ትንሳኤ የራቀው ፖለቲካ!

0
620

ይህ ሳምንት ለክርስትና እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ትንሣኤ የተከበረበት ነው። ይናገር ጌታቸው ይህንን ሃይማኖታዊ ትውፊት ተንተርሰው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከወደቀበት ትንሣኤ ማግኘት የተሳነው ለምንድ ነው በማለት ይጠይቃሉ። ክፍል አንድ ጽሑፍ እነኾ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንሣኤ ስንል
በኢትዮጵ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትንሳኤን የሚያስመኝ ወቅት ስለመኖሩ ያከራክራል። ፖለቲካችን የቁጭት ታሪክ አለው ወይ የሚለው ሐሳብም ያሟግታል። አገሪቱ ገናና የነበረችባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ቢኖሩም ለፖለቲካችን አርአያ መሆናቸው ግን አጠያያቂ ነው። እውነት ነው ሦስት ሺሕ ዓመታት ያሳለፈች አገር ግማሽ ዘመኗ የጦርነት ነው። ግን ደግሞ ሌላም መልክ አለን። ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ካሉ ሦስት ሥመ ገናና መንግሥታት ተርታ ተመድባ ታውቃለች። ዜጓቿን ፍትሐዊ በሆነ መንግድ ለመምራት የጣሩ ነገሥታት እንደነበሯትም ታሪክ ያወሳል።

በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያን ያስተዳደሯት ቀዳሚዊ ዮሐንስ ዜና መዕዋዕል ላይ አንድ አስገራሚ ታሪክ እናገኛለን። ዐፄ ዮሐንስ በእኔ ግዛት አንድም ሰው አዝኖ ከፈጣሪ ሊያጣላኝ አይገባም የሚል አቋም ነበራቸው። እናም ማንም ዜጋ እኔ ፊት እየመጣ ብሶቱን ቢነግረኝ ደስታውን አልችለውም ሲሉ አወጁ። በንጉሡ ዙሪያ ያሉት መኳንንት ግን ነዋሪው ንጉሡን ካገኘ ለእኛ ሥልጣን ጥሩ አይሆንም በማለት ቅሬታ የሚያቀርብ ሰው ከቀዳማዊ ዮሐንስ ፊት እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኑ። የጊዜው ባላባቶች ዜጋው ከመሪው እንዳይገናኝ አድርገው ጥቂት ጊዜያትን ቢያሳልፉም የሕዝብን ሮሮ ግን መግታት አልቻሉም። ይህ ቅሬታ ዐፄ ዮሐንስ ጋር ደርሶም ንጉሡ ሌላ መፍትሔን እንዲከተሉ አደረገ። በንግሥና ከተማቸው መሐል ላይ ትልቅ ደወል አሰቅለው ችግር የገጠመው ሁሉ ያን ደውል ደውሎ ያሳውቀኝ አሉ።

ብዙዎች በዚህ መንገድ ከንጉሡ ፊት እየቀረቡ በየአከባቢያቸው ያለውን ችግር ማስረዳት ቀጠሉ። ከዕለታት በአንዱ ቀን የሆነው ነገር ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ንጉሡ ደወል ሲሰሙ፥ ጠባቂዎቻቸውን ብሶት የሚያሰማ ስላለ ሒዱ አምጡልኝ አሉ። ሎሌዎቹ ደወሉ ያለበት ቦታ ሲደርሱ ሰው የሚባል ነገር የለም። ግራ ገብቷቸው ከተመለሱ በኋላ “ኧረ ጌታዬ ሰው አጣን” ሲሉ ለንጉሡ ተናገሩ። ቀዳማዊ ዮሐንስ “እናስ በቦታው ማንን አያችሁ ታዲያ?” ሲሉ ጠየቁ። ከወታደሮቹ አንዱ አንድ በእርጅና ከቤቱ የተባረረ አህያ ደወሉ ሥር ተኝቷል ሲል መለስ። ንጉሡ አላመነቱም በእኔ ግዛት ላለ የማንም ፍጡር በደል ተጠያቂ እኔው ስለሆንኩ አምጡት ብለው በቤተ መንግሥት እንዲቀለብ ማድረግ ጀመሩ።

