ሕወሓት በሕዝቡ ላይ ጥቃት ማድረሱን ኹለት ፓርቲዎች አስታወቁ

0
634

ባለፈው እሁድ፣ ሚያዚያ 6 የኵሓ ሕዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አካባቢን የማፅዳት ጥሪ ተቀብሎ በተሰማራው ሕዝብ ላይ ሕወሓት ያሰማራቸው አካላት በሕዝቡ ላይ ይህ ነው የማይባል ጥቃት አድርሰዋል ሲሉ ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ እና ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።

ቀደም ሲል የአመራሩ ብኩንነትና አቅመ ቢስነት በፖሊሲ ደረጃ ሲተቹ በነበሩ እንደነ ነቢዩ ስሑል፣ ፅጋቡ ቆባዕ /የዓረና አባል/ ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሰውባቸው ወጣቶቹ ዓይደር ሆስፒታል ገብተው በመታከም ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) በዛው እለት ተደብድበው ጉዳት የደረሰባቸው፣ ሽዋዓለም ለማን ጨምሮ ሌሎች 21 ወጣቶች እቤታቸው ተኝተው በማገገም ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በተለይ የመሬት ነጠቃን አስመልክቶ ፍትሕ በማጣት የተበሳጩት፣ አማከለች ታደሰ ራሳቸውን ሰቅለው ሕይወታቸውን ሲያጠፉ፤ ፀሊላ አብራሃ ደግሞ በብስጭት ብዛት የአካል መንቀጥቀጥ አጥቅቶዋቸው አቤቱታ ለማሰማት በሔዱበት የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤት በራፍ ላይ ወድቀው ሕይወታቸው ማለፉን ኹለቱ ፓርቲዎች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። እሁድ ሚያዝያ 6፤ በመቐለ ኵሓ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ወጣቶችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በፖሊስ መደብደባቸውና መታሰራቸውን ተናግረው፣ እርምጃውን የሕግ የበላይነት የጣሰ ብለውታል። በሌላ በኩል “ሕወሓት በመግለጫው ያቀረባቸው ውንጀላዎች ተቀባይነት የላቸውም” ሲሉ አክለዋል።

በሕውሓት መግለጫ ላይ “ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱና የፌደራል ስርዓቱ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን ኅልውና ማረጋገጥ አለበት” ሲል መቅረቡ እንዳስገረማቸው የገለጹት የትዴት ሊቀመንበር አረጋዊ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ቀዳሚ የነበረው ሕወሓት ሆኖ እያለ እራሱን ሳያርም እንዲህ ዓይነት መግለጫ ማውጣቱ ከጭንቀት የመነጨ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል። መግለጫውም እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመቐለ ኵሓ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ወጣቶችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በፖሊስ መደብደባቸውና መታሰራቸው ተቃዋሚው ዓረና አስታውቆ፣ በጉዳዩ ላይ የዓረናው ሊቀ መንበር አብርሃ ደስታ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፣ እሁድ በመቐለ ኵሓ ወጣቶች በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት ወቅት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት እንደፈፀሙባቸውም ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙርያ አዲስ ማለዳ ከክልሉ መንግሥት በኩል ያለውን መረጃ ለማግኘት የመቐለ ኩሓ ክፍለ ከተማ ፖሊስና የፀጥታ ፅሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ በመደወልና በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው የጽሑፍ መልዕክት ብንልክም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

በአጠቃላይ በትግራይ ሕዝብ በተለይም ደግሞ በወጣቱ ትውልድ ላይ በሕወሓት አመራር እየተወሰደ ያለው ጭካኔ የተሞላው የድብደባ፣ የእስር እና የግድያ እርምጃዎች የዴሞክራሲና የአንድነት ትግሉን ያጠናክረዋል እንጂ በምንም መንገድ ሊገታው አይችልም ያሉት ዓረናና ትዴት፥ ሕወሓት አሁን በእስር ቤት ያጎራቸውን ወጣቶች በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ በፖሊስ ድብደባ ለተጎዱትም ሕክምና እንዲደረግላቸውና ተገቢ ካሳ እንዲከፍላቸው፣ እንዲሁም ይህንን አሰቃቂ ግፍ የፈጸሙትን በሕግ እንዲጠየቁልን ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here