የፓስፖርት እጥረት ለሙሰኞች በር ከፍቷል

0
985

የፓስፖርት እጥረቱን ተከትሎ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በርካታ ኤጀንሲዎች እና አንዳንድ የጉዞ ወኪሎች በሕገ ወጥ መንገድ የድጋፍ ደብዳቤዎችን በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ደርሳበታለች።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ክፍለ ከተሞች፣ የጉዞ ወኪሎች፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አሰሪ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እና አንዳንድ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ባልደረባዎች በሕገወጥ ትስስሩ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው የዳሰሳው ዝርዝር ያስረዳል።

አንድ ዜጋ ፓስፖርቱን ማደስ ወይም አዲስ ማውጣት ሲያስፈልገው ጉዞ ለማድረግ ማቀዱን የሚያረጋግጡ ምክንያቶች እንዳሉት በሰነድ ማስደገፍ ግዴታ ሆኖ መቀመጡ ለሕገወጦቹ ሠፊ በር ከፍቷል። አንድ የድጋፍ ደብዳቤ ለማፃፍም ከ3 ሺሕ ብር እስከ 5 ሺሕ ብር ኢሚግሬሽን ደጃፍ ከሚገኛው ፖሊስ ጣቢያ አንድ ሜትር ሳይርቁ ጭምር ተቀምጠው በሚሠሩት ደላሎች አማካኝት ይጠየቃል።

የ29 ዓመቷ አሚና (ሥሟ የተቀየረ) የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ መግቢያ በር ላይ የሚገኘው የመረጃ መጠየቂያ ባልደረባ ፓስፖርቷ ለመታደስ የውጪ አገር ጉዞ ለማረድረጓ ማስረጀ ማምጣት እንዳለባት ደጋግሞ እያስረዳት ይገኛል። ነገሩ ግራ የሆነባት ወጣት ችግሯን ደጋግማ ብታስረዳውም ሰሚ ያገኘች አይመስልም። ከጉዞ ማረጋገጫው በተጨማሪ የቀበሌ መታወቂያ እንደሚያስፈልጋት የተነገራት አሚና ተስፋ ሳትቆርጥ መታወቂያ እንደሌላት እና ከባንክም ገንዘብ ማውጣት መቸገሯን ትናገራለች።

ገና 18 ዓመት ሳይሞላት ነበር ከትውልድ አካባቢዋ ለሥራ ወደ ከተማ የወጣችው። ታዲያ ለተወሰኑ ዓመታት በሰው ቤት ተቀጥራ ያጠራቀመቻትን ገንዘብ ይዛ በምትኖርበት ወረዳ አደራጅነት ወደ ንግድ ሥራዋ ስትገባ በተጻፈላት የድጋፍ ደብዳቤ ነበር ፓስፖርቷን ማውጣት የቻለችው። ታዲያ ከባንክ ቤት ለሥራዋ ማስኬጃ ገንዘብ ለማውጣት ስትሔድ ነበር የፓስፖርቱ መጠቀሚያ ጊዜ ማለፉን የተረዳችው።

ለወትሮው ግርግር በማያጣው የኢሚግሬሽን መግቢያ እና መውጫ በሮች አካባቢ የፓስፖርት መያዢያና የዶከመንት ማቀፊያ የሚሸጡ፣ ኮንትራት ታክሲ የሚሠሩ እንዲሁም ታክሲዎቹን ተደግፈውና በየጥጋጥጉ ተቀምጠው እንደ አሚና ግራ ለገባቸው መላ አለን የሚሉት ደላሎች ሲራወጡ ማየት የየዕለት ትዕይንት ነው።

