የዐቃቤ ሕጎች መተዳዳሪ ደንብ መሰብሰብ ጀመረ

0
555

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት መከልከልን ጨምሮ ብዙ አዳዲስ ማሻሻያዎችን አድርጎበት የነበረውን የዐቃቤ ሕጎች መተዳደሪያ ደንብ ከዐቃቤ ሕጎች ላይ መሰብሰብ ጀመረ። ለመሰብሰብ ምክንያት የሆነው “የቃላት ግድፈትን ለማስተካከል ነው” የሚል ቢሆንም፣ አዲስ ማለዳ ከተቋሙ ባገኘችው መረጃ መሰረት ግልጽ ያሆነን አንቀጽ ለማብራራት እንደሆነ ታውቋል። ከዚህ በፊት በግልጽ ባይቀመጥም ዐቃቤያን ሕጎች የገዢው ፓርቲ አባል እንዲሆኑ እንደሚገደዱ ሲገልፁ ቆይተዋል።

የመስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ የሆኑት ዝናቡ ቱኑ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ዐቃቤያን ሕጎች ዘንድ ጥቅማ ጥቅምን የተመለከቱት አንቀፆች ይብራሩ የሚል ጥያቄ ስለመጣ እሱን ለማስተካከል መታሰቡንም ተናግረዋል።

ደንቡ ከአንድ ዓመት በፊት የተሸሻለና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ ያገኘ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፊርማ ጸድቆ ነበር። ከፀደቀ በኋላ ለረጅም ጊዜ በነጋሪት ጋዜጣ ሳይታተም በመቆየቱም የሶፍት ኮፒ ግልባጩ በዐቃቤ ሕጎች እጅ መሰንበቱ እንዳለ ሆኖ የተበተነው የወረቀት ቅጂም መሰብሰብ ተጀምሯል።

በረቂቅ ደንቡ ከተሻሻሉት መካከል ዐቃቤያን ሕጎች በሚቀጠሩበት ጊዜ በብሔር ኮታ ይሰጥ የነበረው አካሔድ ቀርቶ በምትኩ፣ በሲቪል ሰርቪስ አዋጁ መሰረት ለታዳጊ ክልሎች በሚሰጥ ማበረታቻ እንዲተካ በማድረግ የዐቃቤ ሕጎቹ ቅጥር በብቃት ላይ የተመሰረት ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ነበር።

ደንቡ ከመፅደቁ በፊት ዐቃቤ ሕጎች በእጅ ከፍንች ወንጀሎች ባሻገር ያለመከሰስ መብት እንዲኖራቸው አቅርቦ የነበረ ሲሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግን አልተቀበለውም። ከዚህ በተጨማሪ ለዳኞች የተቀመጠ የመኖሪያ ቤት ጥቅም ሲኖር ዐቃቤያን ሕጎች ግን ይህ ባለመኖሩ ጥያቄው ቢቀርብም ይሔም ተቀባይነት ካላገኙት መካከል ነው።

የዐቃቤ ሕጎችን የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት የሚከለክለው ይህ ደንብ በኀላፊነት ቦታ ያሉትን ግን አለመመልከቱም አነጋጋሪ ነበር። በተለያዩ የአገራት በሚገኙ የሕግ ወሰኖች ውስጥ ያሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጎች ወይም በኀላፊነት ቦታ ያሉ ዐቃቤያን ሕጎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ይከለከላል። ይህም ለሕዝብ እና ለአገር ጥቅም የመቆም ኀላፊነቱን ለማንኛውም ፓርቲ በመወገን አደጋ ውስጥ እንዳይገባ እንዲሁም ከፖለቲካ ነፃ ማድረጉን በሥልጣናቸው ጣልቃ እንዳይገቡም ለማደረግ እንደሆነ ይታወቃል።

በኢትዮጵያም የጠቅላይ ሚኒሰቴሩ የሕግ አማካሪ እንዲሁም ሚኒስቴሩ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሆኑ አሁንም መንግስት ከፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ እጁን ለመሰብሰብ ዝግጁ አይደለም ለሚሉት አስተያየቶችም በር ከፍቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here