ከተጻፉበት ወረቀት በላይ ፋይዳ የሌላቸው የፖሊሲ ሰነዶች

0
684

ከዐሥራ አምስት ቀናት በፊት ናዝሬት/አዳማ የሚዲያና ተግባቦት ፖሊሲዎች የመጀመሪያው ረቂቅ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ለውይይት መቅረቡ ይታወሳል። ረቂቅ ሰነዱን ያነበቡት ጌታቸው መላኩ፥ ሰነዶቹ ስለዘርፉ መሰረታዊ መረጃ ካለመስጠታቸውም በተጨማሪ አንድ የፖሊሲ ሰነድ ሊያሟላ የሚገባቸውን አንኳር ጉዳዮች አላካተቱም በማለት ይተቻሉ።

የሶሻሊዝምና የኮሚኒዝም ዛር በሚያንዘፈዝፈን ዘመን ከተነገሩ ቀልዶች መካከል የሰሞኑ የሚዲያ ፖሊሲው ሰነድ አንዱን አስታወሰኝ። በጦፈ ʻየምሁራንʼ ስብሰባ ላይ አንድ ያለተጠበቀ ተሳታፊ በጉዳዮች ላይ ሐሳብ ሲሰጥ እንደተለመደው “ጓድ ሌኒን እንዳለው” እያለ ነበር። ሰውየው የሚያነሳቸው ሐሳቦች ውሃ ባይቋጥሩም ተሳታፊዎቹ ግን ማጣቀሻ ቃሏን እየሰሙ የሰውየውን በርካታ ሐሳቦች ሲያደንቁ ቆዩ። በመሀል ስብሰባው ለእረፍት ሲበተን ከግለሰቡ ጋር ሐሳብ ለመለዋወጥ የሚከበው ሰው ቁጥር ጨመረ። ከሁሉም ግን የሚሰነዘረው ተመሳሳይ ጥያቄ ነበር። “ለመሆኑ ይህንን ነገር ሌኒን የትኛው መጽሐፉ ላይ አስፍሮታል?” የሚል። የግለሰቡ መልስ ግን አጭርና አስደንጋጭ ነበር። “የትኛውንም መጽሐፍ አላየሁም፤ እሳቸው ያላሉት ነገር የለም ብዬ ነው” ብሎ እርፍ።

የምሁራዊ ተጠየቁ አጋጣሚ ጉዳዩን ግልፅ ቢደርገውም እንደዚህ ያሉ ʻደፋር ምሁራንንʼ ያፈራና ያለሥጋት እንዲናገሩ ያደረገ፣ ያለ ʻምሁራዊ ይሉኝታʼ እንዲዘላብዱ የሚያደፋፍረው ስርዓትና አሰራርን እስከመቼ እንደምንታገሰው ግን ያሳስበኛል። ምክንያቱም በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች የሚዘወር ስርዓትና አሰራር እውርን እውር ቢመራውን እንዳያስከትልብን።
ከኹለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ሚዲያን ለመጪው ዓመታት ይመራል ተብሎ የታሰበ የሚዲያ ፖሊሲና ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው የተግባቦት ፖሊሲዎች ተቀርፀው የመጀመሪያ ረቂቅ ለውይይት ቀርበው ነበር። በመጀመሪያ በዝግጅቱ ላይ ለመገኘት ካለኝ ፍላጎት የተነሳ ይፋዊ ጥሪ ባይቀርብልኝም ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል አነጋገሬ መታደም እንድችል ስለፈቀዱልኝ ምስጋናዬ ትልቅ ነበር።

ነገር ግን ምስጋናዬን ውሃ የበላው መጀመሪያ የፖሊሲ ሰነዱን አንብቤ ስጨርስ ነበር። ለወትሮው እንደዚህ ዓይነት ከሐሳብ የወጣ፣ መስመሩን ያልለየ ሰነድ የማንበብ ፍለጎት አልነበረብኝም። ነገር ግን የእንጀራ ጉዳይ ሆነና ሰነዱን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሳላነብ ትችትም ይሁን አስተያየት መስጠት አያምርብኝም በማለት ግዴታዬን ተወጣው። ኹለት ጊዜ አንብቤ ጨረስኩ ማለቴ ነው፤ ኹለቱንም ሰነዶች።

