በዓል አልወድም!

0
500

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“የምትይኝን በይኝ! ኃጢአት ከሆነም አላውቅም ይቅር ይበለኝ። ግን በዓል አልወድም!” አለች ጮክ ብላ። ታክሲ ውስጥ የተሳፈረው መድረሻውን የሚጠባበቅ ጥቂት ሰው ትኩረቱን ወደ እኛ አደረገ። ከፊት ወንበር የተቀመጡት ሳይቀሩ ከወገባቸው ዞር አሉ። “የማን ናት ደፋር! እስቲ እንያት!” ብለው መሰለኝ ያዩን ብቻ ግን ከአስተያየታቸው አንዳች ሒስ አለበት።

“ቀስ በያ! ለምንድን ነው ደግሞ በዓል የማትወጂው? መቼም ትንሣኤ እሁድ ስለሚውል እንጂ ሰኞና አርብ ቢሆን ሥራ የለም ብለሽ ትደሳሰቺ ነበር!” አልኳት፤ በእኔ ቤት ቀልድ ቢጤ ጥዬ ነገሩን ለፈገግታ ላደርገው ነበር። በተፈጥሮዋ ቀስ ብላ መናገር የማትችለው ጓዴ ግን ኮስተር ብላ፤ “ውይ! በ’ናትሽ ሥራውስ?! በዓል ሲባል ደስታ ሳይሆን ሥራ ነው የሚታየኝ” አለች።

“የዘንድሮ ሴቶች ሙያ የለማ! ስንፍና ብቻ! ገበያው እንደሆነ የተገነጠለውንም የተከተፈውንም… ያለቀለትን ያቀርብላችኋል። እርሱንም መሥራት ደክሟችሁ ነው?” አንዱ ጎልመስ ያለ ሰው በጨዋታችን ጣልቃ ገብቶ አስተያየት ሰጠ። ቃል በቃል “ምን አገባህ?” አላልነውም እንጂ የተናገረውን እንዳልሰማን ሆነን ነገራችንን ቀጠልን፤

“አስታውሳለሁ እናቴ የምታጣውን እንቅልፍና ድካሟን። በዓሉ ለእኛ ለልጆቿና ለባሏ ነበር እንጂ ለእርሷ የመጣ አይመስልም። ከሥራ ፈቃድ ማግኘት፣ ከዛ ሮጦ መጥቶ ቤት መንጎዳጎድ፣ ቤት ማጽዳት ማሰማመር፣ መጠራረግ… ከዛ ሃይማኖታዊ ስርዓት ላይ ለመካፈል ሩጫ፣ እንግዳ ማስተናገድና ማብላት ማጠጣቱ… ውይ! በዓል ለእናቴ እረፈት ሳይሆን ሥራ የሚያበዛባት ስለሆነ አልወድም።”

“እምጥ!” ከንፈር ሲመጠጥ ሰማሁ። እርሷም ቀጠለች፤ “እውነቴን ነውኮ! በዓል በአገራችን በተለይ ቤተሰብ ላላት ሴት ልጅ ከባድ ሥራ ነው። በግ ገዝቶ እንደመግባትና ዶሮ እንደማረድ፤ ወይም ʻአምጡት እንጂ!ʼ ብሎ ዳቦ እንደመቁረስ አይደለም” አለች።
ሰው እንደማጉረምረም ባለ ሁኔታ ሳቅ፤ መሰማቷ ይበልጥ ደስ ያላት ጓዴ ቀጠለች፤ “ተሳሳትኩ? እና እናቴን እያየሁ በዓልን እንዴት ልወድ እችላለሁ?”

“ለማንኛውም ትክክል ትሆኛለሽ ግን ደግሞ እናቶቻችን ያንንም የሚያደርጉት በደስታ ነው።” አልኩኝ፤ ከታክሲ ተራው ለመድረስ የቀረንን ርቀት ለመገመት አሻግሬ እያየሁ።

“አዎን! ያልሽው ቢገባኝም በዓል ደግሞ ያለ ሴት አያምርም…ነፍስ የምትዘሩበት እናንተ ናችሁ’ኮ” ቅድም ያላናገርነው ጎልማሳ ሰውም ተናገረ።

“ልክ ትሆናላችሁ፤ እኔም እናት ስሆን ለቤተሰቤ ደስታ የማልሆነው እንደማይኖር እገምታለሁ። ግን እኔን በተመለከተ ለእኔ ደስታ ስትል በበዓል ቀን እረፍት የሌላትን፤ እኔ ቁጭ ብዬ መዝናኛ ዝግጅቶች ሳይ ወዲያ ወዲህ የምትለውን እናቴን ስለማስታውስ፤ በቃ! በዓል አልወድም” ቀጥሎ አስተያየት የሰጣት የለም፤ ከታክሲው ወረድን።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here