በኢትዮጵያ የኒውክሌር ማብላያ ግንባታ በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል

0
419

መርሃ ግብሩ በኹለት ምዕራፎች የተከፈለ ነው

በኢትዮጵያ ለኃይል ግልጋሎት እንዲሁም ለግብርናና ለጤናው ዘርፍ ጥቅም ይውላል የተባለው የኒውክሌር ትግበራ መርሃ ግብርን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሦስት ዓመታት ጊዜ ገደብ ተይዞለታል። የኒውክሌር መርሃ ግብሩ በኹለት የተለያዩ ምዕራፎች እንደሚከፈል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን አማካሪ ስሜነው ከስክስ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። እንደ ስሜነው ገለፃ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲኤንኤስቲ ወይም የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል የሚባል ሲሆን ለግብርና እና የጤና ዘርፍን ለማጎልበት የሚረዱ ʻአይሶቶፕʼ ለመፍጠር እንደሚውል ተጠቅሷል።

የኹለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ኤን ፒፒ የሚል ሥያሜ ሲኖረው የኒውክሌር ኃይል ማብላያ ማለት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ለኃይል ማመንጫነት እንደሚውል ተገልጿል። ከሚንስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ጠቅላላው የኒውክሌር መርሃ ግብር በኹለት ምዕራፍ ቢከፈልም በተጓዳኝ እና በተመሳሳይ ጊዜ ግንባታቸው እንደሚካሔድ ለመረዳት ተችሏል። በዚህም መሰረት መጀመሪያው ምዕራፍ በጥቅምት ወር 2011 የቅድመ ዝግጅት ሥራው መጀመሩ የታወቀ ሲሆን በየካቲት 2014 ሥራው እንደሚጠናቀቅ ታምኖበታል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ኹለተኛው ምዕራፍ እና ለኃይል ማመንጫነት የሚውለው ደግሞ በታኅሣሥ 2012 ተጀምሮ በየካቲት 2014 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ስሜነው ስለ መርሃ ግብሩ ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ግንባታውን ለመጀመር በጣም እንደዘገየች ገልፀው በርካታ የአፍሪካ አገራት የኒውክሌር ባለቤት መሆናቸውን ጠቁመዋል። አያይዘውም ሰሜን እና በደቡብ አፍሪካ አገራት ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ በስፋት የኒውክሌር መርሃ ግብርን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ገልፀው ከምዕራብ አፍሪካም በናይጀሪያ ሠላሳ ያህል የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በባለፈው ዓመት በዛምቢያ የኒውክሌር ግንባታ እንደተጀመረ እና በአገሪቱ ከፍተኛ የማዕድን ሀብተ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ለማዕድን ዘርፍ ለማዋል እንደታሰበም አውስተዋል። በቀጣይም ሩዋንዳ የኒውክሌር ኃይል እንዲኖራት ፍላጎት ያሳየች አፍሪካዊት አገር መሆኗን ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ ስለሚገነባው የኒውክሌር መርሃ ግብር አማካሪው ሲያብራሩ፤ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መንግሥት መካከል ድርድሩ እንዳላበቃ ገልፀው፤ የሩሲያ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ወጪውን የሚሸፍንበት ወይም ከሩሲያ ባንኮች ብድር የሚያመቻችበት ሁኔታ እንዳለ አስታውቀዋል።

የኒውክሌር መርሃ ግብሩ ከዓለም ዐቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ይሁንታን በማግኘቱ የመጨረሻው ሰነድ መጋቢት 7/2011 በሩሲያ ሲቺ ከተማ ተፈርሟል። ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እና በሩሲያ አቶሚክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ጀነራል አሌክሲ ሌካቼቭ መካከል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ውስጥ የምርምር ተቋም መቋቋሙን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ካሊድ መሐመድ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የምርምር ማዕከሉንም ለመምራት በከፍተኛ ክፍያ የመጣው ጃፓናዊ ፕሮፌሰርም በተፈለገው ፍጥነት ባለማስኬዱ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን መተካቱንም ጨምረው ገልፀዋል።

ለግብርና እና የሕክምናውን ዘርፍ ለማዘመን ይውላል የተባለው የኒውክሌር ትግበራ በተለይም ደግሞ የቀዶ ጥገና ሕክምናን ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያግዛል። የማምረቻውን ዘርፍ እና የኃይል ማመንጫውንም ወደ ድብልቅ ኢነርጂ ፊቱን እንዲያዞር ያደርገዋል። ኢትዮጵያ በዋናነት በውሃ ኃይል ላይ የተወሰነ የኃይል ማመንጫ የምትጠቀም ሲሆን፤ ይህም የረጅም ጊዜ ዘላቂነቱ አጠራጣሪነቱ ስለሚያመዝን የኒውክሌር ኃይልን መጠቀም ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሚሆን ካሊድ መሐመድ (ዶ/ር) ጨምረው ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here