የሽግግር ጉዞ፡ ያለፈውን እና መጪውን ምልከታ

በዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የፖለቲካ ለውጥ አንደኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀ ዝግጅት አገሪቱ ያሳለፈችው ጊዜና ወደ ፊት መሔድ የሚገባት መንገድ በተመለከተ ውይይት ተደርጎ ነበር። አስማማው ኀይለጊዮርጊስ ውይይቱን በአጭሩ እንደሚከተለው ያስነብቡናል።

ለበርካታ ወራት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ በኢትዮጵያ የተከሰተው የአመራር ለውጥ የብዙ አገራት ትኩረትን መሳቡ ይታወቃል። ብዙዎች የላቀን ተስፋ ያሳደሩበት ሽግግር የተለያዩ ፈተናዎች እየተጋረጡበት ሲጀመር የነበረውን የተለጠጠ ተስፋ አሁን ላይ ማግኘቱ አዳጋች ነው። የሆነው ሆኖ ግን በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የለውጥ ጉዞ አንድ ዓመት መድፈኑን ተከትሎ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት የሽግግር ሒደቱን የተመለከቱ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ እንዲሁም የአንድ ዓመቱን ጉዞ የሚመለከቱ ስብሰባዎች እየተካሔዱ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በዋሽንግተን ዲሲ “የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጅማሮ ከዓመት በኋላ፥ ያለፈውን እና የመጪውን ጊዜ ምልከታ” በሚል ርዕስ ተከናውኗል።

ስብሰባው ከአሜሪካን የኮንግረስ እና ሴኒት ተወካዮች፣ ከስቴት ዲፓርትመንት፣ ከጆንሆፕኪንስ፣ ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲን ከመሳሰሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከሶሊዲያሪቲ ሴንተር እና ከሌሎችም በርካታ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በርካታ እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል። ስብሰባው በአሜሪካ መዲና ይካሔድ እንጂ ንግግር አቅራቢዎቹን ከምታስተዋውቀው የስብሰባው አስተባባሪ በቀር ሁሉም የዚህ ስብሰባ ጥናት አቅራቢዎች ኢትዮጵያን በቅርብ የሚያውቁ፣ ከፊሎቹ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ለዚህ ስብሰባ የመጡ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል አስተማሪ የነበሩ ምሁራን ጨምሮ ያሳተፈ በመሆኑ የተለየን ትኩረት ለስብሰባው አስችሮታል።

የዲሞክራሲያዊ ሽግግሩ ከዓመት በኋላ
በዚህ ስብሰባ ላይ በተለይ የዛሬ ዓመት ገደማ የነበረው ለውጥ በጣም አስገራሚ እና የብዙዎችን አድናቆት የተቸረው ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች፣ የፀጥታ መዋቅሮች ተዳክመው የዜጐች ደኅንነት በተለያዩ አካባቢዎች አደጋ ላይ መውደቁን ተከትሎ የሽግግሩን ሒደት አጉል ጥላ እንዲያጠላበት ማድረጉ እንደ ዋነኛ ተግዳሮት ተወስቷል። ይሁን እንጂ በለውጡ አመራሮች የተወሰዱት በርካታ ገንቢ እርምጃዎች አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድታመራ የሚያስችሉ ስለመሆናቸው በስፋት ተወስቷል። በተለይ ሰብኣዊ መብትን ከማስጠበቅ አንፃር በርካታ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ ጋዜጠኞች በነጻነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደረጉ፣ በፖለቲካ ማሻሻያ በሽብር የተፈረጁ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ አገር ተመልሰው እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱ፣ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸው እና በሒደት ላይ መሆናቸው እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት ከገዢው ፓርቲ ታማኞች ይልቅ በቀድሞው አመራር በግፍ የታሰሩ እና ለሰብዓዊ መብት መከበር በፅናት የታገሉ ዜጐች እንዲመሯቸው እየተደረገ መሆኑ የሽግግሩ ወቅር ዋነኛ በጐ የለውጥ እርምጃዎች ተደርገው ተወስተዋል።

