ፀጋዬ ገብረመድኅን ቀዌሳ (ሎሬት)

0
977

ይህ ቃለ ምልልስ ፀጋዬ መድኅን (ሎሬት) ከዌንዲ ላውራ ጋር ለኢትዮጵያን ሪቪው እ.ኤ.አ. በ1998 ያደረገው ቃለ ምልልስ ትርጉም ነው።
ተርጓሚው ጥላሁን ግርማ አንጎ ትርጉሙን በግጥሞቹ አዋዝተዋቸዋል።

ከግጥምና ጸሐፌ ተውኔቱ ፀጋዬ ገብረመድኅን በተሻለ ለኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ታላቅነት ተምሣሌት ሊሆን የሚችል የለም። ከ1960ዎቹ አንስቶ የኢትዮጵያውያን ምሁራን መሪ ሆኗል። ፀጋዬ የተዘበራረቀውን የኢትዮጵያ ታሪክ መልክ ለማስያዝ ሞክሯል። ዛሬ ላይ እርሱ ማለት የአገር ሀብት ነው።

ፀጋዬ በ1936 እንደ ኢትዮጵያ ከተቀየጠ ቤተሰብ ተወለደ። በአባቱ በኩል ጦረኛ ሲሆን በእናቱ በኩል ደግሞ ከካህን ይመዘዛል። ፀጋዬ ከአማራና ከኦሮሞ ቤተሰብ ተወለደ። በገጠር ተወልዶ በከተማ ያደገ ነውና በቅኔ ትምህርት በፍቅር በወደቅበት በቤተክርስቲያን ትምህርት ቀስሟል። ከዚያም “ፓንቶማይም” በተባለ የምዕራባውያን ድራማ ጋር የተማረከበት የብሪቲሽ ትምህርት ቤት ተቀላቅሏል። ዕድሜ ልኩን ሌሎች እንደ ልዩነት የሚቆጥሯቸውን ባሕሎች በቀጫጭን ገመዶች ለማሰናሰልና ዝምድናን ሊፈጥር ሲሞክር ኖሯል።

ዕድሜው ዐሥራ አምስት እንደሞላ የመጀመሪያ ተውኔቱን ጽፏል። የተለያዩ ነጻ የትምህርት ዕድሎችን አግኝቶ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ቴአትሮች ሔዶ ከተመለሰ በኋላ በወቅቱ አዲስ የነበረውን ብሔራዊ ቴአትር በዳይሬክተርነት አግልግሏል። ፀጋዬ ከዚያ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ የቴአትር ዘርፍ ዋነኛ ምልክት ሆኗል። በ1960ዎቹ ተከታታይ የመድረክ ተውኔቶችን ጽፏል። አዘጋጅቷል። በዚህ ወቅት ነበር አንድ ሐያሲ ፀጋዬ የኢትዮጵያን የቴአትር ዓውድ እንደቀየረው የተረዳው።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቀድሞ ፕሮፌሰር የነበሩት ጃኔ ፕላስቶው “በኢትዮጵያ አዲስ የድራማ መንገድን ያስተዋወቀው ፀጋዬ ነው” በማለት ይገልጻሉ። አዲሱም መንገድ በቁም ነገር የተሞላ፣ ወደ ሥነ ግጥም ያደላና በዋናነት ከቤተክርስቲያን የሞራል አስተምህሮና ከከበርቴው ጭቆና መሣሪያነት ያፈነገጠና ድሃው ማኅበረሰብ በሚኖረው የጉስቁልና ኑሮ ላይ ያተኮረ ነበር።

በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ረዣዥም ሰልፎችን ተሰልፎ ቴአትሮችን መመልከት ቢጀምርም፥ መንግሥት በተደጋጋሚ ሥራውን ሳንሱር ያደርግበት ነበር። ፀጋዬ በሥራው ምክንያት በ1970 ከኀላፊነቱ የተነሳ ሲሆን በ1974 በድጋሚ በዳይሬክተርነት ተሹሟል። ይሁን እንጂ መንግስቱ ኀይለማርያም፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት (ኢሕአዴግ) እንደሚያደርገው ሁሉ የፀጋዬን የተውኔት ሥራዎች አገደ።

