አዲስ እና ብቁ ሰዎች ኀላፊነት ይሰጣቸው

0
842

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የአመራሮች ሹም ሽር የፖለቲካ ታማኝነት ያላቸውን ሰዎች ወደ ላይ ከማምጣት የበለጠ ፋይዳ ኖሮት አያውቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በኢሕአዴግ ስርዓተ መንግሥት ደግሞ ከዚህ በባሰ አንዳንድ ሚኒስትሮች ሦስት እና አራት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችን እየተሽከረከሩ እና እያፈራረቁ እንዲመሩ ይደረጋል። የሚኒስትርነት ማዕረጎች እና ሹመቶች የፖለቲካ ሹመቶች እንደሆኑ ቢታወቅም፥ ሹመቶቹ ዕውቀትን፣ ልምድን እና ሕዝባዊ ቅቡልነትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ግን ማድረግ ግን ይቻላል፤ ያስፈልጋልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነት በዓለ ሲመታቸውን ካደረጉ ገና አንድ ዓመታቸው ነው። ይሁን እና ሦስት ጊዜ የሚኒስትሮች ሹም ሽረት አድርገዋል። በሚያዝያ ወር 2010 ባደረጉት ሹም ሽር በወቅቱ ከነበሩት 28 የካቢኔ አባላት መካከል 10ሩን ቀይረዋቸዋል። በመቀጠልም በጥቅምት ወር 2011 የካቢኔ አባሎቻቸውን ቁጥር ወደ ሃያ በመቀነስ፣ እንዲሁም የሴቶች እና ወንዶችን ቁጥር በማመጣጠን ከፍተኛ ውዳሴ ያስገኘላቸውን ሹም ሽር አካሔደዋል። ይሁን እንጂ ኹለቱንም ሹም ሽሮች ሲያካሒዱ የበለጠ አነጋጋሪ የነበሩ ክስተቶች ስለነበሩ ጉድለቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ውይይት ማድረግ አልተቻለም ነበር።

የመጀመሪያው ሹም ሽረታቸው ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ የተከናወነ በመሆኑና በወቅቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ እያስተናገደች ስለነበር እምብዛም ለትችት አልቀረበም። ኹለተኛ ሹም ሽረታቸው የሴቶች እና ወንዶችን ምጥጥን ያስተካከለ ስለነበር እና በዓለም ዐቀፍ ደረጃም ውዳሴ ያተረፈላቸው እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ አነጋጋሪ የነበረ በመሆኑ ምክንያት የተሿሚዎቹ አመራረጥም ይሁን የተደለደሉበት ቦታ፣ እንዲሁም ብቃታቸው እና ሕዝባዊ ቅቡልነታቸው ከግምት ውስጥ አልገባም ነበር።

ይህ በእንዲህ እያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ሳምንት ሌላ ሹም ሽር በማካሔድ የቀድሞዎቹ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ረዕሰ መስተዳድሮች የአገር መከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ቦታዎች እንዲወስዱ ተደርጓል። የአገር መከላከያ ሚኒስትሯ ደግሞ ቀድሞ ወደነበሩበት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትርነት ተዛውረዋል።
አዲስ ማለዳ እነዚህ ሹመቶች ኹለት የተለመዱ ስህተቶች የተደገሙባቸው ናቸው ብላ ታምናለች።
1ኛ፣ ወጣት እና ብቃት ያላቸው ሰዎች አልመጡበትም፣

2ኛ፣ ሚኒስትሮች በሚያውቁት እና ልምድ ባፈሩበት ዘርፍ አልተመደቡም፣

ሚኒስትሮች እና አመራሮች በኢትዮጵያ ያለፉት ዓመታት ተሞክሮ ቦታ እየተለዋወጡ ከመምራታቸው በስተቀር አዳዲስ ፊት እና ሙያተኛ የማግኘት ዕድላቸው በጣም አነስተኛ ሆኗል። ይህም በየጊዜው የሚለዋወጠውን የዜጎች ፍላጎት እና የአስተዳደር ክኅሎት አቅርቦት ፍላጎት የማይዋጁ ሰዎች ሥልጣን ላይ ሆነው አቅሙ ያላቸው ወጣቶች እና ባለሙያዎች ግን ገሸሽ እንዲደረጉ መንሥኤ ሆኗል።

እነዚህ ችግሮች አዲስ ሳይሆኑ ነባር እና እንደቋሚ ባሕል የተወሰዱ ናቸው። ሚኒስትሮች በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በቋሚነት የማይቆዩ በመሆኑ ምክንያት መሠረታዊ የሆነ ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት ይቸግራቸዋል። ይልቁንም ተቋሙን ትንሽ ከተለማመዱት በኋላ ተነስተው ወደ ሌላ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የሚዛወሩ በመሆኑ የጀመሩትን ሥራ እንኳን መጨረስ ባለመቻላቸው ምክንያት ወጥ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረግም ይሁን ተቋማዊ ባሕል መገንባት እንዳይዋጣላቸው አድርጓል።
አዲስ ማለዳ የሚኒስትሮች ሹም ሽር ለይስሙላ እና የፖለቲካ ታማኞችን መሠረት ያደረገ ብቻ መሆን የለበትም ብላ ታምናለች። ይልቁንም የሕዝብን ቁመና የሚመጥኑ፣ ከፍተኛ ቅቡልነት ያላቸው፣ አዳዲስ ለውጦችን እና እመርታዎችን ማስመዝገብ የሚችሉ፣ የትምህርት እና የልምድ ብቃት ያዳበሩ ሰዎች ወደ አመራር መምጣት ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ የፖለቲካ ለውጥ በሚዘመርበት ወቅት ምንም አልተለወጠም የሚያስብል ድምዳሜ ከማስያዙም በላይ ለውጡን የሚመጥን ተቋማዊ መልሶ ማዋቀር ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል።

በዚህ የለውጥ ጊዜ የሚኒስትር ካቢኔ አባላት ሹመት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሹም ሽረቶች ብቃትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ለውጡን ለማፅናት ወሳኝ ነው። ኦሮሚያን ጨምሮ ትግራይ እና ሶማሊ ክልሎች፣ እንዲሁም አዲስ አበባ የምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው በምክትል ማዕረጎች የተሰየሙላቸው አመራሮች ምን ያህል ለውጥ አመጡ ብሎ መጠየቁም የሹም ሽረቱን ውጤት ያመለክታል።

በዚህ አስቸጋሪ እና ትልቅ የአመራር ክሕሎት የሚጠይቅ ወቅት ያሉትን መሪዎች ወዲያ እና ወዲህ እያቀያየሩ መጠቀም ችግሩን በፈጠረው ጭንቅላት ለመፍታት መሞከር እንዳይሆን አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here