ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ለመውሰድ የአሜሪካ መንግስት እየተጠበቀ ነው

0
499

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ዮሐንስ ነሲቡ የተባለውን ግለሰብ ለአሜሪካ መንግሥት አሳልፎው ለመስጠት ጽሕፈት ቤታቸው መስማማቱን እና የአሜሪካን መንግሥት በተስማማው ሰዓት ተጠርጣሪውን መውሰድ እንደሚችል አሳወቁ። ያሰለፍለው ሳምንት ሰኞ፣ ሚያዚያ 7 2011 ወደ አሜሪካ እንወሰድ ታስቦ የሚጓጓዝበት መንገድ እና ይዘውት የሚሄዱት አሜሪከዊያን መጥተው የነበረ ሲሆን ፍ/ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠቱ ሳይወሰድ ቀርቷል።

የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ማክሰኞ ሚያዚያ 15/2011 በሰጠው ውሳኔ ፖሊስ ለ2 ወራት ሲጠይቅ የቆየውን ጊዜ ቀጠሮ ባግባቡ ስላላተጠቀመ ክሱን ውድቅ እንዳደረገው እና የአካል ደኅንነት መብቱ እንዲጠበቅ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ግን ከእስር አለመፈታቱን እና የሚወስዱት አሜሪካዊያን እስኪመጡ እየተጠበቀ መሆኑም ታውቋል።

የተጠርጣሪው ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የተጠርጣሪውን ወላጅ አባት ሲሲዲ ተብሎ ከሚጠራው ሪል ስቴት ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ የካቲት 16/2011 እንዲታሰሩ እና ፍርድቤት ቀርቦ የ11 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ከተሰጠ በኋላ በስድስተኛው ቀን ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ እንደተለቀቁ ተናግራል። በሞያሌ በኩል ሕገወጥ ገንዘብን በማዘዋወር እና በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥረነዋል ቢሉም በስህተት የተያዘው ወላጅ አባት በተለቀቁበት ቀንም ዮሐንስን ካሳንቺስ አካባቢ ካለ የዘመድ ቤት ፖሊሶች ይዘውት እንደሔዱ ይናገራሉ።

“በኹለቱ አገራት መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍትሕ ዘርፉ እየተደረገ ያለው ትብብር እና ግንኙነት (ወደፊት ለአገራችን ሊያደርጉ የሚችለትን ትብብርም ጭምር) ግምት ውስጥ ገብቶ ግለሰቡ ተላላፎ እንዲሰጥ ቢደረግ ተገቢ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ 6(12) መሰረት ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጥ ተወስኗል” በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፊርማ እና ቲተር የተረጋገጠው ደብዳቤ እንደሚያሳየው።

ግለሰቡ በቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ ካውንቲ ፍርድቤት በቀረቡ አራት ክሶች እንደሚፈለግ አሜሪካው የፍትሕ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዲቪዥን እንዳስታወቀው የገለፀው ዐቃቤ ሕጉ እ.ኤ.አ. ማርች 23 ቀን 2017 የተሰጠ የእስር ትዛዝም እንደደረሰው ያትታል። ምንም እንኳን ኹለቱ አገራት ወንጀለኞችን የሚለዋወጡበት ስምምነት የሌለ ቢሆንም፣ በእንካ ለእንካ መርህ መሰረት ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ወንጀለኛ መኖሩን የአሜሪካ መንግሥት ማስተማመኛ ባይሰጥም የወደፊት ትብብሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰጠ ውሳኔ ነው በማለት ያስረዳሉ።

የተከሳሾቹ ጠበቆችም መንግሥት ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን እንደ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ መስኮች ሲያሳትፉ እና ጠቅላይ ሚኒሰቴሩም በራሳቸው አውሮፕላን የውጪ አገር ፓስፖርት የያዙ ግለሰቦችን ይዘው እየገቡ ዮሐንስን እንደ ሌላ ዜጋ ማየታቸው አግባብ እንዳልሆነ የሞግታሉ። ዮሐንስ ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰቦች ትውልደ ኢትዮጵዊያን እንደመሆናቸው መጠን የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን አላቸው ይላሉ።

ጠበቆቹም አክለው አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ ዐቃቤ ሕግ ሳይሆን የፍርድ ቤት ሥልጣን መሆኑን ገልፀው ጥያቄው የዳኝነት ሥልጣን እንጂ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሥልጣን ወሰኑን በማለፍ የሰጠው ውሳኔ ነው ብለው ይከራከራሉ።የዐቃቤ ሕጉን ውሳኔም የአገሪቱን ሉዓላዊነት ያስደፈረ ነውም ብለዋል።

የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 21 ማንኛውም ኢትዮጰያዊ ዜጋ ተላልፎ እንደማይሰጥ ይደነግጋል። ማንኛውም የውጪ አገር ዜጋም ተላላፎ የሚሰጠው ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ግንኙነት ከሌላት ነው ይላል።

ሔኖክ ዮሐንስ እና ቅድስት ስሜነህ የተባሉ ኹለት የፍቅር ጓደኛሞች ከአደንዛዥ እፅ ጋር የተያያዘ በተባለው ውዝግብ ተተኩሶባቸው ሞተው መገኘታቸውን በወቅቱ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቦ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here