በመጀመሪያ የጠየኩት የራሴን ልምድና ትምህርት ነበር። በእውነት እንደዚህ ዓይነት ሰነድ የፖሊሲ ሰነድ ተብሎ ይቀርብ ይሆን? ያልተገነዘብኩት የረሳሁት ወይም ያለፈኝ ነገር ኖሮ ይሆን ብዬ ወዳጆቼን አማከርኩ፤ ቢያንስ በቅርቤ ያሉትን ዋቢ መጻሕፍት አገለበጥኩ። የተሰጡኝ ሰነዶች በእውነት መነሻና መድረሻቸው ግልፅ ያልሆኑ ሆነው አገኘኋቸው።

የፖሊሲ ሰነዶች ድክመት ከአጻጻፋቸው ይጀምራል። አንድ የፖሊሲ ሰነድ 40 ገጽ ያህል ሲሆን “ምን ዓይነት ትንታኔ ቢይዝ ነው” የሚያሰኝ ነበር። ነገር ግን ዶክመንቱ እንኳን ፖሊሲ ሰነድ ሊሆን በእኔ ግምት መሰረታዊ መረጃ ስለሴክተሩ ለመስጠት የሚችል አቅም ያለው ጽሁፍ እንኳ ሊሆን አልቻለም። በመሆኑም ይህንን ሥራ ለመተቸትና ለማዳበር በቦታው ጊዜና ጉልበታቸውን ሰውተው አበርክቶአቸውን በለጋስነት ለመስጠት የተሰበሰቡት ግለሰቦች “ምን ይሰማቸው ይሆን?” የሚል የሐዘኔታ ትዝብትም አድሮብኝ ነበር።

አንድ የፖሊሲ ሰነድ ውስጥ ሊቀመጡ የሚገባቸውን ጉዳዮች ʻሀ ሁʼን እንኳ ያልያዙት እነዚህ ሰነዶች በመሆናቸው ድክመታቸውን ከመነሻው ለማሳየት ልሞክር። አንድ የፖሊሲ ሰነድ በመጀመሪያ በዚያ ፖሊሲ ትግበራ የሚሳካውን ራዕይና ሊገኝ የሚችለውን ውጤት ማስቀመጥ ቢጀምርም መነሻው ግን በዘርፉ የተደረጉት ትንታኔዎች የሚያሳዩት ነባራዊ ሁኔታዎችን በመግለጫ በማብራራት መሆን አለበት። በመሆኑም ከፖሊሲ ሰነዱ የምጠብቀው መግቢያ መሆን የነበረበት በዘርፉ የተደረጉ የጥንካሬና ድክመት፣ መልካም አጋጣሚና ሥጋት ትንታኔ ነበር። ይህም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተጨባጭ ለማስረዳት ከመቻሉም ባሻገር፣ የሚያስፈልገው ዓይነትና መጠነ ጥረት የሚያመላክት ገላጭ ጉዳይ ይሆናል።

በዚህም ለባለድርሻ አካላት ሰፊ የሐሳብ ማንሸራሸሪያ ምኅዳር ሊከፍት ይችላል። በዚያም የሐሳብ ልውውጥ ጉዳዮች ይነሳሉ፣ ይተነተናሉ አንድምታቸውና ዘላቂ ትርጉማቸው በግልጽና በማያሻማ መልኩ ይቀርባል። የቀረቡት የሚዲያ ፖሊሲና የተግባቦት ፖሊሲ ሰነዶች በዚህ ላይ ምንም ነገር በግልፅ ያስቀመጡት ነገር የለም። በእኔ ትምህርትና ልምድ ይህ ሕዝብ ፖሊሲ ቀረጻ ሒደት መሰረታዊ መነሻ ተግባር ነው።

