በጦላይ ሲቪሎች ላይ የሚፈፀመው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት አለመቆሙ ተገለፀ

0
537

ኢሰመኮ በእስረኞች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት አውቃለሁ ብሏል

በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ሳይፈረድባቸው ለወራት በተሐድሶ ትምህርት ሰበብ በሚታሰሩ ʻሲቪልʼ ወጣቶች የሰብኣዊ መብት ጥሰት መፈፀም መቀጠሉ ታወቀ። ወደ ካምፑ የሚገቡት ታራሚዎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ከመደበኛ ማረሚያ ቤቶች ጋር እንኳን ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚነሱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በጅምላ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ወጣቶች በመደበኛ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ በፀጥታ አስከባሪዎች በሚቋቋሙ ግበረ ኀይሎች ውሳኔ እስከ ኹለት ወር በማሰልጠኛው እንደሚቆዩ ታውቋል።
የመንቀሳቀስ መብታቸውን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች የሚደርስባቸው እነዚህ እስረኞች እንደሌሎቹ እስር ቤቶች መደበኛ የምግብ አቅርቦት እንደሌላቸውና በተከታታይም ዳቦ በወጥ ብቻ እንደሚቀርብላቸው ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና ከወራት በፊት በጦላይ ታስረው የነበሩ ግለሰቦች፥ ቤተሰብ እንዲጠይቃቸው እንደማይደረግም ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማርሴ አሰፋ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ ከጨንቻ ማረሚያ ቤትና ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውጪ ያሉ ማረሚያ ቤቶችና ማቆያዎች ከፍተኛ የሆነ የሰብኣዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች መሆናቸውን አስታውቀው፣ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት የሚፈጸምባቸውን ማረሚያ ቤቶችንና ማቆያዎችን አስመልክቶ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግና ክትትሉንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአዋጅ ቁጥር 1/1987 ነሐሴ 15/1987 የወጣውና ዛሬም ሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከአንቀፅ 14 አንስቶ በክፍል አንድ ከደነገጋቸው ሰብኣዊ መብቶች ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ አንቀፅ 23 የተደረደሩት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተያዙና በሕግ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ሰዎችን የሚመለከቱ ናቸው።

ድንጋጌዎቹ ማንኛውም ሰው የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት እንዳለው፣ በሕግ በተደነገገ ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ፣ በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር) ሕገ መንግሥቱ ኢሰብኣዊና የጭካኔ አያያዝን፣ የኃይልና የማስገደድ ምርመራን ይከለክላል። የተያዙ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጠበቆቻቸው፣ ከሐኪም ጋር የመገናኘት መብት እንዳላቸው ያዝዛል ሲሉ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን አንድ ዓመት የፈጀ ፍተሻ በእሥር ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ አካሒዶ ሪፖርቱን በጥቅምት ወር 2011 ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት መኖሩን ማመላከቱ ይታወሳል።

በቡራዩ ከተማ ከተፈጠረው ግጭት እና እሱን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ወጣቶች በጅምላ ተይዘው ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ከአንድ ወር በላይ ታስረው መቆየታቸው ይታወቃል። ወጣቶቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ይህን ያህል ጊዜ በጦላይ መቆየታቸው የሕግ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል።

በሌላ በኩል ፖሊስ በተቋቋመበት አዋጅ ከተሰጠው ተልዕኮ ባለፈ ባልተሰጠው የማሠልጠን ሥልጣንና በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 177፣ 178 እና 179 ተደንግጎ የሚገኝ “አካልን ነፃ ማውጣትና” አንድ ተጠርጣሪ በተያዘ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ተደንግጎ የሚገኘው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አንቀጽ 19(3)ን የጣሰ በመሆኑ፣ ፖሊስ የፈጸመው ድርጊት ሊኮነን እንደሚገባም የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጅምላ አስሮ ሥልጠና ማስገባት የሕግ አግባብነት እንደሌለው ባወጣው መግለጫ አስታውቆ እንደነበረም አይዘነጋም። የሕግ ባለሙያው መንግሥት እነዚህን ወታደሮች አስሮ ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመላኩ የጣሳቸው ሕጎች አሉ ይላሉ።

ታደሰ (ዶ/ር) እንደሚሉት በመሰረተ ሐሳብ ደረጃ መንግሥት ሰዎችን ሰብስቦ ካሰረ፥ ያሰረበትን ምክንያት ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍቃድ መጠየቅ ይኖርበታል። በወሰደው እርምጃ የቀማው የግለሰቦችን ነፃነት በመሆኑ ይህን ደግሞ ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ማድረግ አይቻልም።

ስለዚህም ግለሰቦቹን ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ የተከሰሱበትን ምክንያት አለማወቃቸውን እንዲሁም የዋስትና መብታቸውን መነፈጋቸው በሃይማኖት አባቶችና በዘመድ መጎብኘት አለመቻላቸውን የመሰሉ ነገሮች ሲታዩ በእርምጃው ብዙ የመብት ጥሰቶች እንዳሉ ታደሰ ያስረዳሉ ብለዋል ።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here