“ፓስፖርት ነው? በአንድ ቀን እናስጨርስልሻለን” የሚሉት ወጣቶች ወጪ ገቢውን ይጎተጉታሉ። መጀመሪያ የሚያቀርቡትም አማራጭ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚፃፈው እና 3 ሺሕ 500 ብር የሚያስከፍለው የትብብር ደብዳቤ ነው።
ድጋፍ አንድ – በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ደላሎች እንደሚሉት እንደ ፓስፖርት ፈላጊው ሰውነት እና የዕድሜ ሁኔታ እየታየ ለተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ወደ ውጪ አገራት እንደሚሔዱ ተደርጎ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ካለ ባልደረባ የሚጻፈው ደብዳቤ ፈጣን አማራጭ ነው። ምንም እንኳን የተባለውን ሰው ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም እራሱን ከቀነኒሳ በቀለ እና ሞ ፋራህ አሰልጣኞች ጋራ ቅርበት ያለው በማለት በተደጋጋሚ በደላሎቹ ያስነግራል።

በአካል ለመገኘት አስቸጋሪ የሆነው ይህ ሰው በሰዓታት ውስጥ ሥራውን አጠናቆ የግብዣ ደብዳቤውን ያስረክባል። እንደ ቻይና ኤንባሲ ያሉ እና ቪዛ ለማገኘት ግብዣ ከሚያስፈልጋቸው አገራት ኢምባሲዎች አካባቢ በቋሚነት ይህንን ሥራ የሚያከናውኑ ግለሰቦች ለዓመታት መተዳደሪያቸው አድርገውት የቆዩ ቢሆንም ዋጋቸው ከ500 ብር ብዙም ያልበለጠ እንደሆነ መረጃዎች ጠቁመዋል።

አንድ መደበኛ ፓስፖርት ለማግኘት ከሚከፈለው ክፍያ ጋራ ሲደመር አጠቃለይ ወጪው ወደ 4 ሺሕ 400 የማድረሱ ጉዳይ የደላሎቹን ግብዣ እንደ አሚና ላሉ ሰዎች የማይሞከር አድጎታል። ነገር ግን ቁጥራችው ቀላል የማይባል ግለሰቦች አገልግሎቱ እስከ ቤታቸው ድረስ እንደሚሔድላቸው ከደላሎቹ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ድጋፍ ኹለት – የብቃት ማረጋገጫ
ኹለተኛው አማራጭ ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አረብ አገራት ለሥራ ለሚሄዱ ሠራተኞች የፈቀደችውን መንገድ በመጠቀም የሚሰጥ የብቃት ማረጋገጫ ነው። የብቃት ማረጋጋጫ ከሦስት ወር መሰረታዊ ሥልጠና በኋላ የሚሰጥ ቢሆንም ከ3 ሺሕ እስከ 3 ሺሕ 500 ብር በመክፈል በደላሎቹ አማካኝነት የብቃት ማረጋገጫው በአንድ ቀን ውስጥ ተሰርቶ ይመጣል።

ድጋፍ ሦስት – የጉዞ ወኪሎች
ከሕጋዊ የጉዞ ወኪሎች የሚገኘው ሌላኛው አማራጭ ደግሞ እስከ 5 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚያስከፍል አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተጠቃሚዎች ተናገረዋል። ጋዜጣችን በሠራችው ዳሰሳም የተባለው ገንዘብ እስከሚጠየቅበት ደረጃ ድረስ ለመድረስ ባትችልም ለተለያዩ ሃይማኖታዊ ጉዞዎች በሚል ሽፋን በሚጸፉ የድጋፍ ደብዳቤዎች ፓስፖርቱ እንዲወጣ ወይም እንዲታደስ ማድረግ እንደሚቻል አረጋግጣለች።

በተለይም ወደ እስራኤል የሚደረገው ሃይማኖታዊ ጉዞ በመሆኑ ተመራጭ እንደሆነ ጋዜጣዋ ያደረገችው ምልከታ ያስረዳል። የጉዞ ወኪሎቹ ከሚጠይቁት ጉርሻ ባለፈ ተገልጋዩ ሊያደርግ ያሰበውን ጉዞ በእነርሱ አማካኝነት ማድረግ እንዳለበት ከሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ነው።