በመቀጠል ሰነዶቹ በዘርፉ በተደረገው ትንታኔ ላይ በመመርኮዝ ቁልፍ አስቻይና ፈታኝ ጉዳዮችን በመለየት ማስቀመጥ የተገባቸው ቢሆንም፤ እነዚህም ጉዳዮች በሰነዶቹ ውስጥ እዚህም እዚያም በተለያዩ ርዕሶች ውስጥ ከመጠቀሳቸው በተለየ ስትራቴጂያዊ የተፅዕኖ ደረጃቸው ግልፅ አልነበረም። በመሆኑም የሰነዶቹን ዋና የትኩረት ጉዳይ በመለየት አንባቢም ይሁን የውይይቱ ተሳታፊ ትኩረታቸው በግልፅ ጉዳይ ላይ የሆኑ ሐሳብና አስተያየት ለመስጠት እንዳይችል እንደሚገድቡት እሙን ነው። ነገር ግን የፖሊሲ ሰነዶቹ ከዚህ ውጪ ምን ማካተት እንደፈለጉ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ምንም ገላጭ ሐሳቦች አልተካተቱበትም። ይህም የሰነዶቹ መሰረታዊ ድክመቶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።

በመቀጠል የሚጠበቀው በትንታኔው ላይ ተመስርቶ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችን ማሳየት የሚቻልበትን ጉዳይ ማስቀመጥ ነበር። በዚህም ላይ ሰነዶቹ ምንም ካለማስቀመጣቸው ባሻገር ግልጽነት የጎደለው ተደጋጋሚ ሐሳቦችን በማስገባታቸው የሰነዶቹን ገፆች ያለወትሮው ከማብዛት ባሻገር የፈየዱት ነገር አልነበረም። በመሆኑም የሚዲያ ፖሊሲውም ይሁን የተግባቦት ፖሊሲው “ከተጻፉበት ወረቀት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም” የሚል ጠንካራ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል።

ወደ ሚቀጥለው ጉዳይ ልሻገርና በቀጣይ ከፖሊሲ ሰነዶቹ በሚቀጥለው ደረጃ የሚጠበቀው ቢያንስ በዐሥር ዓመታት ከተቻለም ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ ውስጥ እነዚህ የፖሊሲ ሰነዶች ተተግብረው የሚያመጡትንና ሊፈጥሩ የሚችሉትን የሚዲያና የተግባቦት ምኅዳር በመቃኘትና አሻግሮ በማየት ወደዚያው የሚወስደንን አቅጣጫ ማስቀመጥ ከሰነዶቹ ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ሰነዶቹ ገላጭ የሚመስሉ ጽሑፎችን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ከማስነበባቸው ሌላ የተለየ አቅጣጫና ውጤት የሚያመላክቱ ጽሑፎች አላገኘሁባቸውም። ይህም አዘጋጆቹ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ ክፍተት የሚያሳይ ሲሆን ለዝግጅቱም የተሰጠውን ዝቅተኛ ትኩረት ያመላክታል።

በዚህ ሚዲያ የአገራችንን ሁኔታ በሚወስንበት ዘመን፣ ፈር የለቀቁና ሙያዊ ሥነ ምግባርን ቸል ያሉ የሚዲና የተግባቦት ሥነ ምግባርን የጣሱ ተግባራት በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመሩ በመጡበት ዘመን፣ ወሳኝ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውን መድኀኒት በእንደዚህ ሁኔታ አኮስሶ አዘጋጀሁ ማለት አንድም ጉዳዩን አለማቅ፣ አሊያም አጉል ድፍረት ነው። ያም ይሁን ይህ ኀላፊነት ያለባቸው ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ጉዳዩን ቸል ማለታቸው አስተዛዛቢ ነው።

በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገውና በጣም የሚያሳስበኝ ጉዳይ በዚህ መልኩ ከተቀረጹ ግልፅነትና አቅም ከጎደላቸው ሰነዶች በቀጣይ ምን ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ፣ መመሪያዎችና ደንቦች ይዘጋጃሉ የሚለው ጉዳይ ነው። ፖሊሲ አንድ አገር/ድርጅት በአንድ መስክ የተሻለና ዘመኑን የዋጀ ለውጥ ለማምጣት አርቆ የሚያስበው ትልም ነው። ይህንን ከዐሥር ዓመት በላይ (በአብዛኛው ማለቴ ነው) የሚዘልቅ ትልም በግልፅ ማስቀመጥ የመጀመሪያው ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ፣ በመቀጠል በተግባር ሲፈፀም የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ከግምት ያስገባ ነው። በመሆኑም የፖሊሲ ሰነዶች ወደ ተግባር ሲገቡ በሒደት የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች በሕግ ማዕቀፍ አየፈቱ፣ የሕግ ማዕቀፎቹን ደግሞ በደንቦችና መመሪዎች የበለጠ እያበራዩ ፖሊሲ ትግበራው ቀና መንገድ መፍጠር ዋናው የፖሊሲ ትግበራ ሥራ ነው።

