‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው››

0
789

ፀሐዬ ተስፋዬ አዘውትሮ ከሚመላለስበት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በአግባቡ መስተናገድ ባለመቻሉ “ያተረፍኩት ድካም ብቻ ነው” ሲል ብሶቱን በማሰማት ይጀምራል። በቅርቡ ከውጪ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለሚጀምረው የማዕድን ማውጣት ንግድ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት በርካታ ጊዜያትን ቢመላለስም በመሥሪያ ቤቱ በኩል በሥራ ሰዓት ስብሰባ ስለሚደረግ በተፈለገበት የጊዜ ገደብ መጨረስ አልቻለም።

ላለፉት ስምንት ወራት በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲመላለስ ቢቆይም ጉዳዩን ከማስፈፀም ይልቅ ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራል። ከንግድ ሚኒስቴር ጀምሮ የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎችን ማንኳኳቱን የሚናገረው ፀሐዬ ደረጃቸው ይለያይ እንጂ በደረሰበት ሁሉ ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት ቢያንስ የአንድ ወር ጊዜ እንደወሰደበት ነው በምሬት የሚገልፀው። በሔደበት ሁሉ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ አንድ መሆኑ እና እሱም “ስብሰባ ላይ ናቸው” የሚል መሆኑ አስገራሚ ነው ይላል።

የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውና በአገር ውስጥ የሌሉት የንግድ ሸሪኮቹ ጋር በሥራው መጓተት ምክንያት ብዙ ውዝግብ ውስጥ እንደገባ የሚናገረው ፀሐዬ ሸሪኮቹ በተደጋጋሚ ሽርክናቸውን እንደሚያቋርጡ እና የንግድ ሐሳቡንም ወደ ሌላ የአፍሪካ አገራት ወስደው እንደሚተገብሩት እንዳስጠነቀቁት ተስፋ በቆረጠ ድምፀት ተናግሯል። በባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ዱባይ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ታስቦ በተካሔደ ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በማንሳት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እና በሽርክና እንዲሰሩ አግባብቶ ሸሪኮቹን ወደ ኢትዮጵያ እንዳመጣቸውና እየሆነ ያለው ነገር ግን ከነገራቸው እጅግ የራቀ በመሆኑ በእሱ ላይ ያላቸው እምነትም እየተሸረሸረ መሆኑን ይገልፃል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስብሰባ ማድረግ የሚችሉት ከሥራ ሰዓት ውጪ መሆኑን ተናግረው እንደነበር የሚያስታውሰው ፀሐዬ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በጣም የተለየ እንደሆነ እና እንዲያውም መደበኛ ሥራቸውን አቁመው ስብሰባን እንደመደበኛ ሥራቸው መያዛቸውን ነው የሚያምነው።
ለዚህ ደግሞ እንደምክኒያት የሚያቀርበው፤ ሥሙን መጥቀስ የማይፈልገው መንግሥት መሥሪያ ቤት ለአንድ ጉዳይ በሔደበት ወቅት የሚፈልጋቸው ኃላፊ ስብሰባ ውስጥ እንደሆኑ እና ትንሽ ጊዜ አርፍ ብሎ እንዲጠብቅ በፀሐፊያቸው በኩል ይነገረዋል።

“ስብሰባው አልቆ ከአሁን ካሁን እጠራለሁ ብዬ ስጠብቅ ሰዓታት ነጎዱ ሰውዬውም ሳይመጡ፥ እኔም በብሶት ጨርቄን ጥዬ ወጣሁ” በማለት በፈገግታ እያስታወሰ ይናገራል። ይህ የአንድ ቀን አጋጣሚው እንደሆነ የሚናገረው ፀሐዬ ፤ “በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙኝ ውጣ ውረዶች አዲስ ንግድ ለመጀመር የሚጋብዙ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ ተስፋ አስቆራጭ ናቸው” ሲል ያክላል፡፡

ከመቼውም ጊዜ በላይ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት ማግኘት ከባድ የሆነው አሁን ነው የሚለው ፀሐዬ ይህ ለዘመናት የቆየው ለጉዳይ ማስፈፀሚያ የሚጠየቁ ጉቦ ያበረታታል ሲልም ይገልፃል። በሌላኛው ትዝብቱ በሥራ ገበታቸው ላይ ተቀምጠው ኃላፊነትን ከመሸሽም ይሁን ከሌላ ጉዳይ ውሳኔ ላለመስጠት እንደ እንደ አማራጭ ማየታቸው ደግሞ የበለጠ እንዲማረር ምክንያት ሆነውታል። “የሌለብኝን ፀባይ ብስጩ አደረጉኝ” ሲል በብዙ መንገድ ምሬቱን ያስተጋባል።

