወጥ የቆየው የጠበቆች ምዝገባ አዋጅ ከአንድ ዓመት በፊት ለማሻሻል ጥናቶች ተጀምረው የነበረ ሲሆን የመጀመሪያ ረቂቁ ላይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከ1 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ጠበቆች በቅርቡ እንደሚወያዩበት ታውቋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ፀጋዬ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በግልፅ የጠበቆች ማኅበር (Bar Association) ከነሙሉ ኃላፊነቱ መቋቋም አለመቋቋሙን ከመግለፅ ቢቆጠቡም መንግሥት ብቻውን የሙያ ሥነ ምግባር ማስከበሩን እንዳላዋጣው ግን ጠቁመዋል። አክለውም ጠበቆች ተደራጅተው እርስ በእርስ ሊተራረሙ እና የሙያ ሥነ ምግባሩን እንዲያስጠብቁ የሚያስችል አዋጅ ነው ብለዋል።

የአሃገሪቱ ምጣኔ ሀብት እያደገ ከመምጣቱ እና የውጪ አገር ባለሀብቶች በሰፊው መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ ቢመጡም ኢኮኖሚውን የሚመጥኑ እና የተደራጁ የሕግ ኩባኒያዎች መቋቋም ባለመቻላቸው ሲቸገሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ጠበቶች በግላቸው ብቻ የሕግ ቢሮ በመክፈት አገልገሎት መስጠት እንደሚችሉ የሚደነግገው እና የመደራጀት መብታቸውን እንደገደበ ሲጠቅሱ የነበረው ይሄ አዋጅ ከተሸሻለ የተለያየ የሙያ ስልጠና ያላቸው ጠበቆች በአንድ ላይ የህግ ኩባኒያዎችን በማቋቀዋም ዘመን ተሸጋሪ ቢሮዎችን መመስረት ይችላሉ።

አንጋፋ እና ታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች ለረጅም ዓመታት የገነቡት ሥም እና መልካም ሥራ ሕይወታቸው ሲያልፍ የህግ ቢሮዎቻቸው እንደ ኩባኒያ መቀጠል ሲያቅተው ይስተዋላል። ለዚህም በስራ ላይ ያለው አዋጅ ኩባኒያዎቹን መቋቋም ቢፈቅድም አዋጁን ወደ ስራ የሚያስገቡ ዝርዝር መመሪያ እና ደንቦች የግድ እንደሚያስፈልጉ ይደነግጋል። ነገር ግን መንግስት እነዚህን ያፈፃፀም ህጎች ለማውጣት ዳተኛ ሆኖ ቆይቷል።

ኩባኒያዎቹ ሲፈቀዱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመ ያለውን በሕግ ሞያ ተመርቀው ሥራ ያጡ ወጣቶችን የሥራ ዕድል በመክፈት አስተዋጽኦው ሠፊ እንደሚሆን ይጠበቃል። በጥብቅና ሞያ ላይ ለሚነሱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችም አዋጁ መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ ለሕጉ መነሻ የተሰራው ጥናት ያመላክታል።

ጠበቆች ባላቸው ስም ብቻ በማያውቁት የሕግ ዘርፍ ለደንበኞቻቸው ጥብቅና የሚቆሙ ሲሆን በሙያቸው ለሚያደርሱት ጉዳትም ዋስትና እንዲሁም ካሳ ለደንበኞቻቸው እንዲከፍሉ አይደረግም። የህግ ኩባኒያዎች ከሙያዊ ስልጠና ትኩረት ባሻገር ለአገልግሎታቸው ዋስትና እና ተጠያቂነትንም ጭምር ማምጣቱ አለማቀፍ ልምዶች ያስረዳሉ።

የሕግ እና የአሰራሩን መሰናክል ተቋቁመው በሕግ ኩባኒያ መልክ ደንበኞቻቸውን የሚገለግሉ በጣት ለሚቆጠሩ የሕግ ቢሮዎች የዐቃቤ ሕጉ መግለጫ ተስፋን ያጫረና የአገሪቱ የፍትሕ እና የሕግ ሞያ ታሪክ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ ተግባር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here