የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ በኹለት የግል ባንኮች በኩል ሊፈፀም ነው

0
654
  • ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ጡረተኞች በመላው አገሪቱ ይገኛሉ

የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ከአዋሽ ባንከ እና ከአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር ውል ተፈራርሞ ለተገልጋዮች ክፍያ መፈፀም እንደ ጀመረ አስታወቀ፡፡ አዋሽ ባንክ ክፍያውን በመላው አገሪቱ ባሉት ቅርንጫፎች መፈፀም የጀመረ ሲሆን አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡
በኤጀንሲው የቡድን መሪ የሆኑት ሐሰን መሐመድ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የተገልጋዮችን ድካም ለመቀነስ በአገሪቱ ለሚገኙት ከ700 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የጡረታ ተከፋዮች መሥሪያ ቤቱ በየወሩ በተለያዩ አማራጮች ክፍያ ለመፈፀም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ ቀደም ደንበኞቻችን ክፍያውን የሚያገኙት በኮሜርሺያል ኖሚኒስ በኩል ሲሆን ድርጅቱ ኀላፊነት በዝቶብኛል ሲል ውሉን ማቋረጡ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀን ከኅብረት ባንክ፣ ከአቢሲንያ ባንክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውል በመፈራረም አገልግሎት እየሰጠ ነው” ሲሉ ሐሰን ተናግረዋል፡፡

ከዛም ባሻገር የጡረታ አገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑ ግለሰቦች አላስፈላጊ የሆኑ ድካሞችን ለመቀነስ ከአዋሽ ባንክና ከአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር ውል ተፈራርመው በአጭር ግዜ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኹለት የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሲኖሩ አንዱ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ነው፡፡ ኤጀንሲውም የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጁን ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 203/2003 የተቋቋመ የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡

የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በ1950 የጡረታ ሚኒስቴር በመባል የተቋቋመ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ እስከ 1953 የአገሪቱ የጡረታ ስርዓት ሲጠና ቆይቶ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ላገለገሉ ሠራተኞች ባወጣው ጡረታ መሠረት የ1953 የመንግሥት አገልግሎት ጡረታ ጉባዔ በመባል ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በተለያየ ግዜ፣ ሥያሜና አደረጃጀቱን ሲለዋውጥ የቆየው መሥሪያ ቤቱ በ1988 የማኅበራዊ ዋስትና ባለሥልጣን በመባል የሚታወቅ ሲሆን በ1998 ጀምሮ በአዋጅ ቁጥር 495/98 ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በመባል ተቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here