የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 1 ሺሕ 181 ሔክታር መሬት በእሳት ወደመ

0
442

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መነሻው ባልታወቀ ሰደድ እሳት 1 ሺሕ 181 ሔክታር የሚሆነው የፓርኩ ክፍል መውደሙን የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌትነት ይግዛው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። በባለስልጣኑ ይፋ ተደረገው መረጃ መሰረት መጋቢት 20/2011 በድጋሚ ለኹለተኛ ጊዜ እሳቱ አገርሽቶ ያወደመውን ሳይጨምር እንደሆነ አስታውቀዋል ።

እንደ ጌትነት ገለፃ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፓርኩ ኹለት ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት ያጋጠመው ሲሆን የፓርኩን ሠፊ ክፍል ለውድመት መዳረጉንም ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ 22 ሺሕ ሔክታር ከሚሸፍነው የፓርኩ የቆዳ ስፋት ውስጥ በመጀመሪያው የሰደድ እሳት አደጋ 1 ሺሕ 181 ሔክትሩ እንዲወድም ሆኗል። እሳቱ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ያደረሰባቸውን አካባቢዎች ጌትነት ይግዛው ለአዲስ ማለዳ በዝርዝር እንዳስታወቁት፤ 39 ሔክታር የሚሆን ውድመት በሳንቃበር ʻሳይት ካምፕʼ የደረሰ ሲሆን ይህም ከተከሰቱት ጉዳቶች ዝቅተኛው ነው ።

በሌላ በኩል ደግሞ በፓርኩ ውስጥ እሜት ጉጉ በሚባል አካባቢ 3 መቶ ሔክታር በሰደድ እሳቱ ወድሟል። በዚህ አካባቢ በኅብረተሰቡ ርብርብ እሳቱ በቁጥጥር ሥር ባይሆን ኖሮ በፓርኩ ውስጥ ተጠልለው ወደሚኖሩት ብርቅዬ የዱር እንስሳቶች ተዛምቶ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ኃላፊው ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ 4 መቶ ሔክታር ውድመት የደረሰበት ግንጭ በመባል የሚታወቀው የፓርኩ ክፍል ሰደድ እሳቱ ካደረሰው ጉዳት ከፍተኛውን ይይዛል። በዚህ አካባቢ እሳቱ ከፍጥነቱ የተነሳ እንደሌሎች አካባቢዎች በኅብረተሰቡ ርብርብ የማይቻል ከመሆኑም በላይ በንፋስ እየታገዘ አቅጣጫውን በመቀያየሩ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደነበር ጌትነት ተናግረው፤ በአካባቢው ዝናብ የመዝነብ አጋጣሚ በመፈጠሩ የወደመው የፓርኩ ክፍል ወድሞ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች ተጨማሪ አካባቢዎች በድምር 442 ሔክታር የሚሆን የፓርኩ ክፍልም ጉዳት ተከስቶበታል።

ባለሥልጣኑ አሁን ባለው መረጃ ይህን ይበል እንጂ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ኃላፊው እምነት እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ሰደድ እሳቱ በተከሰተበት ወቅት በርካታ ገደላማ ቦታዎችን በማዳረሱ ምን ያህል ስፋት ያለው የፓርኩን ክፍል በውል መለካት አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ትክክለኛውን ልኬት ማወቅ አልተቻለም። ለዚህ ደግሞ ሊማሊሞና አዳርቃይ በተባሉ ኹለት አካባቢዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ከገደላማነታቸውም በተጨማሪ ድንጋያማ መሆናቸው ሥራውን በሰው ኃይል እማይሞከር እንዳደረገው ከኃላፊው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።

ለኹለተኛ ጊዜ በስሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ ስለተከሰተው ሰደድ እሳት ባለሥልጣኑ እንደገለጸው፤ ሰደድ እሳቱ እንደገና እንዲያገረሽ በፓርኩ ይኖሩ ነበሩ ሰዎች ካሳ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ከተደረጉ በኋላ ቅሬታ ያሰሙ እንደነበርና ቅሬታቸውን በዚህ መንገድ ገልፀው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ በምክንያትነት ይጠቅሳል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በፓርኩ ላይ ለተከሰተው ሰደድ እሳት የተጠረጠሩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

መጋቢት 20/2011 ሌሊት እንደጀመረ የተነገረው ሰደድ እሳት በከፍተኛ ፍጥነት የፓርኩን አብዛኛውን ክፍል ያዳረሰ እንደነበር ታውቋል። እንደ ከዚህ ቀደሙ የአካባቢው ማኅበረሰብ እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ ቢያደርግም ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ የፌደራሉ መንግሥት በክልሉ መንግሥት በኩል ጥሪ ቀርቦለት እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ከእሳቱ ፍጥነት በተጨማሪ የአካባቢው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እሳቱን ለማጥፋት የሚደረገውን ርብርብ ከባድ አድርጎት ነበር። በአስቸጋሪው የመሬት አቀማመጥ ምክንያት እሳቱን ለማጥፋት ከተሰማሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ የአንድ ሰው ሕይወት ሊጠፋ እንደቻለ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልፀዋል።

እሳቱን በሄሊኮፕተር ካልሆነ በስተቀር ሌላ የሚጠፋበት አማራጭ አለመኖሩን በመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት ከኬንያ ለዚሁ ዓላማ የሚውል ሄሊኮፕተር የጠየቀ ሲሆን፤ በኬንያ መንግሥትም ይሁንታን አግኝቶ ነበር፤ ነገር ግን በአገሪቱ ፓርኮች በድንገት በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ሄሊኮፕተሮች ወደ ሥራ በመግባታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

በኋላም ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት በውሰት አንድ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር የተገኘ ሲሆን፤ የእስራኤል መንግሥትና በእስራኤል አገር የሚኖሩ ቤተ- እስራኤላዊያን ትብብር ዐሥር አባላት ያሉትን የእሳት አጥፊ ብርጌድ ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል። ከአስተባባሪ ኮሚቴውም ውስጥ የቀድሞ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዘባድያ ይገኙበታል። አንድ ኬንያዊ አብራሪም ከኬንያ መንግሥ ትብብር መገኘቱ ታውቋል።

በሄሌኮፕተር የታገዘው የእሳት አጥፊ ብጌድ ሥራውን እንደታሰበው በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉን የሚገልፀው ባለሥልጣኑ ለዚህም ደግሞ ሄሊኮፕተሯ ውሃ እና ነዳጅ ለመቅዳት ደባርቅና ጎንደር ከተሞች ድረስ መሔድ ስላለባት ነው ብሏል። ይሁን እንጂ የውሃውን አቅርቦት በቦቴ ወደ አቅራቢያው በማድረስ እሳቱን በፍጥነት በማጥፋት በቁጥጥር ሥር እንዲውል እንደተደረገ ተጠቁሟል። ይሁን እንጂ ባለሥጣኑ መጋቢት 30 የጀመረው የኹለተኛው የእሳት አደጋ በፓርኩ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳስከተለ እና ምን ያህል ሔክታር መሬት እንደወደመ በባለሙያዎች እየተጠና እንደሆነና አሁን ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here