‘ሲያምሽ ያመኛል’ በሚል ርዕስ ሦስተኛ የሙዚቃ አልበሙን ከሦስት ወር በፊት የለቀቀው ድምፀ መረዋው ጎሣዬ ተስፋዬ፥ ቅዳሜ፣ ሚያዚያ 26 ለሚያካሒደው የሙዚቃ ድግሥ 2 ሚሊዮን ብር ሀበሻ ዊክሊ ሊከፍለው ውል አስረዋል።
በተስረቅራቂ ድምጹና በአዚያዚያም ስልቱ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ እንዳኖረ ብዙዎች የሚመሰክሩለት ጎሣዬ፥ የተሰጥዖውን ያክል ግን ብዙ ሥራዎችን ባለመሥራቱ ትችት ይሰነዘርበታል። እንደማሳያም ሦስተኛ አልበሙን ኹለተኛ አልበሙን ካወጣ 11 ዓመት ቆይታ በኋላ በዚሁ ዓመት ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ መልቀቁ ይጠቀሳ።
በእስካሁኑ የሙዚቃ ሕይወቱ ‘ሶፊ’፣ ‘ሳታማኻኝ ብላ’ እና ‘ሲያምሽ ያመኛል’ የሚባሉ ሦስት አልበሞች አሳትሟል። ‘ቴክ ፋይፍ’ እና ‘ኢቫንጋዲ’ በሚል ከሙያ አጋሮቹ ጋር በጥምረት ኹለት አልበሞችም ለአድናቂዎቹ አድርሷል። በተጨማሪም ከዐሥር በላይ ነጠላ ዜማዎችን የለቀቀው ጎሣዬ፥ በተለይ ማኅበራዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑት ‘ማለባበስ ይቅር’ በኤች አይቪ/ኤድስ ዙሪያ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በኅብረት እንዲሁም ‘ለታናሿ ልስጋ’ ያለዕድሜ ጋብቻን በተመለከተ ተጠቃሽ ሥራዎቹ ናቸው። ‘አደራ’ ከትዝታው ንጉሥ መሐሙድ አሕመድ እና ‘ባላገር’ ከዝነኛው ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ ጋር በጥምረት ከአልበም ውጪ ሰርቷቸው ከፍተኛ ተደማጭነት ካገኙት መካከል ይመደባሉ።
ከአፉ ለአፍታም ሳይጠራ የማያልፈውን ባለቤቱን ገኒ (አጸደ ተስፋኹነኝ) በማለት በቁልምጫ የሚጠራት ጎሣዬ፥ አሜንና ገብርኤል የተባሉ ልጆች በትዳሩ አፍርቷል። ጎሣዬ የሕይወት አጋሩ ለሙያው እድገት የአንበሳውን ድርሻ እንደምትይዝ በመጥቀስ የአዲሱን አልበም ሽያጭና የዓለም ዐቀፍ ኮንሰርት ዝግጅቶችን የምትመራውም ራሷ ገኒ መሆኗንም ተናግሯል።
የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ድምፃዊ ጎሣዬ ተስፋዬ ለሚያዚያ 26ቱ የሙዚቃ ድግሥ ከቅላፄ ባንድ ጋር ልምምድ በሚያደርግበት ቀበና አካባቢ በሚገኝ አዳራሽ አግኝቶት ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ማለዳ፡ አዲሱ ‘ሲያምሽ ያመኛል’ አልበምህ ከተለቀቀ ሦስት ወራትን ገደማ አስቆጥሯል። ተቀባይነቱን እንዴት አገኘኸው?
ጎሣዬ ተስፋዬ፡ ከቆይታዬ አንጻር በጣም ቆንጆ ተቀባይነትን አግኝቷል ብዬ አስባለሁ። በእርግጥ ʻሳታማኻኝ ብላʼ የተባለውን አልበሜ ያወጣሁት የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ነው። ከዛ በኋላ ለአራት ዓመት በየአገሩ እየዞርኩ ኮንሰርቶችን አቅርቢያለሁ። በተቀሩት ዓመታት የአልበሜ ዝግጅት ላይ አሳልፌያለሁ።
ዞሮ ዞሮ ከ11 ዓመት ቆይታ በኋላ የመዝናኛው ዓለም እንቅስቃሴ በጣም ፈጣን በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ሰው ሲጠብቅህ የሚያኮራ ነገር ነው። ከአሁን በኋላ በእርግጠኝነት ይሄን ያክል አስጠብቃለሁ ብዬ አላስብም። ይሁንና አሁን ብዙ ያለቁ ሥራዎች በእጄ ላይ ስላሉ እነሱን እንደገና ʻማስተርʼ አስደርጌ ማውጣት ነው የሚጠበቅብኝ።
በተረፈ ለአዲሱ አልበሜ ያገኘሁት ግብረ መልስ እግዚያብሔር ይመስገን በጣም ጥሩ ነው።
እስከሁን ምንም ዓይነት የሙዚቃ ቪዲዮ አለቀቅክም። በርግጥ ‘ከእሁድ እስከ እሁድ’ በቅርብ ቀን እንደሚለቀቅ የፌስቡክ ማስታወቂያ ተነግሯል። አድናቂዎችህ መቼ ይጠብቁት?
