በ“ማንነት” ሥም

0
630

በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም ዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች የማንነት ጉዳይ አንገብጋቢ ሆኗል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለው የማንነት አረዳድ በአንድ ነገር ላይ ብቻ የተቸከለ ነው። ቤተልሔም ነጋሽ በሕይወት ገጠመኛቸው እና ንባባቸው የተረዱትን በማጣቀስ የማንነት ጉዳይ ውስብስብ እንደመሆኑ በቀላሉ ለመተርጎም መሞከር እንደማይገባም ያመላክታሉ።

 

ባለፈው ሳምንት ሰሞኑን ወዳለሁበትና ለሥራ ወደ መጣሁበት ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ስመጣ ከአዲስ አበባ የሚመጣው በረራ ከሚያቆምበት ጆሃንስበርግ አንስቶ 45 ደቂቃ የሚሆነውን የፍጥነት መንገድ ጉዞ የተጓዝኩት የማርፍበት ሆቴል በተጨማሪ ክፍያ ባዘጋጀልኝ መኪናና ሾፌር ነበር። በኢሜይል የበረራ ሰዓቴንና የምቆይበትን ቀን፣ የምፈልጋቸውን አገልግሎቶች፣ የሚጠበቁብኝን ክፍያዎች ከምነጋገራት የሽያጭ ሠራተኛ በቀር ኤርፖርት መጥቶ ስለሚቀበለኝ ሰው መረጃው አልነበረኝም።

ከአዲስ አበባ በጠዋት ተነስቼ ከአምስት ሰዓታት በረራ በኋላ ኦሊቨር ታምቦ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሼ፣ ብዙም ያላቆየኝን የኢሚግሬሽን ሰልፍና ጥያቄ ጨርሼ፣ አሰልቺውን ሻንጣ ጥበቃና የጉምሩክ “ምን ይዘሻል” አልፌ መውጫው’ጋ ስደርስ ሥሜን ከአያቴ ሥም ጋር በትልቁ አስጽፈው የቆሙ ሸምገል ያሉ ነጭ ጋር ተገጣጠምኩ። እኔ መሆኔን ገልጬ ቀረብ ስላቸው ቀልጠፍ ብለው ሻንጣዬን የያዘውን ጋሪ ተቀበሉኝ። ቁጥራቸው በርከት ያለ ነጭ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች እንዳሉ ስለማውቅ ነጭ ሾፌር ሊቀበለኝ መምጣቱ ብዙም አልደነቀኝ።

ባለብዙ ወለሉን የኤርፖርቱን ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሦስት ወለል በሊፍት ወርደን መኪናቸው ወደቆመበት ስንደርስ፣ በመደዳ የቆሙት እጅግ ዘመናዊ አዳዲስ መኪኖች እያየሁ ተደንቄ ሳላበቃ ሾፌሬ መኪና ጋር ደርሰን እንድገባ ሲከፍቱልኝ አላመንኩም። ፅድት ያለ አዲስ መርሴዲስ መኪና። ከዛ በቃ በአውሮፓ እንደተለመደው ጡረታ ወጥተው አነስተኛ የእንግዳ ማረፊያ ከፍተው የሚሠሩ፣ የሆቴሉ ባለቤት መሆን አለባቸው ብዬ አሰብኩ። በቀስታ አውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ግቢ ለቀን በተንጣለለ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ባለ አራት ሰፋፊ መንገድ የፍጥነት ጎዳና መንገዳችንን ስንይዝ ወሬ ተጀመረ። ሾፌሬ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁኝ ጡረታ የወጡ ሲቪል ኢንጅነር፣ ሆቴሉን ከወንድማቸው ጋር የከፈቱ፣ ወንድማቸው የአውሮፓውያን ፋሲካ በነበረበት እሁድ ለእረፍት ባለመኖሩ እኔን ለመቀበል መምጣታቸውን ነገሩኝ። የመጣንበትን ዘመናዊ ጎዳና ሳደንቅ በሥራው እንደተሳተፉ እየነገሩኝ፣ ከኢራን እስከ አውስትራሊያ ዛምቢያና ናሚቢያ በሥራ ምክንያት ስላሳለፉት እያጫወቱኝ ከአዲስ አበባ ደብረዘይት የሚሆነውን ከጆሃንስበርግ እስከ ፕሪቶሪያ ዘለቅን።