ድጋፍ አራት – በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የአሰሪ እና ሠራተኛ የሚያገናኙ ወኪሎች
የፓስፖርት እጥረቱን አባብሰውታል ተብለው ከሚጠቀሱት እና የኢሚግሬሽን ሠራተኞች ተሳትፎ እንዳለበት ጭምር የሚጠቀሰው በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የአሰሪ እና ሠራተኛ አገናኝ ወኪሎች ለአንድ ግለሰብ እስከ 3 ፓስፖርት እንዲወጣ በማድረግ በተለያዩ አገራት ሥራ ለማፈላለግ የሚጠቀሙበት መንገድ አንዱ ነው።

ተጓዦች ያልጠፋ ፓስፖርትን እንደጠፋ ሪፖርት በማድረግም ጭምር ተጨማሪ ፓስፖርት ይዘው እንዲመጡ ከአንዳንድ አሰሪ እና ሠራተኛ አገናኝ ወኪሎች እንደሚጠየቁ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ድጋፍ አምስት – የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ ሠራተኞች
የፓስፖርት እጥረቱ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የኢሚግሬሽኑ ባልደረቦች ጉርሻ መጠየቅ መጀመራቸውን ገንዘቡን ተጠይቀናል ያሉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል። ለወራት ወረፋቸውን ከጠበቁ በኋላም ፓስፖርታቸው መጥቶ እንዳዩት ነገር ግን አልደረሰም በሚል የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ ሆን ብለው እንዳጉላሏቸው እና በመጨረሻም ጉርሻ መጠየቃቸውን ማንንታቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት ግለሰብ ተናገረዋል።

እነዚህ የሙስና ተግባሮች ከሕግ እና ከአስተዳደር ጉዳይነት ባሻገርም የደኅንነት ሥጋት ምንጭ እንደሆኑ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንጋፋ የደኅነት እና የመረጃ ትንተና ባለሞያ ይናገራሉ።

በተለያዩ መደለያዎች ፓስፖርት ለማግኘት የተፈቀደላቸውን ግለሰቦች ግልጋሎት ለማፋጠን ተብሎ የሚፈፀም የሙስና ተግባር የሕግ እና የአስተዳደር ግድፈት ቢሆንም ችግሩ ሥር እየሰደደ ሲመጣ ለማይገባው ሰውም ጭምር በመስጠት በቀጥታ የደኅንነት አደጋ ወደ መሆን ሊሸጋገር እንደሚችል ይናገራሉ።

ባለሞያው ማንኛውም የሙስና ድርጊት የደኅንነት ሥጋት ሆኖ እንደሚታይ እና ከዚህ ቀደም የነበረው የፓስፖርት አሰጣጥ አገልጋሎት የተሸለ ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት ተንታኝ አሁንም የሚታዩትን እነዚህን ክፍተቶች ለማረም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የፓስፖርት እጥረቱ ካጋጠመበት ወቅት ጀምሮ ኤጀንሲው ለመጠባበቂያነት ይዞ የቆየውን ወረቀት እና ለመለበድ የሚያገለግለውን ላሚኔቲንግ ግብዓት አሟጦ መጠቀሙ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ላጋጠመው ከፍተኛ እጥረት እንደ መሰረታዊ ምክንያትነት ይጠቀሳል። ሌላው እጥረቱን ያባባሰው በኅብረተሰቡ ውስጥ ፓስፖርት ይዞ የመቀመጥ ፍላጎት ባለፉት ኹለት ዓመታት በፍጥነት እያደገ መምጣቱ እንደሆነ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ፓስፖርት ለጉዞ ሰነድነት ቢያገለግልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ መታወቂያነት መገልገልም የተለመደ እየሆነ መጥቷል። አንድ ብሔራዊ መታወቂያ በሌላት አገር ፓስፖርትን ከቀበሌ መታወቂያ ጎን ለጎን ወይም ለብቻው መጠቀም አስገራሚ አይደለም። በተለይም ፓስፖርት ላይ የትውልድ ቦታ እንጂ ብሔር ባለመጠቀሱ አንዳንዶች በተለይም በብሔራቸው ምክንያት ልዩ ለሆነ ጥቃት የሚጋለጡ መስሎ በሚሰማቸው ወቅቶች ሁሉ ፓስፖርታቸውን መጠቀም ይመርጣሉ።

የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያሳየው ፓስፖርት ከሚያወጡ ግለሰቦች መካከል ከ50 በመቶ የማይበልጡት ብቻ ለጉዞ ይጠቀሙበታል። አንድ ጊዜም ሳይጓዙ ለማደስ የሚመጡ ግለሰቦችን ማስተናገድም ለጊዜው የተገታ ሲሆን ሀብት ታባክናላችሁ በማለት እንደሚከለከሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተጠቃሚዎች ተናግረዋል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ በድንገት የሚያጋጥም ጉዞ ቢኖር ፓስፖርቱን ለማግኘት የሚያስፈለግው ጊዜ ቀላል ባለመሆኑ ቀድመው ይዘው መቀመጡን የሚመርጡ ናቸው።

የፓስፖርት ደብተር
አንድ የፓስፖርት ደብተር ለማሰናዳት የሚጠቅሙ ኹለት ግብዓቶች በተለይም ከፈረንሳይ እና ከእስኤል አገር በውድ ዋጋ ተገዝተው እንደሚመጡ የኢሚገሬሽን የቅርብ ጊዜ የግዢ ታሪክ ያሳያል። ለመለበጃነት የሚያገለግለው ላሚኔቴር እና ወረቀቱ ከውጪ አገር ከተገዛ በኋላ አገር ውስጥ ደብተሩ ይዘጋጃል።

አንድ የፓስፖርት ቅጠል ወረቀትም እስከ አንድ የአሜሪካን ዶላር ድረስ እንደሚያወጣ ቢገመትም ወደ ተጠቃሚው ሲደርስም መንግሥት ድጎማ አድርጎበት ነው። ባጠቃላይ ኹለቱን ግብዓቶች ከውጪ አገር ለመግዛት ዓመታዊ ወጪው ከ5 ሚሊዮን ዶላር እንደማያንስ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአሁኑ ወቅት አምስት ዓይነት የጉዞ ዶክመንቶች ያሉ ሲሆን የዲፐሎማት ፓስፖርት፣ ሰርቪስ ፓስፖርት፣ መደበኛ ፓስፖርት እና ሊሴ ፓሴ (የይለፍ ሰነድ) ይገኙበታል። ኤጀንሲውም በቀን እስከ 5 ሺሕ ፓስፖርት የማደል እና የማደስ አቅም ሲኖረው ባለው ፍላጎት ግን እስከ 10 ሺሕ ያክል ተገልጋዮች በመላው አገሪቱ በሚገኙ ቅርንጫፎቹ ደጅ ይጠናሉ።

የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ አወቃቀር
ለረጅም ዓመታት ባልተማከለ መንገድ ሲሰጥ የነበረው የኢሚገሬሽን አገልገሎት በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ተቋማዊ መልክ መያዝ እንደጀመረ ሰነዶች ያስረዳሉ። ሕጋዊ ተቋም በአዋጅ በማቋቋም እና ዘመናዊ ስርዓት በማላበስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋም ደረጃ ማደራጀታቸውን ታሪክ ያስረዳል። በ1980 የኢሚግሬሽን እና የስደተኞች መምሪያ ተብሎ እንደገና የተደራጀ ሲሆን በወቅቱ በአገሪቱ ከነበሩ ነውጦች ጋር ተያይዞ መምሪያው ከፍተኛ የሆነ የደኅነት መሣሪያ ሆኖ እንደነበር ይጠቀሳል።

በደኅነነት መሥሪያ ቤቱ ሥር ሆኖ ዘመናትን የተሻገረው ተቋሙ የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተደደር ባካሔደው አዲስ የመዋቅር አደረጃጀት የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ሥር ከብሔራዊ መታወቂያ ጋራ በአንድ እንዲጠቃላል ተወስኗል። እንዲሁም የስደት ተመላሾች ኤጀንሲን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ ማስከበር እና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች በሰላም ሚኒስቴር ሥር እንዲዋቀሩ መደረጉ ይታወሳል።