ወደ ሥልጣን ከመጡ አንድ ዓመትን ያስቆጠሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አፅንዖት ሰጥተው ማሻሻያ ካደረጉበት ዘርፍ ውስጥ የንግድ ስርዓቱን ማሳለጥ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በቅርቡ “የንግዱን ስርዓት ቀላል ማድረግ” ወይም “Ease of doing business” የሚል መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ በተለይ ለአዳዲስ ንግድ ለሚጀምሩ በአንድ መስኮት የሚያልቅ የአሰራር መስመርን መዘርጋታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይሁን እንጂ በሚገባ እየተተገበረ ላለመሆኑ ደግሞ እንደ ፀሐዬ ዓይነት ንግድን ለመጀመር ረጅም ጊዜያት የወሰደባቸው ግለሰቦች ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው።

በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ረጅም ጊዜ የፈጀ ጉዳይ የያዘው ሚኪያስ ቦንገር በገባበት ቢሮ ሁሉ የሚመለከተውን ኃላፊ በቀጥታ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ያገኘበት ቀን እንደማስታውስ ይናገራል። ስብሰባ ላይ ናቸው የሚል ምክንያት በየጊዜው ከመስማቱ የተነሳ ትልቅ ምሬት ውስጥ የገባው ሚኪያስ፤ ኃላፊዎችን ቢያገኛቸው እንኳን ወይ ወደ ስብሰባ ሊገቡ ችኮላ ላይ ወይም ደግሞ በስብሰባ የዛለ አዕምሮ ይዘው በመሆኑ እንኳን ጉዳዩን ሊፈቱ ሊያናግሩትም እንደማይፈልጉ ይናገራል።

ላለፈው አንድ አመት ጉዳዩን ይዞ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ቢመላላስም ዛሬም እልባት ሊያገኝ ላለመቻሉ ከሌሎች ተደራቢ ምክንያቶች ባሻገር በሥራ ሰዓት የሚደረጉ ስብሰባዎች ቁጥር አንድ ራስ ምታት እንደሆኑበት ይናገራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የደንበኞች ማረፊያ ወንበሮች ላይ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎችን ለረጅም ሰዓታት ተቀምጠው መመልከት የተለመደ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። ሠራተኞች ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ሰበብ ሥራ ሰዓትን ጠብቀው ጉዳያቸውን ለመጨረስ የሚጣደፉትን ባለጉዳዮች ጊዜያቸውን በዋዛ እንዲያጠፉ ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ለተጨማሪ ገንዘብ ወጪ፣ የማኅበራዊ ሕይወት መዛባት እና ከፍ ሲልም ደግሞ በአገር ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ላይ ያለው ጫናም የሚናቅ አይደለም።

ሥሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የንግድ ሚኒስቴር ባልደረባ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራራ፤ በሚኒስቴሩ ውስጥ እሱን ጨምሮ በርካታ ሠራተኞች በየጊዜው በሚደረገው ስብሰባ ምክንያት መሰላቸታቸውን እና ስብሰባውን ተከትሎ በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰው መጉላላት እንደሚያሳዝናቸው ይናገራል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስብሰባ የሚደረግበትን የጊዜ ሰሌዳ በግልፅ ከተናገሩ በኋላ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን መደበኛ የሥራ ሰዓታትን ሳይነካ ይከወን እንደነበርና ተገልጋዮችንም በአግባቡ ማስተናገድ ይቻል እንደነበር አስታውሶ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ወደ ቀደመው አካሔድ እንደተመለሰ ያስረዳል። ይህ ነገር በተደጋገመ ቁጥር ሕዝብ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ያለው እምነት እየሳሳ እንደሚሔድና ወደ አልተፈለገ ተቃርኖ እንደሚያደርስ ያምናል።
“ስብሰባ መኖሩ ባልከፋ ነገር ግን የሥራ ሰዓታትን እስከመበደል ከደረሰ ግን ጉዳቱ አያሌ ነው” የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል አስተማሪው ቴዎድሮስ ውድነህ(ዶ/ር) በተለይ ደግሞ በሕግ ተቋማት ላይ ይህ ዓይነት ችግር የሚስተዋል ከሆነ ሕዝብ እምነቱን በተቋማቱ ላይ እያጣ ስለሚሔድ የትኛውንም ችግር በኀይል ከመፍታት እንደማይቆጠብ ያስረዳሉ። ለዚህ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የምናያቸውን ከልክ ያለፈ ስርዓት አልበኝነትን ያነሳሉ።

በእንጭጩ መገታት ያለበት ትክክል ያልሆነ የአሰራር ሥነ ስርዓት ነው የሚሉት ቴዎድሮስ አሁን ላይ ቀላል የሚመስለው ነገር እያደር ግን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍለን እንደማይጠራጠሩ በሐሳባቸው መቋጫ ላይ አክለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here