በመንገዳችን ያየሁት ትልቅ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚል ከታች ደግሞ አነስ በሚል ጽሑፍ “የክርስቲያኖችን ፓርቲ ምረጡ” የሚል ቢልቦርድ ያጫረብኝ ጥያቄ ውይይታችንን ከግል ልምዳቸው ወደ አገራቸው ደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ወሰደን። ጥያቄዬ የክርስቲያኖችን ፓርቲ ምረጡ ሲል በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ፓርቲ አለወይ የሚል ነበር። ወዲያውም የአገሬ ዘር ተኮር ፓርቲዎች በሐሳቤ እየመጡ። “አይ በሃይማኖት ተደራጅቶ ወይም በዚያ ተጠርቶ ሳይሆን ክርስቲያኖች ተሰባስበው የመሠረቱትን ፓርቲ ምረጡ ማለታቸው ነው” አሉኝ። አልሸሹም ዞር አሉ ነው አልኩ በሆዴ፥ ልክ የእኛ አገር አንዳንድ ፓርቲዎች ብሔር ተኮር አይደለንም ቢሉም በሥራቸውና በስብስባቸው እንዲሁም ትኩረት በሚሰጡባቸው ጉዳዮች ወደ የትኛው ያጋደሉ እንደሆኑ እንደምንረዳው መሆኑ ነው።

ሾፌሬ እንዳሉኝ በግንቦት ወር መጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ ምርጫ አለ። በዚያው ፖለቲካ ተነስቶ ነጩ ጡረተኛ “ነጻ ስንወጣ” እያሉ ሲያወሩ ትንሽ ግራ ሆነብኝ። ከላይ እንዳልኩት ደቡብ አፍሪካ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነጭ ዜጎች እንዳሏት ባውቅም፥ ነጮች ጥቁሮችን በቅኝ ገዙ ከሚለው ዘመኔን ሙሉ ከማውቀው ተረክ ባሻገር ነጭ ከሌላ ነጭ ነጻ መውጣቱን መስማት ትንሽ ለጆሮ ግራ ሆነብኝ። ከዚያ ማንነት ምንድነው የሚለውን ጥያቄ አጫረብኝ። ከአገራችን እውነታ አንፃር በተለይ ባደግኩበት ብዙ ብሔርና ብሔረሰቦች “መጤ” በሚባሉበት ከተማ ተወልዶ ማደግም፣ ቋንቋ መቻልም “የእኛ” የማያስብልበት ሁናቴ በአጠቃላይ እዚህ ነኝ ለማለት የመፈለግን ተፈጥሯዊ ፍላጎትና ነኝ የሚሉትን ማንነት የመከልከል አዝማሚያ አስታወሰኝ። በተለይ ከአንድ በላይ የሆኑ ብሔሮች ቅይጥ በሆነበት ማንነት ምርጫ ነው ወይስ የተጣለ ግዴታ (የእናት ማንነት ለፖለቲካ ወይም ለሌላ ምክያት ሲፈለግ በሚተውበት ሁኔታ) “ንፁኅ እንትን” መባልስ ለራስ ሽንገላ ወይስ በማንነት ቀውስ ውስጥ የመዳከር አባዜ የሚለው ትዝ አለኝ።

ከላይ ባስቀመጥኩት ገጠመኝ መነሻነት ግን ከዚህ በፊት በሌሎች አገራት ጉብኝቴ እና የሥራ ጉዞዬ በራሴም ድክመት ጭምር አጋጥሞኝ ከማያውቀው ከሥራ ውጪ ካሉ መደበኛ ከአገሬው ሰዎች ጋር የመወያየት አጋጣሚ ጋር አብሮ ያስታወስኩት ስለማንነት ሲነሳ ለአገራችን ሁኔታ በጣም የሚሥማማ የሚመስለኝ የአንድ ጸሐፊና አሰላሳይ ሥራን በተመለከተ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማካፈል በመፈለጌ ነው።

