የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር 49 የፍቃድ ጥያቄዎችን ውድቅ አደረገ

0
866

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድናት ምርመራ ፈቃድ ከጠየቁ 56 የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ኩባንያዎች ውስጥ ለሰባቱ ብቻ ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የማዕድን ምርመራ ለማድረግ ፍቃድ እንዲሰጣቸው የጠየቁት 56 ኩባንያዎች አብዛኞቹ በሚኒስቴሩ የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላት እንዳልቻሉ ታውቋል። ሚኒስቴሩ ለሰባት ኩባንያዎች ስምንት ዓይነት ፍቃድ መስጠቱ የታወቀ ሲሆን፤ ኩባንያዎችም በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልል የማዕድናት ምርመራ ላይ እንደሚሠማሩ ለመረዳት ተችሏል።

በወርቅ፣ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት፣ በከሰል ድንጋይ፣ በላይም ስቶን እና ፖታሽ ማዕድናት ላይ ምርመራ ያካሒዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መስፈርቱን አሟልተው ከተመረጡት ኩባንያዎች ውስጥ ሰቆጣ ማይኒንግ ፒ ኤል ሲ፣ አይጋ ትሬዲንግ ኢንደስትሪስ፣ አጎዳዮ ሜታል ኤንድ አዘር ሚኒራልስ፣ አፍሪካ ማይኒንግ ኤንድ ኢነርጂ፣ አልታው ሪሶርስስ ሊሚትድ፣ ሰን ፒክ ኢትዮጵያ እና ሂምራ ማይኒንግ የተባሉ አገር በቀልና የውጭ አገራት ኩባንያዎች ይገኙበታል። ስለ ኩባንያዎች አመራረጥ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኪሮስ አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፤ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ያላቸው አቋም እና የኩባንያዎች ግለ ታሪክ በጥልቅ መዳሰሱን ተናግረዋል።

እንደ ኪሮስ ገለፃ ጥያቄ ባቀረቡ ኩባንያዎች ላይ ሚኒስቴሩ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ጥቂት ማሻሻያ ላደረጉ ኩባንያዎች ፍቃድ እንደሚሰጥ ጠቁመው በቅርቡ ለተጨማሪ አራት የማዕድን ምርመራ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ፍቃድ ይሰጣል ብለዋል። መንግሥት ከኩባኒያዎቹ ጋር ለሦስት ዓመት የሚቆይ ውል እንደገባና በቀጣይም አግባባነቱ እየታየ ይታደሳል ብለዋል፡፡

ፍቃድ የተሰጣቸው ሰባቱ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ለ1 መቶ ሰላሳ ሺሕ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን 88 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈሱ ታውቋል። በዚህም ረገድ መቀመጫውን በአውስትራሊያ ያደረገው አፍሪካ ማይኒንግ ኤንድ ኢነርጂ ከተጠቀሰው መዋዕለ ንዋይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ኩባንያዎች ግንባር ቀደም መሆኑን ኪሮስ አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ስለ ኩባንያው ግለ ታሪክ ለአንድ መቶ ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ በማዕድን ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ የነበረ ኩባንያ መሆኑንም ኪሮስ አክለዋል።

አፍሪካ ማይኒንግ ኤንድ ኢነርጂ ከዚህ ቀደም በ2010 መጋቢት ወር ላይ ቀንጢቻ ታንታለም ማዕድን ማውጫን ለመሸጥ ጨረታ በወጣ ጊዜ ለመግዛት በሕጋዊ መንገድ ተጫርቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ጨረታው ግልፅ ባለሆነ መንገድ በመንግሥት እንዲሰረዝ በመደረጉ ሳይሳካ ቀርቷል። በሌላ በኩል ደግሞ በ2010 ታኅሣሥ ወር ላይ ኩባንያው የወርቅ ማውጫ መሬት በአዶላ አካባቢ ተረክቦ የአመራረቱ ሒደት በምን መንገድ ይሁን በሚል ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here