በኦሮሚያ ክልል አራት ከተሞች ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የተበደሩትን ገንዘብ አልከፈሉም

0
431

• አማራ ክልል ያለበትን እዳ እከፍላለሁ ሲል፣ የኦሮሚያ ክልል ግን እስከአሁን ምላሽ አልሰጠም

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ከብድሩ ተጠቃሚ የሆኑት 4 ከተሞች ለአራት ዓመት መክፈል ከነበረባቸው እዳ 53 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንዳልተከፈለው የውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በክልሉ ከተገነቡት ፕሮጀክቶች ውስጥ ለሙገነት፣ ሻኪሶ፣ አዶላ እና ሰበታ የሚገኙበት ሲሆን እነዚህም ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን የተበደሩትን እዳ መክፈል አልጀመሩም። የተበደሩትን ብድር በማዘግየታቸው ጊዜውን ጠብቀው መክፈል እንዲጀምሩ ጽሕፈት ቤቱ ለክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ደብዳቤ የላከ ቢሆንም፣ እስከአሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዋና ዋኬ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በተያያዘም የአማራ ክልል ለውሃ መጠጥ ፕሮጀክት ግንባታ ማስፋፍያ 7 ከተሞችን ከብድሩ ተጠቃሚ በማድረግ ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ እንዲያቀርቡ በማሰብ በከተሞቹ ላስጀመሯቸው ፕሮጀክቶች 72 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መክፈል የነበረባቸው ቢሆንም፣ ከተሞቹ እዳቸውን በተያዘላቸው ጊዜ እየከፈሉ ስላልሆነ ጽሕፈት ቤቱ ለክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፥ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከሐምሌ 2011 ጀምሮ እዳቸውን መክፈል እንደሚጀምሩ ከውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጋር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። እንዲሁም፣ ፅሕፈት ቤቱ ለግንባታ ማስፋፍያው ብድር ተጠቃሚ ካደረጋቸው ከተሞች ደቡብ ክልል 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሁም፣ አዲስ አበባ 26 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ቢኖርብንም መሰብሰብ ግን አልቻልንም ሲሉ ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።

ጽሕፈት ቤቱ የብድር አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ1996 በሚዛን ቴፒ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲሆን፣ እስከአሁን በ104 ከተሞች ለ114 ፕሮጀክቶች የ10 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ሰጥቷል። ይሁንና ጽሕፈት ቤቱ በዚህ ዓመት ግንባታቸውን ካጠናቀቁ 34 ፕሮጀክቶች ውስጥ መሰብሰብ የነበረበት 689 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ ማከናወን የቻለው ከ17 ከተሞች 528 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። በመሆኑም በተቋሙ የተቀላጠፈ ሥራ እንዳይሠራ እያስተጓጎለው ያለው ከተሞቹ እዳቸውን መክፈል በማቋረጣቸው መሆኑን ፅሕፈት ቤቱ አሳውቋል።

በ1994 የተቋቋመው የውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ለከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም፣ ለሰፋፊና መካከለኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል ፋይናንስ ከውጪ አገራት አበዳሪዎች እና እርዳታ ሰጪ ተቋማትን እያፈላለገ ነው።

የውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ከውሃ ዘርፍ አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂ መርሆች አንዱ በሆነው ዋጋን በማስመለስ መርኅ ላይ በመመስረት ለተጠቃሚው ኅብተረተሰብ በረጅም ጊዜና በአነስተኛ ወለድ የሚከፈል ብድር ለመስጠት ታስቦ የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here