አሚን ማአሉፍ በትውልድ ሊባኖሳዊ በዜግነት ፈረንሳዊ የሆነ አረብኛ ተናጋሪ ሆኖ ያደገ ከዛ በፈረንሳይኛ መጻሕፍትን የጻፈና መጽሐፎቹ ከ40 በላይ በሆኑ የዓለማችን ቋንቋዎች የተተረጎሙለት ድንቅ ጸሐፊ ነው። አባቱ መልኪቲ እየተባለ ይጠራ የነበረው የኬልቲክ ማኅበረሰብ አባል የነበረ ሲሆን እናቱ የቱርክ ዝርያ ያላት ግብፃዊት ስትሆን ካቶሊክን የምትከተል ከመሆኗ የተነሳ በሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች እንዲማር ትወተውት ነበር። አሚን በርካታ መጽሐፎችን ያበረከተ ሲሆን ተጠቃሾቹ እ.አ.አ. በ1983 የታተመው “የመስቀል ጦርነቶች በአረቦች ዐይን”፣ “አፍሪካዊው ሊዮ” (1986)፣ “ሳማርካንድ” (1994)፣ “የብርሃን አፀዶች” (1996)፣ “የታንዮስ አለት” (1994) የተሰኙት ሲሆኑ ለዛሬ አንዳንድ ነጥቦች ለማለት ያሳሳኝና እ.አ.አ. በ1998 የታተመው ደግሞ “በማንነት ሥም፦ ጥቃት እና የሚጠጉበትን መፈለግ” (In the Name of Identity: Violence and the Need to Belong) የተሰኘው መጽሐፉ ነው። መጽሐፉ ማእሉፍ አረቦች በተለይ ለምዕራባዊያን ሥልጣኔና አኗኗር በመጋለጣቸውና ከምዕራቡ ዓለም ጋር በፈጠሩት የተለያየ ግንኙነት ምክንያት የገቡበትን የማንነት ቀውስ የራሱንም አረብ ክርስቲያን ማንነትና ያለፈበትን ልምድ ጨምሮ የተረከበት ነው።

በበኩሌ መጽሐፉንና በተለይም ምዕራፍ አንድን መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገ የምሥራቅ አፍሪካን ወጣቶች በአመራር ላይ ለማሠልጠን የቀረፀው ዝነኛ ፕሮግራም አካል በነበርኩበት ወቅት ለንባብና ለውይይት ከተመረጡ ምዕራፎች አንዱ በመሆኑ ነው ላገኘውና ላውቀው የቻልኩት። አሁን ላለንበት ደረጃ በተለይም ባለፉት ዓመታት ለነበርንበት ማንነትን (ብሔር፣ ዘር፣ ብሔራዊ ማንነት ወዘተ.) የመፈለግና በዚያም ምክንያት ነውጥና ሰላም እጦት ውስጥ መግባትን በሚመለከት የሚያቀርባቸውን ሐሳቦች ስለማደንቅ በአጋጣሚው ጥቂት ነጥቦችን ለማጋራት በመፈለግ ነው።

መጽሐፉ በአምስት ዋና ዋና ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን በግርድፍ ትርጉም “ማንነትና መጠጊያ”፣ “ዘመናዊነት ከሌሎች ሲመጣ”፣ “የአርቲፊሻል ዘረኞች ዘመን”፣ “ተንኮለኛውን ማላመድ” እና የቃላት መፍቻ ናቸው። ለዚህ ጽሑፌ ዓላማ የምጠቀመው ግን በመጀመሪያው ምዕራፍ የተጠቀሱ ሐሳቦችን ነው። የተጠቀምኩት መጽሐፍ በባርባራ ብሬይ አማካኝነት ከፈርንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የተመለሰውንና በፔንጊውን መጻሕፍት አማካኝነት እ.አ.አ. 2000 የታተመውን ኮፒ ነው።
“ማንነት” ምንድነው?