ኤጀንሲውን የመነጠሉን እርምጃ በበጎ ጎኑ የሚመለከቱት የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ባለሙያው ከጠቅላላ ተጓዦች መካከል ጥቂት ሰዎች ለደኅንነት አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ሥጋት ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታው የሚበልጠውን ይህንን ሰፊ የአስተዳደር ሥራ በደኅንነት መዋቅር ሥር ማድረግ ለአላስፈላጊ የሥራ ጫና ሊያጋልጠው እንደሚችል ይናገራሉ።
ይህንን ክፍተትም ለመሙላት በአዲሱ ኤጀንሲ ሥር አንድ የደኅንነት የሥራ ዘርፍ ተዋቅሮ በተጠናከረ መልኩ የመረጃ ሥራውን በማቀላጠፍ የሚጠበቁትን ችግሮች መፍታት ይቻላል ብለው ያስባሉ።

“የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ቅርንጫፍ ማብዛት የለበትም፣ ይልቁንም በዋና ዋና የምጣኔ ሀብት፣ ወታደራዊ እና ሌሎች ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ማጠንጠን አለበት” ሲሉ የደህነነት ባለሞያው ይሞግታሉ።

የሰላም ሚኒስቴር ሲቋቋምም በቂ ማብራሪያ ያልተሰጠበት ጉዳይ ነው ያሉት እኚሁ ተንታኝ፥ የሆነው ሆኖ ደኅንነቱ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተቆጣጣሪ ተቋም ማግኘቱ ግን አግባብ ነው ይላሉ። ተቋሙ ሲወቀስበት ከነበረው አንዳንድ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ውጪ ጠንካራ የሚባል መዋቅር እንደነበረው እና በአንድ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ የመገንባቱ አዝማሚያ ግን ከሙያው አንፃር የሚመከር እርምጃ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የለውጥ ሥራዎቹ መልካም ጎኖች ቢኖሩትም የመዋቅር ለውጡ ቀስ በቀስ መደረግ እንዳለበት፣ ዋና ዋና የሥራ ኃላፊዎችን መቀየር እንዳለ ሆኖ ሌላው በየደረጃው እና በጥንቃቄ መደረግ ያለበት መሆኑን አፅንዖት የሚሰጡት ጉዳይ ነው። ሥር የሰደደ ጥፋት ካጠፉትም ውጪ፣ ሁሉንም ማሰር እና መቅጣትም አግባባ እንዳልሆነ፥ ይህም እነዚህን ልዩ የሞያ ሥልጠና ያላቸውን ግለሰቦች ሞራል በመንካት ያልተጠበቀ ጉዳት ለወደፊት ማቆየት ጭምርም እንደሆነ ይናገራሉ።

“የደኅንነት ሥራ የዜጎችን ሰብኣዊ እና የሲቪል መብቶችን ሁሉ ያከበረ መሆን ቢኖርበትም፥ ከሕዝብ ደኅንነት እና ከአገር ጥቅም አንፃር ታይቶ የሚወሰዱ እርምጃዎች በየትኛውም አገር ሊኖር ይችላል” ብለዋል።

ሌላው የደህንነት ባለሞያ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እና ባልተረጋጋ አሕጉራዊ ቀጠና ውስጥ ለሚገኙ አገራት ኢሚገሬሽንን ከደኅነት መስሪያ ቤቱ መነጠል አደገኛ እርምጃ እንደሆነ ያሰምሩበታል። የየብስ ድንበራቸውን፣ የአየር ክልላቸውን እንዲሁም የሚቃጡባቸውን የሽብር ጥቃቶች በአግባቡ መቆጣጣር ባልቻሉ አልፎ ተርፎም መንግስት አልባ በሆኑ ሃገራት በተከበበች ሃገር ደህንነትን ከኢሚግሬሽን መለየት ትክክለኛ እርምጃ እንዳልሆነ ያሰምሩበታል።

የኢትዮጵያ የደኅንነት መዋቅር ከደርግ ጊዜ ጀምሮ የምሥራቅ አፍሪካን እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ የሽብር ጥቃቶችን መመከት የቻለ እንደነበር እና አሁንም በዚያው መስመር ተጠናክሮ መሄድ ሲገባው ወደ ተለያዩ ጥቃቅን ተቋማት የመከፋፈሉ ፋይዳ እንደማይታያቸው ያብራራሉ።