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ፀጋዬ ወጥ ሥራዎችን በማቅረብ ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያኑን ቀደምት የጥበብ ሥራዎችንና ግጥሞችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ተርጉሞ ያቀርብ ነበር። ለሥራዎቹም የኢትዮጵያ የግጥም ሎሬት የሚለውን ማዕረግ ጨምሮ ብዙ ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል። ብዙ ምሁራን በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ማግኘት ይገባው ነበር ሲሉ ይሞግታሉ። ያም ሆኖ ፀጋዬ ሁሌም ተመስጋኝ ብቻ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ለውጭ አገር ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ያስቸግራል፤ አድናቂዎቹ ብዙዎቹን ሥራዎቹን አንብበው ለመረዳት ይከብዳቸዋል። የሥራ ባልደረቦቹም አብረው ለመሥራት ይቸገራሉ።

ይሁን እንጂ ፀጋዬ ከማንም የተሻለ የኢትዮጵያ ባሕል ጠበቃ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀደምና በውስጧ በተደበቁ እምቅ ቃላት ላይ እምነት ነበረው።

በጁላይ 1998 የኢትዮጵያ አርቲስቶችን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ ተጉዤ ነበር። በወቅቱ ፀጋዬን የማናገር ዕድል አገኝ ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጌ የነበረ ሲሆን የጤናው ሁኔታ ጥሩ ባይሆንም በሚያስደስት ሁኔታ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ሆነ። በማግስቱ ታክሲ ተኮናትሬ ቀለል ያለ የአትክልት ሥፍራ ወዳላትና ሕፃናት ወደ ሚቦርቁበት ቤቱ ሔድኩ። ፀጋዬ የተጎዳ እግሩን አንጠልጥሎ ከፒያኖው ፊት ለፊት ተቀምጦ ጠበቀኝ። ወደ ፊት ካዘነበለው ትከሻው ላይ ነጭ ሸማ ተጎናፅፏል። ግርማ ሞገሳዊ ግንባሩና መርማሪ ዓይኖቹ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያነበብናቸውን የጥበብ ሰዎች ያስታውሳሉ።

ቃለ መጠይቁን ከጀመርሁ በኋላ ሌሎች ሰዎች ለምን “ፀጋዬን ቃለመጠይቅ ማድርግ ከባድ ነው” እንደሚሉ ተረዳሁ። ፀጋዬ ሊያወራ ስለፈለገው ነገር እርግጠኛ የሆነ መረዳት ስላለው ንግግሩንና አስተያየቱን እስኪጨርስ ድረስ ማንም እንዲያናጥበው አይፈቅድም። ይሁን እንጂ ይሄ ለእኔ ምንም ማለት ነው። ፀጋዬ ሕይወቱን በሙሉ ምዕራባውያን ስለ አፍሪካ የጻፉትን፣ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢትዮጵያን የጻፉትን ሲያነብብ ኖሯል። ይሄ ታላቅ ስጦታ ነው።

ዌንዲ፦ ዛሬ በመሃከላችን አንድ ሰው ቢገኝና ያ ሰው አሜሪካዊያንና ምዕራባውያን ስለ ኢትዮጵያ የሚያስቡትን ዓይነት አመለካከት ያለው ቢሆን የኢትዮጵያን ታሪካዊ አስፈላጊነትና ታሪካዊ ሚና እንዴት አድርገህ ታስረዳዋለህ?
ፀጋዬ፦ ወዳጄ እውነቱን ማወቅ አለብህ። እውነትም ነጻ ያወጣሃል። የሰው ልጆች መገኛ እዚህ ነው። የሰው ልጅ መጀመሪያ እዚህ ነው። ያንን መካድ አትችልም። አርኪዎሎጂስቶች፣ ጂኦሎጂስቶች በየቦታው ሲቆፍሩ ኖረው የሰው ልጅ መገኛ መሆናችንን የሚያረጋግጥ አጥንት ያገኙት እዚህ ነው። እናም ያ ሰው ሲያንቀላፋ አልኖረም። ከተፈጠረበት ዕለት አንስቶ እርሱም ሲፈጥር ኖሯል። እናም የዚያ ሰው ቅርስ፣ የቅድመ እህቶቻችን ቅርስ፣ የዓለምም ቅርስ ነው።