መጽሐፉን በመጀመሪያው ምዕራፍ ጸሐፊው ሐሳቡን የሚጀምረው የቃላትን ኀያልነት በማተት ነው “በጸሐፊነት ያሳለፍኩት ሕይወት ያስተማረኝ አንድ ነገር ቃላቶችን መፍራት እንዳለብኝ ነው። ግልጽ ያሉ ትርጉማቸው የማያሻማ የሚመስሉት በጣም ልንጠነቀቃቸው የሚገባ ሲሆን “ማንነት” የሚለው ቃል ከእነኝህ አንዱ ነው” ካለ በኋላ፥ ቃሉን በአንድ ትርጉም የማጠር ፍላጎትና ዕውቀትም እንደሌለው ጠቅሶ “ራስህን ዕወቅ” ከሚለው የሶቅራጥስ ጥቅስ ጀምሮ እስከ ሲግመንድ ፍሮይድ ቃሉ ወይም ማንነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ከፍልስፍና መሠረታዊ ጥያቄዎች አንዱ መሆኑን ያትታል። አዲስ አቀራረብና ትርጉም ለማምጣት ሐሳብ የለኝም ቢልም መመለስ የሚፈልገው መሠረታዊ ጥያቄ ወይም ማንሸራሸር የሚፈልገው ሐሳብ ግን “በዘመናችን በርካቶች በሃይማኖት፣ በዘር/ብሔር፣ በብሔራዊ ማንነት ወዘተ. ሥም ወንጀል የሚፈፅሙት ለምንድነው?” የሚለው ነው። ተያይዞ ሌሎች ጥያቄዎች ሲመጡ አንዱ “ይሄ ነገር ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው ወይስ አሁን የመጣ?” የሚለው ነው።

ማንነት ምንድን ነው የሚለውን ሊጠይቅ የሚሞክረው ከቀላሉ ምሳሌ ነው – ከመታወቂያ፣ የመታወቂያ ካርድ በተለይ በእንግሊዝኛው ማንነት የሚለውን ቃል ካመጣንበት ቃል አንፃር “የማንነት ካርድ” የሚል ቀጥታ ትርጉም ሲኖረው የሚይዘው በተለያዩ ሁኔታዎች የሚለያይ ሆኖ፥ ሥም ከነአያት፣ ፎቶ፣ ምናልባት አንዳንድ አካላዊ መግለጫዎች (ለምሳሌ የዓይንና የፀጉር ቀለም)፣ የባለመታወቂያው ፊርማና አንዳንዴም የጣት አሻራ የዶክመንቱ ባለቤት ሰውየው ለመሆኑ ያለጥርጥር ያስረዳሉ የተባሉትን ሁሉ ያካትታል። እነኝህ መረጃዎች መንትያ ወንድም ወይም እህት እንኳን ቢመጡ በስህተት እሱን እንዳይመስሉን ለማሳወቅ ይረዳሉ የሚባሉ ናቸው። ጸሐፊው እንደሚለው “የእኔ ማንነት ከሌላ ሰው ጋር አንድ ዓይነት ከመሆን የሚከለክለኝ ነገር ነው”። እንደሱ አባባል ይህን ዓይነቱ የማንነት ትርጉም በአንፃራዊ መልኩ የማያሻማ ትርጉም ይሰጣል። ሆኖም ግን የእያንዳንዱ ሰው ማንነት ከላይ በተዘረዘሩት ፓስፖርትም ይሁን መታወቂያ የሚይዛቸው መለያ ባሕርያት ባለፈ በርካታ ዝርዝሮች ያሉት ነው። ለበርካታ ሰዎች ደግሞ ይህ ማንነት የእኔ የሚሉት የሚታመኑት ከሆነ ቡድን የመገኘት ነገርን (allegiance) ያካትታል። ለአንዳንዶች ይህ የሚታመኑለት ቡድን ሃይማኖት ወይም የእምነት ቡድን ነው፤ ከአንድ በላይ ነው። ለሌሎች ተቋም (ፓርቲ)፣ ሙያ ወዘተ. ሊሆን ይችላል።