በቀደመው ዘመን የነበረው በመንግሥትና በዜጎች መካካል ያለ ግንኙነት የበዝባዥና ተበዝባዥ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለ ተምኔታዊት ኢትዮጵያን የመፈጥር ሙከራንም ያነገበ ነበር። ይች አገር ሥልጣን ከአምላክ ይመነጫል ከሚል ትርክት ባለፈ ሥልጣን ከሕዝብ ይገኛል ብሎ የሚሰብክ የገዳ ስርዓት ስታራምድ የኖረች ናት። ሥልጣን ሙጥኝ ያላሉና ያያዙትን ንግሥና ይብቃኝ ብለው የሚመልሱ ንጉሥ ካሌብን የመሰሉ መሪዎች የነበሯት ናት። እንዲህ ያለው ታሪካችን ግን ከዘመናዊነት ደጃፍ አልደረሰም። የኛው አገር ክብረ ነገሥት እንደ እንግሊዞቹ “ማግና ካርታ” በጊዜ ሒደት እየተሻሻለ እንዲሔድ ዕድል አልተሰጠውም። ዴሞክራሲያችን እንደ እንግሊዛውያን ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን ከለመድነው በኋላ የመጣ አይደለም።

በዚህ የተነሳም የአገራችን ፖለቲካ ትንሳኤ የሚለው ጉዳይ መልኩ የተደበላለቀ ሆኗል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከትናንት ሽሽት የሚወድ በመሆኑ ያለፈው መልካም ነገር አይታየውም። ትውፊታዊውን ሕገ መንግሥት (ክብረ ነገሥት) እንደ ጅምር ወስዶ ከማሻሻል ይልቅ ቅርጫት ውስጥ ጠቅልሎ መጣል ያስወድሳል። በአክሱም ዘመን የነበረውን ገናና ሥልጣኔና ተውሶ በየዘመናቱ የመጣውን ስርዓት ፍታሐዊ የማድረግ እንቅስቃሴ ለማዘመን መጣር የድሮ ስርዓት ናፋቂ ያስብላል። እንዲህ ያለው የታሪክ አረዳዳችንም የፖለቲካ ትንሳኤ ሲባል ትናንት የተቀበረውን ስርዓት ለመመለስ ከመሞከር ጋር ይተሳሰራል፤ ግን አይደለም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንሳኤ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ሙግት በኀልዮትና በገቢር መሐል የሚዋልል ነው። በገቢር ስንል የውጪው ዓለም ተፅዕኖ ሳይጎላ ዜጎችን በፍትሐዊ መንገድ ለመምራት የተደረጉ ሙከራዎችን መናፈቅ ነው። ኀልዮታዊ ስንል ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሕልሞችን መዳሰስ ነው። በሁሉም በኩል ምልዑ የሆነች ተምኔታዊ ኢትዮጵያ የምትፈጠረው ከኹለቱ በሚቀዳ ሐሳብ ነው። በገቢር የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለማሠልጠን ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። አገር እንደ አገርም ምዕተ ዓመት ተሻግሯል። ኢትዮጵያ የሚል አገረ መንግሥትም ተመሥርቷል። ኀልዮታዊ የሆነው የአገራችን ሁኔታ ግን ሕልም እንጅ የተተገበረ አይደለም።

አገራዊ ሕልም
ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር) “What Did We Dream? What We Achtive? And Where Are We Heading?” በተሰኘ ጥናታቸው በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ዓላሚ መሪ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ናቸው ይላሉ። አንድ ጠንካራ መንግሥትን ለመመሥረት ከመታተር የሚቀዳው የንጉሡ ሕልም ፈርጀ ብዙ የሚሉት ዓይነት ነበር። አንድሪያስ እሸቴ (ፕ/ር)“The Uniqueness of Modernity” በተባለ ጽሑፋቸው የንገሡን ሕልም ምንጩ ኹለት ነገር ነው ይላሉ። የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ ከሆነ ስርዓተ ማኅበር ወደ ዓለማዊነት ለማሸጋገር መጣራቸው ሲሆን ኹለተኛው በኢትዮጵያ ያለውን ስርዓት ከውጪው ዓለም ጋር አነፃፅረው መመልከታቸው ነው።