ʻከእሁድ እስከ እሁድʼ ለተሰኘው ሥራዬ የሙዚቃ ቪዲዮ አልቋል። ምናልባትም የእናንተ ጋዜጣ ለአንባቢ በምትደርስበት ጊዜ [ቃለ መጠይቁ የተደረገው ማክሰኞ፣ ሚያዚያ 15 ነው] ለአድናቂዎቼ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ። የሙዚቃ ቪዲዮው በጣም የተለፋበትና ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚወደው ተስፋ አደርጋለሁ።
ለዘፈኖችህ የሙዚቃ ቪዲዮ በብዛት ለምንድን ነው የማትሠራው?
ስንፍና ይሁን ወይም የፍላጎት ማጣት እርግጠኛ አይደለሁም። ትኩረቴ በድምጽ ለሚሠራው (audio) አልበሜ ላይ በማድረጌ ሊሆን ይችላል። ለመጨረሻ ጊዜ የለቀቅኩት የሙዚቃ ቪዲዮ ከጋሽ መሐሙድ አሕመድ ጋር ʻአደራʼ ብዬ የሠራሁትን ነው።
ቅዳሜ፣ ሚያዚያ 26 በጊዮን ሆቴል የምታካሒደው የመድረክ የሙዚቃ ዝግጅትህን ቅላፄ ባንድ እንደሚያጅብህ ይታወቃል። ስለባንዱና ልምምዳችሁ እስቲ ንገረን።
ቅላፄ ባንድ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ሥራቸውን በማቅረብ የሚታወቁ ጎበዝ፣ ታዛዥ እና ስሜት የሚረዱ ባለሙያዎች ናቸው። ይህ በመሆኑም ነው ከእነርሱ ጋር ለመሥራት የወሰንኩት።
በነገራችን ላይ ከቅላፄ ባንድ ጋር በመጀመሪያ መሥራት የጀመርነው ከአንድ ወር በፊት የአልበም ምርቃት መርሃ ግብር ለማዘገጀት ነበር። ይሁንና ከአልበም ምርቃት ይልቅ አንደኛውኑ ኮንሰርት ቢሆን ይሻላል በሚል ዘፈኖች ጨማምረን በማጥናት ላይ እንገኛለን። የልምምድ ሰዓቱን በተመለከተ በቀን ከ3 እስከ 4 ሰዓት ጥናት እናካሒዳለን።
አድናቂዎችህ ከኮንሰርትህ ምን የተለየ ነገር ይጠብቁ?
ከዝግጅቱ በርግጠኝነት አድናቂዎቼ የተለየ ነገር ይጠብቁ። ኮንሰርቱን ያዘጋጀው ሀበሻ ዊክሊ ነው። በድምጽ (sound system) እና መብራት አጠቃቀም የተለየ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ አውቃለው። ይሄ በራሱ አንድ ለውጥ ነው።
የመድረክ ላይ ብቃትና ከአንዱ ወደ ሌላኛው ዘፈን የሚደረገው ሽግግር በተለየ ሁኔታ እንዲሆን በዝግጅት ላይ እንገኛለን። በአጠቃላይ አድናቂዎቼ ብዙ ነገር ይጠብቁ ነው የምለው።
ጎሳዬ በተሰጠው ተሰጥዖ ልክ አልተጠቀመበት፣ አባክኖታል ብለው ለሚተቹህ ምላሽህ ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር አለመርካት ሲበዛ ስንፍና ይመስላል ብዬ አስባለው። እኔ ከሙያዬ አንድም ቀን ተለይቼ አላውቅም። ዘፈን መረጣ ላይ ግን የአለመርካት ችግር አለብኝ። በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ይሔ ይመስለኛል።
