የመርከብ ባለሞያዎችን የሚያሰለጥነው ድርጅት ሕጋዊነት ጥያቄ አስነሳ

0
553
  • ድርጅቱ የተመዘገበ ቢሆንም ከግብር እና ከሠራተኞች ሰብኣዊ መብቶች አያያዝ ጋር ጥያቄ ተነስቶበታል

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጨምሮ ለ6 ተቋማት በፃፈው ደብዳቤ የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬዲንግ ኢንስቲትዩት ፈቃድ ሳይኖረው ከ2002 ጀምሮ ተማሪዎችን በራሱ አሠልጥኖና አስመርቆ ሥራ ማስቀጠሩ እንዲሁም የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ማድረሱን እንዲያቆም እና ተገቢው እርምጃም እንዲወሰዱበት ጠየቀ።

በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ እና በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ሰልጣኞችን ለስድስት ወር 36 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ክፍያ በማስከፈል በማስማማት በባሕር ዳር እና በቢሾፍቱ ባቡጋያ ሃይቅ ላይ ሥልጠናዎችን የሚሰጠው ድርጅት 10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከሠልጣኞች ቢሰበሰብም ግብር እየከፈለ ስለመሆኑ እንደሚጠራጠር ኮንፌዴሬሽኑ ገልፃል።

ባለቤትነቱ የአሜሪካን ሆኖ በእስራኤላዊያን ቁጥጥር ሥር እንዳለ የሚነገረው ይህ ተቋም የመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎቹን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በተገኙበት ማስመረቁ ይታወሳል።

ሕጋዊነትን የሚገልፅ ማስረጃ ስለመኖሩ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ማስረጃውን ማቅረብ አለመቻሉ እንዲሁም የሰልጣኞችን የትምህርት ማስረጃ፣ ፓስፖርት፣ የባሕርተኝነት መታወቂያ፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫዎች እና የሥራ ልምድ በእጁ በመያዝ መሰረታዊ የሆኑ የሠራተኞች መብት ሲጥስ በይሁንታ መታለፉ እንዳሳሰበው ኮንፌዴሬሽኑ ይገልፃል።
ኮንፌዴሬሽኑ የሠራተኞቹን ዶክመንቶች ከመመለስ ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆርጥ የነበረውን ክፍያዎች ተመላሽ እንዲያደርግ ጠይቋል። የመርከብ ቴክኒሻኖቹ ለረጅም ጊዜ ጥያቄቸውን ሲያነሱ ቢቆዩም መንግሥት ሥልጣን የሰጣቸው፤ ነገር ግን አያገባኝም የሚሉ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በማስፈራራት፣ ደግሞ በቀጠሮ በማመላለስ ቅሬታ አቅራቢ ባሕረኞቹን እየተንገላቱ ነው ብለዋል። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ሰውን በባርነት፣ በግዴታ ወይም ለማንኛውም ዓላማ በሰው ልጅ መነገድን የሚከለክለውን ድንጋጌ የሚፃረር ድርጊት ነው በማለትም ይገልፃል።

ረዳት ቴክኒሻኖች የዋና ቴክኒሻን ሥራ እንዲሠሩ እንደሚደረግ እና ደሞዛቸውም አነስተኛ መሆኑ ተጠቅሷል። ኤጀንሲው ያለበትን ችግር መንግሥት እያየው አይደለም ያሉት ሠራተኞቹ፣ እነዚህን ችግሮች ለኤጀንሲው ብናቀርብም ምንም ምላሽ አልተሰጠንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም አገልግሎት ድርጅት በባሕር ዳርና ባቡጋያ የሚገኙ የመርከብ ኢንጂነሮችንና ቴክኒሻኖችን የሚያሠለጥኑትን ተቋማት የትምህርት ጥራት የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ሠራተኞች ያቀረቡትን በትምህርትና ሥራው አለመገናኘት ዙሪያ ምላሽ ሲሰጡ ሀገራችን ባሕር የሌላት በመሆኑ የሚሰጠው ሥልጠና ንድፈ ሐሳብ በመሆኑ፣ የሙከራ ትምህርት ወደ ሥራው ሲገቡ እዛው እንዲያውቁ ይደረጋል ሲሉ የማሪታይም ባለሥልጣን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሺ ፈቃደ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የተቋሙ ዓላማ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው የሚል ቢሆንም በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ እና በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን “አለም አቀፋዊ የሆነ የባሕርተኝነት ሙያ ባለቤትና ዓለማቀፋዊ ሥራ አገኝላችኋለው” በማለት ተማሪዎችን በየስድስት ወሩ እያስመረቀ ያለምንም የትምህርት ማስረጃ ሥራ እያፈላለኩ ነው በሚል ለከፍተኛ ችግር እንዳጋለጣቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ለኹለት ተከታታይ ሳምንታት ኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች በአካል በመሔድ በስልከ እና በኢሜል መልዕክት ብትልክም ለኅትመት እስከገባችበት ሰዓት ድረስ ምላሽ አላገኘችም።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here