እራስህን ማወቅ የምትጀምረው ከመሐል መንገድ አይደለም። ከአውሮፓ አትጀምርም። ምክንያቱም አውሮፓም የአፍሪካ ጥንስስ ናትና። የተጠነሰሰችውም ከኢትዮጵያና ከግብፅ ነው። አፈ ታሪክ የተጀመረው በግብፅና በኢትዮጵያ ነው። ጳጳሱ የሚደፉትን አክሊል ብታይ እንኳን ድርብ አክሊል ነው። ይሄንን አክሊል ፈርኦኖች ከ5 ሺሕ ዓመት በፊት ደፍተውታል። ዛሬም ተመሣሣይ ባሕል እየተገበርን ልንክደው እንሞክራለን።

አሜሪካዊውን በየዓመቱ ጁላይ 4 ቀን በዋሽንግተን የሚከበረውንና አሜሪካውያን የአክሱም ሐውልት በሚመስለው የዋሽንግተን ሐውልት ዙሪያ የፀሐይን መቅደስ ሲያመልኩ እንዲመለከት እነግረዋለሁ። አሜሪካውያን የፀሐይን መቅደስ ከሮማውያን ተዋሱ። ሮማውያን ከግሪኮች ተዋሱ። ግሪኮች ከኢትዮጵያና ከጥቁር ግብፃውያን ተዋሱ። ሁሉም አንድ የፀሐይ መቅደስ ነው። የጥቁር ግብፃውያን፣ የአክሱማውያንም በለው የኢትዮጵያውን ሁሉም አንድ ነው። በፀሐዩ መቅደስ ዙሪያ የሚነድደው የችቦ እሳት የጥቁሮች ልማድ ነው። ድንጋዩ የእኔ ድንጋይ ነው። ፀሐዩ መቅደሴ ነው። የጋራ ቅርሳችን ነው።

ስለሆነም ለአሜሪካዊው ወዳጄ ምንም አዲስ ነገር ይዞ እንዳልመጣ እነግረዋለሁ። እናንተ ምዕራባውያን በተሻለ ቴክኖሎጂ ትደግሙት ይሆናል። ዛሬም የፀሐይ መቅደሴን እያመለካችሁ ነው። እኛ አንድ ነን። እናም እዚህ ሲመጣ ቅርሱን እንዲፈልግ እነግረዋለሁ። የቅም አያቶቹን ቅርስ እንዲፈልግ አሳስበዋለሁ። አፈታሪካችንን እንዲያጠና እመክረዋለሁ። የአያቶቹን ዱካ እንዲከተል እነግረዋለሁ። ይህ ምድር የጥንታዊው የሰው ልጅ፣ የአሜሪካና የሌሎች አገሮች ታሪክ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሚያሳይ ሙዚየም ነው። ሁሉም ልዩ በሆነው የክርስትና፣ የእስልምና እና የቅድመ አይሁድ አምልኮዎቻችን እጃቸውን አፋቸው ላይ ይጭናሉ።

ስለሆነም ለአውሮፓዊው ወዳጄ፣ ለአሜሪካዊው ጓደኛዬ ባሪያዎች ከሰረቋት በኋላ”ከደመና ወርዳልን ነው” ያሏትን ታቦተ ፅዮንን አትስረቅ ብዬ እመክረዋለሁ። የወሰዷት ከደመና ወርዳላቸው አልነበረም። ሰርቀዋት ነው። በኋላም ሰሎሞን መልሷታል።

በስጦታነት ሰጥቶኝ ሳይሆን መልሷት ነው። ይህ ምንጭ ነው። የእርሱ ምንጭ ነው። ይህ ቅርስ ነው። የእርሱ ቅርስ ነው። የእኛም ቅርስ ነው። የሰው ልጆችን ዱካ ተከትሎ መምጣትና መመለስ አለበት። አሜሪካዊያኑ ወደ ጨረቃ ሲወጡ ያገኙት አቧራ ነው። አሜሪካውያን ሩቅ ተጉዘው ሌላ ፕላኔት እያፈላለጉ ነው። ይሄ በጣም ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ መጀመሪያ እራስህን ማወቅ ይኖርብሃል።

ለአሜሪካዊው ጓደኛዬ የምነገረው ይሄንን ነው።

ስለቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያውያን ታሪክስ ምን ትነግረኛለህ?
ኢትዮጵያ ዳግም ተመልሳ ትቆማለች። ዲሞክራሲ ይሰፍናል። ጎሰኝነት ሳይሆን ሕግ የበላይነት ይኖረዋል። ሕግና ዴሞክራሲ ሲኖር የሕዝብ የበላይነት ይረጋገጣል። ብዙ ስቃይ አይተናል። የተሰቃየነው በትንሽነታችንና በስግብግብነታችን ምክንያት ነው። ዘውዳዊ ስግብግብነት፣ የአፍሪካ ዳግም ቅርምት። ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚነግረን በእውር ስግብግብነት ሲያግበሰብሱ የኖሩ ግዛቶች ሁሉ በሕዝብ ኀይል ይበላሉ። ይሄንን ታሪክ ግሪካውያንና ሮማውያን አድርገውታል። ሌሎች አገራትም እንዲሁ አድርገዋል። ይሁን እንጂ በሕዝብ፣ ለሕዝብና ለሕዝብ የሆነ መንግሥት እንደገና ያቸንፋል!