አንተ እና የአንተ ዘመነኞች ከሚተቹበት ነገሮች መካከል ግጥምና ዜማ መድረስን እንደ ግዴታ መውሰዳችሁ ይገኝበታል። ከእናንተ ቀደም ያሉት አንጋፋ ዘፋኞች በዚህ ነገር አይታሙም። እናንተና ከእናንተ በኋላ የመጡት ዘፋኞች የግጥምም የዜማም ደራሲ የመሆን ዝንባሌ ያሳያሉ። ይህ ለምን ይመስልሃል፣ በጥበብ ሥራው ላይስ ተጽዕኖ አያሳድርም?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው። ለምሳሌ አንተና ካሜራ ማኑ ብትለዋወጡ የሚፈለገው የሥራ ውጤት ላይመጣ ይችላል። በፊልሙም ዓለም ከወሰድክ ራሴ ደርሼ፣ ዳይሬክት አድርጌ፣ ተውኜ፣ ቤተሰቦቼ እንዲተውኑ አድርጌ ዘመን ተሸጋሪ ሥራ እንዲሆን መጠበቅ አስቸጋሪ ይመስለኛል።
ዜማ ወይም ግጥም የመሥራት እምቅ ችሎታ ያለውና ራሱ ድምፃዊው መዝፈን የሚችል ከሆነ ዘመን ተሸጋሪ ሥራ የማይሠራበት ምክንያት የለም። ከዜማና ግጥም ደራሲዎች እየተቀበሉ ደግሞ ዘመን ተሸጋሪ የሆኑ ሥራዎች የሠሩልን ድምፃውያንን በቁጥር ልገልጽልህ አልችልም። ምናልባትም አበበ መለሰንና ይልማ ገብረአብን በዋናነት ተጠቃሽ ላደርግልህ እችላለሁ። ከቀደምቶቹ መካከል ሳህሌ ደገጎን መጥቀስ ይቻላል።
እነጋሽ ጥላሁን ገሠሠ ግጥምና ዜማ ተቀብለው በመዘፈናቸው ምንም የጎደለባቸው ነገር የለም። ይህ የሚያመለክተው ሁሉንም የእኔ ላድርግ በማለት የመስገብገብ ባሕልም ሆነ ስሜት ስለሌላቸው ዘመን ተሸጋሪ ሥራዎች አስቀምጠውልናል።
ስለዚህ አቅሙ ያላቸው ሰዎች አሁንም ይሥሩ። መወቀስ ያለባቸውም አንዳንድ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዳሉ አስተውላለሁ። “ጠዋት ተመርቶ፥ ከሰዓት መርካቶ” ዓይነት ሥራ ኪነ ጥበብን ይጎዳዋል ብዬ አስባለሁ።
አንተ በግልህ ለሙያ ነፃነት ምን ያክል ዋጋ ትሰጣለህ?
ከስቱዲዮ ጀምሮ እስከ ባንድ ጥናት ከራሴ አዘፋፈን ስሜት ባሕሪይ ውጪ ዜማ የመድረስ ዝንባሌ እንዳለኝ ይሰማኛል። አንዳንድ የሙያ ባልደረቦቼ የሠሯቸው የእኔ ሥራዎች አሉ።
የማቀናበሩም ሒደት ቢሆን እንደዚሁ ነው። ከነአበጋዝ ጋር ስቱዲዮ ውስጥ በምሠራበት ጊዜ “ይህቺን እንደዚህ ብታደርጋት ምን ይመስላችኋል?” እላለሁኝ። የሚቀበሉትን ይቀበላሉ፤ የማይቀበሉትን ደግሞ “ይህቺ በዚህ ብትተካ” ሲሉኝ አልጋፋቸውም።
እነሱም በነፃነት እንዲሠሩ፥ የእኔንም ነፃነት እንይነፍጉኝ ከመፈለግ አኳያ ነው የምሠራው። ከባንዱም ጋር ቢሆን እንደዚሁ ነው የምሠራው። ቅጡን ያጣ መሆን የለበትም እንጂ፥ ኪነጥብብ ላይ ነፃነት ያስፈልጋል።
አንተን ጨምሮ ጥሩ የመድረክ ተከፋይ እና የአልበም ሽያጭ ያላቸው ድምፃውያን፥ ልክ እንደታዋቂዎቹ ሯጮች በኢንቨስትመንት ዘርፍ በጉልህ ሥማቸው ሲነሳ አይሰማም። ይህ ለምን ይመስልሃል?
