አዶኒክ ወርቁ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ

0
679

አዶኒክ ወርቁ በተለይ በመዝናኛ የቴሌቪዥን ዝግጅትና ትልቅ የንግድ ትርዒቶችን በማሰናዳት የሚታወቀው የሀበሻ ዊክሊ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነው። ውልደትና እድገቱ አዲስ አበባ የሆነው አዱኒክ፥ ከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ዘርፍ ተከታትሎ የመጀመሪያ ዲግሪውን ሰርቷል።

በ2001 በሶፍተዌርና ኔትወርክ ልማት ላይ የሚሠራ ‘አዶኒክ ኮምፒውተር ሶሊሽን’ በሚል ስያሜ የሚጠራ ኩባንያ አቋቁሞ ከኹለት ዓመታት ቆይታ በኋላ በመዝናኛውና በኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ላይ በግል በነበረው ከፍተኛ ፍቅር ምክንያት ‘ሀበሻ ዊክሊ’ የሚል ድርጅት አቋቋመ።

ሀበሻ ዊክሊ በኢትዮጵያ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን በውጪ አዘጋጆች የሚቀርብ በኩባንያው ሥም የሚጠራ የቴሌቪዥን መርሃ ግብር በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ማዘጋጀት ጀመረ። ይሄ ሀበሻ ዊክሊ የተባለው ሳምንታዊው መርሃ ግብር ትኩረቱን በማኅበራዊና በመዝናኛ ዓለም በሳምንቱ ምን እንደተከናወነ የሚዳስስ አዝናኝ ዝግጅት እንደሆነ አዱኒክ ያምናል።

ከሕዝብ ጋር በሰፊው ያስተዋወቀውም ይሄው የቴሌቪዥን ዝግጅት እንደሆነ የሚናገረው አዱኒክ፥ ኩባንያው ግን በተለያዩ የንግድ ዘርፎች መሰማራቱን ይናገራሉ።

ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት የሆነው አዱኒክ፥ ሀበሻ ዊክሊ ባዘጋጀውና ዛሬ ምሽት በጊዮን ሆቴል ስለሚካሔደው የታዋቂው ድምፃዊ ጎሣዬ ተስፋዬ የሙዚቃ ድግስ በተመለከተና በተሠማራባቸው ሌሎች የንግድ ዘርፎች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ ሀበሻ ዊክሊ በዋናነት የሚያከናውናቸው ተግባራት ምን ምን ናቸው?
አዶኒክ ወርቁ፡ ሀበሻ ዊክሊ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ኪነ ጥበብ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ በትጋት እየሠራ ይገኛል። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ከመሆኗ አንጻር ብዙ ሊታዩ፣ ሊነገርላቸውና ሊጎበኙ የሚችሉ ቦታዎች አሏት። ከዚህ አንጻር አስተዋጽዖ ለማድረግ የተቋቋመ ኩባንያ ነው።

ኩባንያችን በዋናነት የሚሠራቸው ኩነትን ማዘጋጀት (event management)፣ የሚዲያ ሥራዎች፣ ማንኛውንም የማስታወቂያ ሥራዎች እና የኩባንያ ብራንዲንግ ናቸው። በተጨማሪም ከኢንፎርሜሽነን ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘም ሶፍትዌር ልማት እና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ማስተዋወቅ (promotion) እንዲሁም በንግድ (trading) ላይ እንሳተፋለን።

ዛሬ በጊዮን ሆቴል የሚካሔደው የጎሣዬ ተስፋዬ የሙዚቃ ድግሥ አጠቃላይ ዝግጅት ምን ይመስላል?
የጎሣዬ ተስፋዬን የሙዚቃ ዝግጅትን በተመለከተ ከሀበሻ ዊክሊ ጋር ውል ተዋውሏል። ጎሣዬ አልበም ከለቀቀና ኮንሰርት ካዘጋጀ 10 ዓመት ሆኖታል፤ አዲሱን አልበሙን ከለቀቀ በኋላ ይሄኛው የመጀመሪያው ኮንሰርት ነው። ከአዲስ አበባው በተጨማሪ አገር ዐቀፍ ኮንሰርት የማድረግ ውልም ተዋውለናል።

ዝግጅቱን በተመለከተ ጎሣዬ መሆኑ በራሱ አንዱ ልዩ ነገር ነው፤ በጣም በጉጉት ይጠበቅ የነበረ ድምፃዊ ነው። ከዚህ ቀደም ጥሩ ሥራዎችን ሠርቷል። በአዲሱም አልበም እንደዚሁ ሰኬታማ ነው። ከረጅም ጊዜ በኋላ ከሕዝብ ጋር የሚገናኝበት መድረክ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

ሌላው የክፍያ ሥርዓቱን በተመለከተ መግቢያው ላይ ዲጅታል ስርዓት ለመጠቀም ከባንኮች ጋር ድርድር እያደረግን ነው። የትኬት መጭበርበር እንዳይኖር ቲኬቱ ውጪ አገር ታትሞ ነው የመጣው።