ኢትዮጵያዊ መሆን ለአንተ ምን ማለት ነው?
ኢትዮጵያዊ ማለት ቀለል ያለ የሰው ዘር ነው። በአፍሪካዊ ታሪኩ፣ ሥልጣኔውና ባሕሉ ላይ የነቃ መረዳት ያለው ነው። በዓለም ሥልጣኔ፣ ባሕል፣ በእኩልነት እንዲሁም በዓለም ዐቀፋዊ ወንድማማችነት ላይ የነቃ መረዳት ያለው ነው። እንደሚገባኝ እኛ የአፍሪካ ጥንታዊ ታሪክን ነው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ የምንለው። ስለሆነም እኛ አሜሪካ አገር ለትምህርት እንደምንሔደው ሁሉ አሜሪካውያንም እዚህ መጥተው ሊማሩ ይገባል። በቅድመ አያቶቻቸው ፊት ትህትና ማሳየትንና እብረተኝነታቸውን ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ማለት ይሄ ነው።

አንድ ጓደኛህ “ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?” ስለሚለው የግጥም ሥራህ እንድጠይቅህ ጠቁሞኛል። እርሱ እንደነገረኝ ከሆነ ይህ ግጥም በሦስት ስርዓቶች ውስጥ ሳንሱር ተደርጓል።

በ1959 ልክ የከፍተኛ ኹለተኛ ትምህርቴን እንደጨረስኩ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ወደ አስመራ ተጉዤ ነበረ። የጉዞዬ ዓላማ አዲስ አበባ ውስጥ በነበረው ሳንሱር ምክንያት መጽሐፍ ማሳተም ስላልቻልኩ አስመራ ማሳተም እችል እንደሁ ለማየት ነበር። አንድ የክፍል ጓደኛዬ ነበር አስመራ ውስጥ በነጻነት ማሳተም እንደምችል የነገረኝ። (ጊዜው ኤርትራ ወደ እናት አገሯ ኢትዮጵያ የተዋሐደችበት ነበር)። የመጀመሪያ ጉዞዬ ወደ ወልዲያ ትግራይ ነበር።

በወቅቱ በእዚያ የነበረው ሁኔታ በዋናው ከተማ ያልተሰማ፣ ያልተጻፈና ያልተዘገበ ስለነበረ ከገሃነም ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምሁ። በዚያ ረሃብ ነበረ። ዕድሜዬ 29 ዓመት ነበር።

ደሴ ስንደርስ መሽቷል። አውቶቡሳችን በብዙ ሰዎች ተወረረ። ሰዎች ተሰልፈው ዕርዳታ ይጠይቁን ጀመር። ሁኔታው አዲስ አበባ ከማውቀው እጅግ ይለያል። ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ላይ አውቶቡሱን እንድንሳፈርና የትግራይ ዋና ከተማ ወደሆነችው መቐለ እንድንሔድ ከእንቅልፋችን ተቀሰቀስን። አላማጣ አካባቢ ያለ አንድ ዳገትማ ሥፍራ አቋርጠን ‘ቋሃይ’ ወደ ተሰኘች ትንሽ መንደር ስንደርስ ጊዜው መሽቷል። በእዛም ሰዎች ምግብና ዕርዳታ ለማግኘት ሲለምኑና ሲያለቅሱ ሰማሁ።
ከአውቶቡሱ እንዳልወርድ ተነገረኝ። ፖሊሶች አውቶብሳችንን ከሰዎቹ ለመጠበቅ ዙሪያውን ከበቡት። ሰዎቹ ወደ አውቶቡስ እየተተራመሱ ተንጋጉ። አጠገቤ የተቀመጡ አዛውንት እጃቸውን ወደ ወንበሩ ሥር ሰድደው ደሴ ላይ የገዙትን ዳቦ የያዘ ማዳበሪያ አወጡ። ሌላም ሴት እንዲሁ በሌላኛው መስኮት ጥግ በኩል እንዲሁ አደረጉ። እኔ ምንም አልተዘጋጀሁም። ይሄ ይገጥመኛል ብዬም አላሰብኩም። አብረውኝ የነበሩት ሰዎች ግን ችግር እንዳለ ስለጠረጠሩ ተዘጋጅተው ነበር።