ለአገራችን ወርቅ፣ በብርና ነሐስ ከማምጣታቸው አልፎ ሕንፃ ቢገነቡ፣ አገራቸው ላይ መዋዕለ ነዋይ ቢያፈሱ እና የሥራ ዕድል ቢፈጥሩ የሚገርም ነገር አይደለም፤ መሆንም ያለበት አይመስለኝም።
እኛ እንኳን ከቅጂ መብት ችግር አንፃር ፀጉራችንንም እያከክን ቢሆን የሕንፃ መሣሪያ መሸጫ ቢኖረን እንኳን ትልቅ ነገር ነበር። ይህ የማይሆንበት ከክፍያችን አኳያ ነው። የኪነጥበብ ቤተሰብ የሚከፈለው ለኢንቨስትመንት ይሆናል ማለት በጣም ከባድ ይመስለኛል፤ ያ እንዲመጣ ግን እንመኛለን። ይሁንና ኹለቱ ዘርፎች [አትሌትና ድምፃዊ] ለንጽጽር የሚቀርቡ አይደሉም።
መጪው ፋሲካ ነው፥ እንደአባወራ በቤተሰብህ ውስጥ የበዐል ዝግጅት ተሳትፎህ ምን ታደርጋለህ?
ፋሲካ ለጎሣዬ ተስፋዬ የተለየ ትርጉም አለው። የተወለድኩት በፋሲካ ቀን ነው። አብዛኛዎቹ ሥራዎቼ ʻቴክ ፋይፍʼ፣ ʻኢቫንጋዲʼ እና ʻሳታማኻኝ በላʼ የፋሲካ ሰሞን ነው የወጡት። የባለቤቴም ልደት ከፋሲካ ጋር ይገናኛል። ይሄ ግጥምጥሞሽ ይገርመኛል። በአጠቃላይ ፋሲካ ከመንፈሳዊ ሕይወታችንም ጋር እንዲሁ ልዩ ትርጉም አለው።
የፋሲካ ውሎ ምን ይመስላል ላልከው፥ አብዛኛውን ጊዜ በበዐላት በውጪ አገር የሚኖሩ አድናቂዎቻችን ለሥራ ስለሚጠሩን እቤት የመገኘቱና በዐሉን የመታደሙ ነገር ብዙ የለም። ይህንንም ባለቤቴ ትረዳለች። አብዛኛው በዐላት ላይ የኪነጥብብ ሰውና ፓይለት ቤቱ ይገኛል ብዬ አላስብም።
ከቤተሰቤ ጋር በዐል ለማክበር በተገኘኹበት አጋጣሚ ግን ቆንጆ መንፈሳዊ ሕይወት ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ያረፈበት በዐል እንደማሳልፍ ነው የሚሰማኝ።
ወቅታዊው የአገራችንን ሁኔታ በተመለከተ ምን ትላለህ?
የምናያቸው እድገቶች እንዳሉ ሆነው እናትና አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው እና ደማቸውን አፍስሰው የከፈሉለትን አገር የምንጠያየቅበትና እንደገና እንድንገነባ ነው የምፈልገው። ያቺ አገረ ደግሞ የምትገነባው በፎቅ ሳይሆን በመተሳሰብ እና በመቻቻል ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ይቀረናል ብቻ ሳይሆን ካለን፣ ከነበረን ነገር ሁሉ እየሸረሸርነው ነው የመጣነው።
በአዲሱ ሥረዬ ውስጥ በተካተተውና የአንጋፋዋ ዓለምፀሐይ ወዳጆ ሥራ የሆነው፡-
ሰለም ይስጠን እግዜር ገናና
ከጋረደን ጥቁረ ደመና
ጊዜው ይሁን እላለሁ እኔ
የሚሆነውን ሳስተውል ባይኔ
ነው ያልኩት። ይህንን ቃል አሁንም ላጥፈው አልችልም። እግዚያብሔር ለአገራችን ሰላምና ጤና ይስጣት እላለሁ።
የእግዚአብሔር ሰጪነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሰላም የምንሰጣጠው ደግሞ እርስ በርሳችን ስንተሳሰብ ነው።
እንደመርካቶ ልጅነቴ ኦሮሞውም፣ አማራውም፣ ትግሬውም፣ ጉራጌውም፣ ወላይታውም፣ ከምባታውም ቤት አድገን፣ አኩኩሉ ተጫውተን፣ ዓመት በዐል ሲመጣ ድፎ ዳቦ ተቀብለን ያደኩ እንደመሆኔ መጠን፥ ያንን ስሜት አሁን ላይ እያየሁት አይደለሁም። ከእኛ ብርታት ጋር ያቺን ኢትዮጵያ አሁንም አምላክ ይመልስልን።
አጫጭር ጥያቄዎች
አዲሱ አልበምህን በአገር ውስጥ ምን ያክል ሲዲ ሸጥክ? በውጪ አገራትስ?