ነገር ግን የፖሊሲ ሰነዶቹ ለሕግ ማዕቀፍ፣ ለደንቦችና መመሪዎች መነሻ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል በአንክሮ ለመረዳት ያልጣሩ የሚመስሉት የሚዲያ ፖሊሲውና የተግባቦት ፖሊሲው ʻአዘጋጆችʼ ሙያዊ ቅኝትና ትጋት የታየባቸው በፍፁም አይመስሉም። የፖሊሲ ሰነዶቹ ግን የሕግ ማዕቀፍ ባሕርያትም፣ የደንብም፣ የመመሪያም ጉዳዮችን አጭቀው በአንዳንድ ርዕሶች ውስጥ የያዙ ከባድ የግልጽነትና የዓላማ መሳት ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ለመገንዘብ የዘርፉ ሊቅ መሆን አይጠይቅም። በመሆኑም የፖሊሲ ሰነዶቹ አንድን ትልቅ ዘርፍ ከመምራት ይልቅ አሳሳችነታቸው ግልጽነት ለጎደለው አተረጓጎምና ትግበራ ሊዳርግ ከመቻሉም ባሻገር ላላስፈላጊ ክርክርና ጭቅጭቅ በር እንዳይከፍቱ ሥጋት አለኝ።

የአስተባባሪዎች አመድ አፋሽነት
እነዚህ የሚዲያ ፖሊሲና የተግባቦት ፖሊሲ ቀረጻ ተግባራዊ እንዲሆኑ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም እንደሆነ ሰነዶቹ ያመላክታሉ። ለእኔም እንቆቅልሽ የሆነብኝ ጉዳይ ይህ ነው። ይህ አንጋፋ የተባበሩት መንግሥስታት ድርጅት አካል በሥሙ እንደዚህ ዓይነት ሰነድ፣ ሊያውም በሚጠቀምበት ኦፊሴላዊ ቋንቋ በእንግሊዝኛ መዘጋጀቱን አላወቀው ይሆን? የሚመለከታቸው ኀላፊዎችስ አላዩት ይሆን? ወይስ ባለቤት ያጣ አጉል ጉዳይ ሆነባቸው? ይህ በእውነት የድርጅቱን ሥም ከማኮሰሱም ባሻገር፣ ድርጅቱን አመድ አፋሽ ሊያደርገው ችላል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በምክር አገልግሎት ግዢ ላይ ከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠው መስፈርት እንደሚስቀምጥ አውቃለሁ። በድርጅቱ ድጋፍ የሚዘጋጁ ሰነዶች ላይ የድርጅቱ ማኅትም ወይም መለያ አርማ እንዲያርፍበት የሚያስገድድበትም አሰራር እንዳለም እገምታለሁ። ነገር ግን እንደዚህ ያለ ሊያውም የሚዲያና የተግባቦት ፖሊሲ ሰነዶች ዝግጅትን ድርጅቱ በቸልተኝነት አሳየ።

ለማንኛውም ሰነዱ የሚጠቅመውም የሚጎዳውም በዋናነት ኢትዮጵያን በተለይ ደግሞ የመገናኛ ብዙኀን ዘርፉን ስለሆነ በዘርፉ የተሰማራን ግለሰብ ባለሙያዎችም ሆንን ተቋማት እንደዚህ ዓይነት ፈረንጆቹ (grave mistake) የሚሉት ስህተት እስኪሰራ ባንጠብቅና በባለቤትነት መክፈል ያለብንን መስዋዕትነት ከፍለን ብናዘጋጅ፤ ያ ባይሆን እንኳን ጉዳዩ የሚሔድበትን መንገድ በመከተል ችግር ከመድረሱ በፊት የየራሳችንን ኀላፊነት ብንወጣ መልካም ነው። የኋላ ኋላ ዕዳው ገብስ የሚሆነው ለእኛው ነውና።

ጌታቸው መላኩ የሚዲያና ተግባቦት አማካሪ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው
getachewmelaku@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here