ወዲያው ያንን የዳቦ ቁራሽ እጃቸውን በመስኮት አውጥተው እየወረወሩ ያድሉ ጀመር። የዳቦ ቁራሹን ለመቅለብ አቅም አግኝተው ከተዘረጉት እጆች ውስጥ ብዙዎቹ ቁርስራሹን አገኙ። ሌላ ለማግኘትም ተንጠራሩ። የተወሰኑ ቁራሾች ልፍስፍስ፣ ቀጭንና የተራበ ሕፃን ባዘለች አጭር ሴት ጭንቅላት ላይ በረሩ። ከዳቦ ቁራሾቹ መሐከል አንዷ ትከሻዋ ላይ ስላራፈች እጇን ብትሰድድ በጀርባዋ ያዘለችው ሕፃን በፍጥነት አንስቶ አፉ ውስጥ ከተተው። ወዲያው አንድ ረጅም ዱላ የያዘ ፖሊስ በያዘው ዱላ ረሃብ ያንገላታትን ሴት ዥልጦ መሬት ላይ ጣላት። በቁሟ ተዘረጋች። በጀርባው ያዘለችው ልጅ ከወገቧ ወደ መሬት ተሽቀነጠረ።

በደመነብስ አጠገቤ ወደ ተቀመጠው ሰው የካኪ ካፖርት እጄን ስሰድ የሆነ ነገር ጎትቼ አወጣሁ። ሽጉጥ ነበር። [ጓደኛዬ] በፍጥነት እጄን ይዞኝ ይሰድበኝና አብጄ እንደሆነ ይጠይቀኝ ጀመር።

በከተማዋ ወዳለች ትንሽ ካፊቴሪያ ለመግባት አልቻልንም። አብዛኞቻችን ከቋሃይ 30 ወይም 35 ኪሎ ሜትር ወደምትርቀው መቐለ እስክንደርስ ከአውቶቡሱ ላለመውረድ ወሰንን። ከተማው በሙሉ ያለቅስ ነበር። መቐለ ስንደርስ እየመሸ ነበር። ሌሊቱን በሙሉ እነርሱ ሆቴል የሚሏት ካፊቴሪያ ውስጥ ተቀምጬ አሳለፍሁ። ሁኔታው በጣም ጎድቶኝ ነበር። በጣም ያስፈራል። ሰምቼው የማላውቀው ነገር ነው። በእርግጥ ፖሊሶች ሆቴሉን ከብበው ከሕዝቡ ይጠብቁን ነበር። አመሻሽ ላይ ካፊቴሪያው ሻይና የዳቦ ቁራሽ አቀረበልን። መስኮቱን ከፍቼ ለቅሶ የሚመጣበትን አቅጣጫ አዳመጥሁ። የዳቦ ቁራሼን ይዤ ወደ ደቃቃ ትንሽ የሰው ፍጥረት ሮጥሁ። ፖሊስ ለሞት ትቶት ሌሎች ሰዎችን በሌላኛው በኩል ይጠብቃል። ይሄኛው እራሱን እንዲጠብቅ ትቶታል።

አጎንብሼ ላቀናው ሞከርሁ። የዳቦውን ቁራሽ በአፉ ላደርግለት ሞከርሁ። ከቁራሹ ጥቂት እንደገመጠ ዓይኖቹ ፈጥጠው እራሱን እኔ ላይ ጣለ። ይኼው ነበር። አለቀ። ሞተ።

ተመሳሳይ ነገሮች በመንገድ ላይ አየሁ። ወደ አስመራ ስንጓዝ ተመሳሳይ ነገሮች ገጠሙኝ። አስመራ ውስጥ ሳይቀር ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኛል። እንደ መቐለውና እንደ ቋሃይ ባይሆንም ረሃብ እዚያም ነበር።