ዐፄ ቴዎድሮስ በኹለቱ መንገድ አገራቸው ወደኋላ መቅረቷን ለመረዳት አፍታ አልወሰደባቸውም። በዚህ ምክንያትም አገራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል ያሉትን አማራጭ ሁሉ ለመጠቀም ጥረዋል። ጋፋት ላይ ቤተ መጽሐፍት እንዲከፈት አድርገዋል። በአውሮፓ አገራት የሥራ ማስታወቂያ እንዲወጣ በማድረግ የአገራቸውን ሰው ዓለማዊ ዕውቀት እንዲኖረው ለማድረግ ሞክረዋል። የጦር መሣሪያ ፋብሪካም ከፍተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም አንዲት አገር መመሥረት ለነገ የማይባል መሆኑን በመረዳት ለስኬቱ ሌት ተቀን ደፋ ቀና ብለዋል።

ይህ ልፋታቸው ግን ውጤታማ የመሆን ዕድሉ አናሳ ነበር። ብሩህ ዓለምነህ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” በሚለው መጽሐፋቸው የንጉሡን ፍላጎት ለመሸከም የሚረዳ አመክኖያዊ ማኅበረሰብ በሌለበት ሁኔታ ዐፄ ቴዎድሮስ ያን ያህል መልፋታቸው ውሃ ወቀጣ ዓይነት መሆኑን ያነሳሉ። ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር) በአንፃሩ የንጉሡ አንዲት ኢትዮጵያን የመመሥረት ፍላጎት ራሳቸው በመረጡት መንገድ የተነሳ የከሸፈ ነው ይላሉ። የዳግማዊ ቴዎድሮስ ሕልም ትክክል ቢሆንም የሔዱበት መንገድ ግን በዘመኑ ዐውድ ከታየ ቀይ ሽብርን እንደማወጅ ነበር ሲሉም ይሞግታሉ። ንጉሡ በእንግሊዝ ወታደሮች ተከበው የማይቀር ሞታቸውን ሲጎነጩ የተናገሩት ነገር ግን ከራስ ይልቅ ሕዝብን መውቀስ የሚታይበት ነበር።

ገብረሕይወት ባይከዳኝ “ዐጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተባለ መጽሐፋቸው ዳግማዊ ቴዎድሮስ በእንግሊዝ ወታደሮች በተከበቡ ወቅት ስርዓት የሌለውን ሕዝብ መምራቴ ለሽንፈት አበቃኝ ማለታቸውን ያነሳሉ። እዚህ ላይ ጥቂት ጥያቄዎችን ማንሳቱ ተገቢ ነው። ዐፄ ቴዎድሮስ ስርዓት የሚሉት ጉዳይ ምንድን ነው? የዐፄ ቴዎድሮስ ስርዓት ትርጉም ፈርጀ ብዙ ነው። ይሁን እንጅ እየተወያየንበት ካለው የፖለቲካ ታሪካችን አንፃር “ስርዓት” የሚለው ቃል በሕዝብና በመንግሥት መካካል ያለውን ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር ነው ።

እንዲህ ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄ በመንግስትና በህዝብ መካካል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሠረት የሚኖረው ምን ሲደረግ ነው? የሚል ይሆናል። የዚህ ሐሳብ ፖለቲካዊ ምላሹ ኹለት መልክ ያለው ነው። የመጀመሪያው ዳግማዊ ቴዎድሮስ የጀመሩትን አንዲት ኢትዮጵያ በኃይል አማራጭ የመመሥረት ጉዞ ከማስቀጠል ይመነጫል። ይህ አማራጭ ከንጉሡ ሕልፈት በኋላ የመጡ መሪዎች በየዘመኑ የሞከሩት ነው።

(ሳምንት ይቀጥላል)
ይነገር ጌታቸው ተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here