በስብሰባው ላይ ቀዳሚ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሣሁን ፎሎ በአገሪቱ ያለውን በጐ የለውጥ ጅምር ወደ ላቀ የስኬት ደረጃ ለማድረስ የኅብረተሰቡ መለወጥ ቁልፍ ቦታ ሊቸረው እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዚህ ደግሞ ከላይ ያሉት አመራሮች መለወጡ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ለውጡ እታች ድረስ ለመውረድ እንደሚገባው እና በተለይ በቀጥታ ማኅበረሰቡን የሚያገኙት አመራሮችን እታች ድረስ ወርዶ በሚገባ መለወጥ ካልተቻለ በቀር ሽግግሩ የታሰበለትን ግብ ሊመታ የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደማይችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ እርምጃ ጋር በተያያዘም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያለ ጠንካራ ሲቪል ማኅበራት ሊኖር ስለማይችል በመንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዚህ ረገድ የላቀ ሚናን መጫወት ያለባቸው ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

የፍሪደም ሀውስ ሲኒየር ፕሮግራም ኦፊሰር ዮሴፍ ባድዋዛ በበኩላቸው ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር የተወሰዱትን ጠቃሚ እርምጃዎች በማድነቅ በአሁኑ ወቅት ግን ሽግግሩ ያለበት ሁኔታ “በጣም አሳሳቢ” መሆኑን አውስተዋል። ፊሪደም ሀውስን ከመቀላቀላቸው በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ካውንስል ዋና ጸሐፊ የነበሩት ካሣሁን “በሕይወት መኖር ከማንኛውም ነገር በላይ ይቀድማል” በማለት በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱን ታጣቂዎች በሚገባ መቆጣጠር እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ለመግታት መንግሥት ፈጣን እርምጃ ካልወሰደ በቀር የአገሪቱ ሰላም እና ፀጥታ ከዚህ እየከፋ ሊሔድ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

“በፍርሐት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አሉ”
ከበርካታ ዓመታት ከአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የተለያዩ ክልሎችን በመጐብኘት ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ከዕድሜ ባለጠጎች ሆነ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በስፋት ለመወያየት መቻሉን ያወሳው የ‘ሶሊዳርቲ ሙቭመንት ፎር ኤ ኒው ኢትዮጵያ’ መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር አባንግ ሜቶ ለውጡ ሲጀመር መላው ማኅበረሰቡን በነቂስ ለማሳተፍ የቻለ እንደነበር በማስታወስ፥ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች እየተከሰተ ያለው የብሔር ግጭት ከመቼውም ጊዜ ባላነሳ አገሪቱን ለአሳሳቢ ሁኔታ እንደዳረጋት አስምሮበታል። ከሱ የትውልድ አካባቢ ጋምቤላ አንስቶ እስከ ሐረር ድረስ የተለያዩ ግጭቶች መታዘቡን በመጠቆም እንዲህ ያለውን የሽግግር ሔደቱን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ኅልውና ጭምር አደጋ ላይ ሊጥል የሚችለውን ብጥብጥ ለማስቀረት “ከብሔር ፖለቲካ ተላቆ በኅብረ ብሔር ፓርቲ መደራጀት እንደሚገባ” በፅኑ አሳስቧል።
“በኢትዮጵያ በነበረኝ ቆይታ ከምንም በላይ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖ ያገኘሁት የብሔር ግጭትን ነው።” ያለው ኦባንግ በአንፃራዊነት በአዲስ አበባ ያለው ዓይነት ነጻነት በሁሉም ክልሎች እንደሌለ አውስቷል። ይህ የሆነው “በብሔር መከፋፈሉ በመብዛቱ ነው” በማለትም ኦባንግ በአንዳንድ ክልሎች “ዜጐች በገዛ አገራቸው ወደ እኛ ክልል ምን ልታደርጉ መጣችሁ? ክልላችንን ለቃችሁ ውጡ እየተባሉ ከነገ ዛሬ ምን ይገጥመን ይሆን? በሚል በፍርሐት ውስጥ እንዲኖሩ ተደርገዋል” በማለት በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ለውጦች ቢመጡም ዜጐች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር እና ሀብት የማፍራት መሠረታዊ መብታቸው ባስተማማኝ ደረጃ ተከብሯል ለማለት በእጅጉ አዳጋች መሆኑን ጠቁሟል።

አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚገኙ አራማጆችን በተመለከተም “እነሱ በሰው አገር ሲኖሩ የማንኛውም ሰው መሠረታዊ መብት ተጠብቆላቸው ነው። ቅድመ ሁኔታውን ሲያሟሉም ዜጋ የመሆን ዕድል ሁሉ አላቸው። ይሄንን ዓይነት ዕድል በሰው አገር እያገኙ የገዛ አገራቸውን ዜጋ በብሔር ስላልመሰላቸው ብቻ ሰፋሪ ማለታቸው በጣም አሳዛኝ ነው” በማለት ውጪ አገር ያሉ አራማጆች ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ ማኅበረሰቡን አንድ በሚያደርጉ እና ለአገሪቱ የላቀ ፋይዳን በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ጠቁሟል። በአጠቃላይ ሽግግሩን ለስኬት ለማብቃት እና አገሪቷን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በዋነኛነት “በአንዱ ላይ የደረሰ ጥቃት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰ ጥቃት መሆኑን ማመን የወደፊቷ ኢትዮጵያ መርሕ ሊሆን ይገባዋል” ሲል ሐሳቡን ቋጭቷል።

የአፍሪካ ሲቪል ሊደርሺፕ ፕሮግራም ፕሬዝዳንቱ ሰይፈ አያሌው በበኩላቸው የባለፈውን ዓመት የሽግግር ጉዞ በስፋት የቃኙት በአገሪቱ እየተካሔዱ ካሉ የሕግ ማሻሻያዎች ላይ ልዩ ትኩረትን በማድረግ ነበር። በአጠቃላይ በአዲሱ አመራር እየተወሰዱ ያሉትን የሕግ ማሻሻያዎች በእጅጉ ያደነቁት እጩ ዶክተሩ “አሁን በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች በዋነኛነት ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሕጐች በማሻሻል ላይ ነው። በአጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ግንባታ አንፃር ሲታይ አሁን እየተኬደበት ያለው መንገድ በጣም የጅማሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ (Early stage) ነው” ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

እንደ ሕግ ምሁሩ ሐሳብ ከሆነ የሕግ ማሻሻያው ዐቃቤ ሕግ ሥር በተቋቋመው የሕግ ማሻሻያ ካውንስል ብቻ መደረጉ የሕግ ማሻሻያዎች በዋነኛነት በፌደራል ደረጃ ብቻ እንዲወሰን በማድረግ ከታች ጀምሮ በየደረጃው ሊኖር የሚገባውን ሰፊ ሕዝባዊ ውይይት በማስተናገዱ ረገድ ክፍተት መፈጠሩ እንደማይቀር ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

በተለይ የሕግ ሪፎርሙ መነሻው እና መድረሻውን ያሉትን ጥቂት አፋኝ ሕጎች ማሻሻል ላይ ማድረጉን የተቹት የሕግ ምሁሩ በተለይ በአገሪቱ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በአጠቃላይ አገሪቷ ያሏትን ሕጐች በስፋት የመዳሰስ እና ያሉትን ማናቸውንም ሕጐች ማሻሻል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ሕጎችን በማርቀቅ በየደረጃው በሚመለከታቸው አካላት ውይይት የማድረግ ባሕል ሊዳብር እንደሚገባ ገልጸዋል። በተለይም መንግሥት ሕጐቹን ለማሻሻል ያሳየውን ፍላጎት በዋንኛነት ሕጐቹን በአግባቡ በመተርጎም ረገድ የላቀ ቁርጠኝነት ማሳየት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

በመጨረሻም ከስብሰባው ተካፋዮች “አሜሪካን ተገቢውን ድጋፍ እያደረገች ነው?” ከሚለው አንስቶ “የሽግግሩ የወደፊት ሒደት ምን ያህል አስተማማኝ ነው?” እስከሚለው መሠረታዊ ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጐባቸዋል። በአጠቃላይ የስብሰባው ድባብ ላይ የነበሩ ሐሳቦች ሽግግሩ መነሻው በጣም አስገራሚ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ለውጡ በሳል አመራርን ከቁርጠኛ እርምጃ ጋር የሚሻ በመሆኑ የለውጡ አመራር የአገሪቱን ሽግግር ወደ ውጤት ለማድረስ በእጅጉ መትጋት፣ እና ውሳኔን ለማሳለፍ በቶሎ መቁረጥ እንዳለበት ተወስቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here