ብስክሌት ተከራይቼ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ዞርሁ። ሳንሱሩ ቀድሞኝ መግባቱንና መጽሐፌን ማሳተም እንደማልችል ተረዳሁ። ስለሆነም ለብዙ ቀናት ከተማዋ ውስጥ እየተንሸራሸርሁ ልለምዳት ሞከርሁ። ዋና መሐል ከተማውን፣ መስጊዶቹንና ቤተክርስቲያኖቹን ጎበኘሁ። ከተማዋ በጣም ፅዱ ከተማ ናት። አስመራ የኢጣሊያውያን ንብረት ነበረች። አሁን እራሳቸውን ኤርትራውያን ብለው የሚጠሩት ኢትዮጵያውያን ከተማዋ ውስጥ በዋናው መንገድ ላይ መጓዝ አይፈቀድላቸውም ነበር።
(ፀግሽ ያኔ ነበር ስለ አስመራ
ያውራ ጎዳናሽ ጠለላ – ሁሉን በአክናፉ እየጠራ
ዐሥር ሰዓት ላይ ሲደራ
አደባባይ ሲያነጥፉ
አድባራትና መስጊዱን – ካቴድራሉን በየረድፉ
ገበያውን በየመልኩ – እንደ አውታር እያሰለፉ
በየክፍሉ፣ በየበሩ፣ በየመልኩ፣ በየተራ
ምነው ሁሉ እንዳንቺ አስመራ
እንደ ከተሞች መዲና – አቀያየሱ ቢጠራ…
በማለት ነበር የገጠመው።)

ስለሆነም ምን ዓይነት ከተማ ብትሆን፣ ምን ዓይነት መንገድ ቢሆን እንዳይሔዱበት እንደከለከሏቸው ይበልጥ ለማወቅ ብፈልግም የልጁ ትውስታ ከፊቴ እየመጣ መንፈሴን ስለረበሸኝ መጫር ጀመርሁ። ማስታወሻዬን አውጥቼ እንደ አዲስ ጻፍሁ። ከእዚያ ስመለስ ግጥሜን በወቅቱ የሬዲዮ ጣቢያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ለነበረ ጓደኛዬ ሰጠሁት። ግጥሙን አንብቦ ወደደው። ይህ ሰው በብዙ ተውኔቶቼ ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል። የዛኑ ዕለት ምሽት በእራሱ ጊዜ ግጥሙን በራዲዮ እንዲነበብ አደረገ። በእርግጥም ግጥሙ እንዲተላለፍ በማድረጉ ወዲያውኑ ከሥራ አባረሩት። መንግሥት ጉዳዩን በምሥጢር ይዞት ስለነበረ ትልቅ ብስጭት ተፈጠረ። ረሃቡ በምስጢር ተይዞ ነበር። ይሄ እንግዲህ የሆነው ከ32 ዓመት በፊት ነበር።
(የዐፄ ኃይለስላሤን መንግሥት ያስቆጣው ግጥም – ቅንጭብ
ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?
… በጣር አፋፍ ላይ ያለህ ሰው፣ ራብ እንዴት ነው የሚያዛልቅ
ለስንት ቀን ቀን ይሰጣል፣ አንደበትክን ሳይሸመቅቅ
ሸረሪት በልሣንህ ላይ፣ የድር ትብትቡን ሳይሠራ
ቁራና ቀበሮ በቀን፣ ከቀየህ ድባብ ሳይደራ
ጥንብ አንሳ ሊጭር ሳይመጣ፣ ቅምቡርስ ከጐጆህ ጣራ
እንደፍካሬ ኢየሱስ ቃል፣ በጣር ምፅአትን ሳትጠራ
አንደበት ሳለህ ተናገር
የምታውቅ የራብን ነገር
አስከሬንህ ከየጥሻው፣ ተርፎ እንደሁ ሳይቀረቀር
ስንት ደቂቃ ስንት ፋታ፣ ቀጠሮው ስንት ትንፋሽ ነበር
ቆሽት አርሮ ሳይፈረፈር
ትናጋህ በድርቀት ንዳድ፣ ጉሮሮህ ሳይሰነጠር? . . . .
የሆድ ነገር ስንት ያቆያል? ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓልት? ስንት ሌሊት?
ስንት ሰዓት ነው ሰቆቃው፣ ስንት ደቂቃ ነው ጭንቁ
እስቲ እናንተ ተናገሩ፣ ተርባችሁ የምታውቁ
ስንት ያቆያል? ስንት ያዘልቃል? . . . .
እውነት ራብ ስንት ቀን ይፈጃል?)

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here