አለፍም ሲል ለሌሎች ጠንካራ ቁርኝት ያላቸው አካል የሚኖሩበት ሰፈር፣ አውራጃ፣ መንደር፣ ጎሳ፣ የእግር ኳስ ቡድን፣ የጓደኛማቾች ማኅበር ወዘተ. ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ቁርኝትና ታማኝነቱ ደረጃው ለእያንዳንዱ አካል መጠኑ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዱም የማይረባ ወይም በግለሰብ ሕይወት ላይ ተፅዕኖ የሌለው ሊሆን አይችልም፤ የማንነት አካል ነውና። እንደ ማዕሉፍ እምነት የእነኝህ ነገሮች ቅንብርና ጥንካሬ በየዕድሜያችን የሚለያይ ነው። የትኛውም የማንነታችን መሠረት የሆነ አካል ከሌላው ላይ ፍፁም የበላይነት የለውም። ይልቁንም እንደ ጊዜውና ያለንበት ወቅት በተለያየ መልክ ይገለጻል። ለምሳሌ እምነታችን የተነካ ወይም ጥያቄ ላይ የወደቀ ሲመስለን የእምነት አርበኞች ሆነን ብቅ እንልና ጎልቶ የሚወጣው ማንነታችን ያ ሆኖ ይሳላል። የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ወይም የመጣንበት የምንለው ብሔር አደጋ የተደቀነበት ሲመስለን እንዲሁ።

ከላይ የተቀመጡት የማንነትና እዚህ ነኝ የምንልባቸው የእምነት፣ የዘር፣ የፖለቲካ ታማኝነት፣ የሆነ ቡድን ደጋፊነት፣ የሆነ ቦታ መወለድ ወዘተ. ከሰው የሚለየን ቢመስልም በብዙ ሌሎች ሁኔታዎች ግን አንድ የሚያደርገንም ጭምር ነው። በየሁሉም ዓይነት ክፍል ከሌሎች በርካታ ሰዎች የምንጋራው ነገር አለንና። ዞሮ ዞሮ ነጥቡ አንዱን ማንነት ወስዶ (እንኳንስ የተቀየጠ ማንነት በበዛበት፣ ደራሲው እንዳለው በአያቶቻችን ጎጆ ማን እንዳለፈ በማናውቅበት) ሰው በዚያ ብቻ እንደሚተነተን ማሰብ ስህተት የሆነውን ያህል፥ ማንነቶቻችን ተጨፍልቀው ሁላችንም ሰው ነን የሚለው አስተሳሰብም ትክክል አለመሆኑን መረዳት። የማንነት ጉዳይ የተወሳሰበና የብዙ ነገሮች ጥርቅም እንዲሁም የሚለዋወጥ እንዲህ በቀላል የማይገለጽ መሆኑን አውቆ የኹለቱ አስታራቂ የሆነ ሰፋ ያለ ትንታኔ መፈለግ የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው።

በተረፈ ይህ ጽሑፍ ቁንፅል ቢሆን ጥያቄ ለማጫር ያህል እንደተጻፈ ታስቦ፥ ምናልባት በዝርዝር በሰፊው ሌላ ጊዜ ለመመለስ ቃል በመግባት ከማቆሜ በፊት አንድ ሌላ ሳነበው ትርጉም የሰጠኝ ለእኛ አገር ሁኔታ ተገቢ የመሰለኝን የማዕሉፍን ሐሳብ ላስቀምጥ።

“ብዙ የማንነት ክፍሎች ወይም በዘር በእምነት በተቋማት ወይም በመጡበት አካባቢ በርካታ ሚመደቡባቸው አካላት ያላቸው ሰዎች በማንነት ሥም ወንጀል በሚፈፀምባቸው ጊዜያት የሚጫወቱት ሚና አላቸው። እንደ እኔ አረብ፣ ክርስቲያን፣ ሊባኖስ፣ ፈርንሳዊ፣ ካቶሊክ የሆኑቱ እንደዚህ ያሉ ናቸው። ቢያንስ በአንዱ ጎኔ ከሌሎች በርካቶች ምድብ እጋራለሁ በእነሱና በሌሎች በሌላ ጎኔ ከምጋራቸው ጋር ድልድይ ሆኜ ማገልገል፣ የበለጡ ኹለቱ ምድቦች ወደ መረዳት፣ ወደ መተዋወቅ እንዲመጡ ምክንያት ልሆን እችላለሁ። ይህን ማድረግ የምችለው ግን አንደኛውን ማንነት እንድመርጥ የሚያስገድደኝ ወይም በብሔሬ ወይ በሃይማኖቴ አንፃር ብቻ እንድቆም ተፅዕኖ ከሌለ ብቻ ነው።”

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here