የአልበም ሽያጩን በተመለከተ ውዷ ባለቤቴ ገኒ የአንበሳውን ድርሻ ትይዛለች። ጥያቄውን ግን ለመመለስ በአገር ውስጥ ከመቶ ሺሕ በላይ ሲዲ ተሸጧል። የውጪውን የአይ ቲዩንና የዩቱዩብ ሽያጭን በቁጥር ለማስቀመጥ ይቸግረኛል።
በአገር ውስጥና በውጪ አገራት ምን ያክል የሙዚቃ ድግሥ (ኮንሰርት) ታዘጋጃለህ?
በአገር ውስጥ ከሀበሻ ዊክሊ ጋር የአዲስ አበባውን ጨምሮ 10 የመድረክ ሥራዎች በተለያዩ ከተሞች ለማዘጋጀት ተስማምተናል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ማለት ነው። [ነገር ግን] በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ ልንሠራቸው የያዝናቸውን ሥራዎች ለጊዜው አቆይተናቸዋል።
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አትላንታ ላይ ከሚዘጋጀው የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ጀምሮ ሌሎች መድረኮች ይኖራሉ። የዓለም ዐቀፉን የሙዚቃ ጉዞ የሚመለከታት አሁንም ባለቤቴ ናት።
አዲሱን አልበምህን ከማውጣትህ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በመድረክ ላይ ያቀረብከው ዘፈን የትኛውን ነው?
የሙሉቀን መለሰ ዜማ ሲሆን ዓለምፀሐይን ወዳጆን ለመቀበል በተዘጋጀው የብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ነው።
በሙዚቃ ሕይወትህ በመድረክ ዝቅተኛው እና ከፍተኛው ክፍያህ ምን ያክል ናቸው?
ዝቅተኛው ክፍያ ድሮ በገንዘብም ባይሆን በምሳ [ግብዣ] ከጓደኞቼ ጋር የሠራሁበት አለ። ከፍተኛ ክፍያው ‘ሳታማኻኝ ብላ’ አልበም ከወጣ በኋላ በመድረክ የተከፈሉኝ ሲሆኑ ክፍያዎቹ በሥራው ዓይነትና ሁኔታ ስለሚለያዩ ይሔ ነው ለማለት አልችልም።
ከአገራችን አንጋፋ ድምፃዊያን ብዙ ጊዜ ሙሉቀን መለሰንና ቴዎድሮስ ታደሰን በአርዓያነት ትጠቅሳለህ። ከዘመነኞችህ ውስጥ የምታደንቀው ወንድ ድምፃዊን ከነምክንያትህ ጥቀስ?
የማዲንጎ አፈወርቅ አዘፋፈን ደስ ይለኛል።
ከሴት ድምፃውያን መካከል የመታደንቃትስ?
የዘሪቱ ከበደ የአዘፋፈን ሒደት፣ የግጥሟ አፃፃፍ ፍሰቱና ሥሜቱ ደስ ይለኛል። ከተሰጥዖዋ አንፃር ግን ብዙ አልሠራችበትም።
‘ይታየኛል’ የሚለውንን ዘፈንህን ዜማ ከአር ኬሊ ‘when a woman loves’ ጋር ይመሳሰላል ለሚሉት ምላሽህ ምንድን ነው?
ከቴክ ፍይፍ ጀምሮ ልብ ብለህ እንደሆነ የነማርክ ሞሪሰንን፣ የነፒዲዲን ሪሚክስ ሥራዎች ተጠቅመያለሁ። በተለይ የአር ኬሊ አዘፋፈንና የዜማ ፍሰት በጣም ደስ ይለኛል። ከዜማና ግጥም ደራሲ ዓለማየሁ ደመቀ ጋር ተነጋግረን የሠራነው ሥራ ነው። ‘ይታየኛል’ን በአር ኬሊ ሥራ ተነሳስቼ ነው የሠራሁት።
ቀጣዩን የሙዚቃ አልበምህን አድናቂዎችህ መቼ ይጠብቁት?
እድሜና ጤና ይስጠኝ እንጂ ከአሁን በኋላ ዐሥራ አንድ ዓመት አልጠብቅም።
ይፋዊ የማኅበራዊ ገጽ አለህ?
አዎ! በዚህ አጋጣሚ በታዋቂ ሰዎች ሥም የተሳሳተ የውሸት አድራሻ እየከፈቱ፥ የውሸት መረጃ የሚያሰራጩን እንታቀቡ እመክራለሁ። ከዚህ በፊት በእኔ ሥም በተከፈተ አድራሻ ሃይማኖቱን ቀየረ በሚል የተሳሳተ መረጃ ተሰራጭቶ እንደነበረ ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011