በቅርቡ ከአልሸባብ ጋራ ግንኙነት እንዳለው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የሚገኘው ግለሰብ ለኹለት ሳምንታት በደኅንነት ባለሞያዎች ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ከአገር ለመውጣት የኢሚግሬሽን መቆጣጠሪያውን አልፎ ወደ ጂቡቲ ለመብረር ደቂቃዎች ሲቀሩት አቬሽን አካባቢ ባሉ የደኀንነት ባለሙያዎች ተለይቶ በቁጥጥር ሥር መዋሉ የኢሚገሬሽን እና የደኅነት መስሪያ ቤቶች መካከል ያለው የመረጃ ሰንሰለት ለሴኮንድም መለያየት እንደሌለበት ያስረዳል።

በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየት እና ሕገወጥ መታወቂያ በማሰራት ከሌሎች ግበረ አበሮቹ ጋራ በመሆን የተለያዩ የሕዝብ መሰብሰቢያ አካባቢዎች ላይ ጥናት ሲያድገ መቆየቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ፀጋዬ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ በጨረፍታ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ስቴዲየም፣ አዲስ በመገንባት ላይ ያለው የንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ሕንፃ፣ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲሁም ዋና ዋና የገበያ ማዕከላት በፎቶ ግራፍ ይዞ የተገኘው ይህ ግለሰብ፥ ወደ አገር ሲገባ በሌላ አገር ፓስፖርት እንደገባ እንዲሁም ሲወጣም ያስመዘገበው ፓስፖርት የተለየ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

የ 9/11 የሽብር ጥቃት እና የኢሚግሬሽን ደኅህንነት
እ.ኤ.አ መስከረም 11/2000 በአሜሪካ መንትዮቹ የፔንታጎን ሕንፃዎች ላይ ከደረሰው የሽብር ጥቃት በኋላ አገራት የፀረ-ሽብር ዘመቻቸው በሕግ እና በአሰራር ተጠናክሮ ዘልቋል። ኃያሏ አሜሪካም ጥቃቱ ከደረሰ በጥቂት ሰዓታታት በኋላ የየብስ እና የአየር ክልልሎቿን በመዝጋት የጀመረችው እርመጃ የኢሚግሬሽን ስርዓቷ ላይ መሰረታዊ የደኅንነት ለውጦችን እስከማድረግ አደርሷታል። በሃገሪቱ በየብስ እና በአየር የሚገቡ ዜጎች ላይ በተለይም የመካከለኛው ምሥራቅ ተጓዦች እና ስደተኞች ላይ ጠንከር ያሉ የቪዛ መስፈርቶችን በማስቀመጥ ሕጋዊ የሆነውን መስመር በመከተል ሊከሰሰቱ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ይሞከራል።

በዓለም ላይም ተጓዦች እንዲሁም ስደተኞችን በሙሉ እንደ ደኅንነት ሥጋት የመመልከቱ አዝማሚያ ከፍተኛ ክርከር ከሚደረግባቸው አስተሳሰቦች መካከል ሆኖ እስካሁን ዘልቋል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተሰይመው እየጠነከሩ የመጠጡ የሽብር ተቋማት በሥፋት በሚንቀሳቀሱበት ቀጠና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አገራት ጉዳዩን በቀላሉ ባለማለፍ የተለያዩ እርመጃዎችን በኢሚግሬሽን እና ደኅነነት ተቋሞቻቸው ላይ ወስደዋል።

የመረጃ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ በሥሩ ከያዛቸው ዘርፎች መካከል የአገር ውስጥ መረጃ እና ደኅንነትን ከውጪ አገር መረጃ እና ጥናት ክፍሎች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ እንደመሆኑ የኢሚግሬሽን መነጠል ዋጋ የሚያስከፍል ውሳኔ ነው ብለው የሚሞግቱት ባለሞያው አዲስ የደኅነነት ሥጋት ምንጮች ተጨምረው የከፋ ችግር ሳይፈጠር ማስተካከያዎች እንዲወሰዱ አሳስበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here