ከመድረክ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው አራት ማዕዘን መድረክ ነው። ይህንን የተለመደ መድረክ በመለወጥ ከፍተኛ ሥራ ሠርተናል። የመድረክ ገጽታ ግንባታ እስከዛሬ ከተሠሩት የተለየ ነው። ሌላው ድምፃዊው ወደ መድረክ ሲወጣ በተለመደው መልኩ ሳይሆን በልዩ ሁኔታ ይሆናል።

ሌሎች ድንገቴ ተጋባዥ ድምፃውያንም ይኖራሉ። አንጋፋና ወጣት ድምፃውያንም እንዲሁ በሙዚቃ ድግሱ ላይ ይሳተፋሉ። በተረፈ በዝግጅቱ እድምተኞች ላይ ድንገቴ የሆነ አስደሳች ነገር ለመፍጠር ስለምንሠራ ከዚህ በላይ ባልነግርህ ይሻላል።

ድርጅቶች ስፖንሰር እንዲያደርጉ ማስታወቂያ በሠፊው ሠርታችኋል። ስፖንሰር ጠፋ እንዴ?
ይህ በራሱ ዝግጅቱን ለየት ከሚያደርጉት መካከል ይመደባል። ጎሣዬ ትልቅ ድምፃዊ ነው፤ እየመጣን ነው ለማለት ነው እንጂ ያን ያክል ስፖንሰር ፈልገን አይደለም። ይህን ስልህ በዋናነት ጎሣዬ የመድረክ ዝግጅቱን ለማቅረብ እየመጣ መሆኑን ለማሳወቅ ሲሆን እግረ መንገድ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች አብረውን እንዲሠሩ ለመጋበዝ ነው። አንድ ትልቅ ኩባንያ የዚህ ኮንሰርት ይፋዊ አጋርና ስፖንሰር ነው።

በአጠቃላይ ለዝግጅቱ ምን ያህል ወጪ አወጣችሁ?
ለኮንሰርቱ ዝግጅት በአጠቃላይ ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚደርስ በጀት ተይዞለታል። ለጎሣዬ ብቻ 2 ሚሊዮን ብር ተከፍሎታል።

በዝግጅቱ ላይ ምን ያክል ታዳሚ ይገኛል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?
እስከ 10 ሺሕ የሙዚቃ አፍቃሪ ይመጣል ብለን እንጠብቃለን።

የሙዚቃ ዝግጅቱ በቪዲዮ ተቀርፆ ለሙዚቃ አፍቃሪ ማቅረብን በተመለከተ የታሰበ ነገር አለ?
ይህንን ጉዳይ ከጎሣዬ ጋር እየተወያየንበት ያለ ጉዳይ ነው። በኮንሰርቱ ላይ ለመገኘት ያልቻሉ ብዙ አድናቂዎችና ሙዚቃ ወዳጆች ስለሚኖሩ የመድረክ ሥራዎቹ በከፍተኛ ጥራት ተቀርፀው በቪሲዲና ማኅበራዊ ገፆች እንዲሰራጩ ለማድረግ ስምምነት ላይ እንደምንደርስ ተስፋ እናደርጋለን።

ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞችስ ተመሣሣይ ዝግጅት ታዘጋጃላችሁ?
የአዲስ አበባውን ኮንሰርት ጨምሮ 10 ከተሞችን ያካተተ ኮንሰርቶች ለማዘጋጀት ወደ 10 ሚሊዮን ብር ገደማ ለመክፈል ተስማምተናል። በአንድ ዓመት ወይም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲያልቅ ኮንሰርቶቹ አንዲካሔዱም ተስማምተናል። ይሁንና ይህ ሁሉ የሚሆነው አገራችን ሰላም ስትሆን ብቻ ነው።

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚዘጋጀውን የዘንድሮውን የፋሲካ የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት ጨረታ አሸንፋችሁ ዝግጅቱን አካሒዳችኋል። ይሁንና ከዓመት ዓመት የጨረታው ገንዘብ የተጋነነ መሆን አላስፈላጊ ፉክክርና ዓላማውን እንዳያስተው ብዙዎች ሥጋታቸውን ይገልፃሉ። እዚህ ላይ ምን ትላለህ?
እውነት ነው! በየጊዜው ለሚታየው የዋጋ መናር ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ የገናውን ባዛር ያሸነፍነው በ21 ሚለዮን ብር ሲሆን ይሔኛውን [የፋሲካውን] ደግሞ በ26 ሚሊዮን ብር አሸንፈናል። በአጠቃላይ ኹለቱን ዝግጅተቶች በ47 ሚሊዮን ብር አሸንፈናል ማለት ነው።

ኤግዚቢሽን ማዕከል በጣም ትልቅ ሥም ያለው ተቋም ነው። ብዙ ጎብኚዎችም ይመጣሉ። በእኛ በኩል ብዙ የፈጠራ ሐሳበች ተጨምረውበት በተቻለ አቅም በጀቱን ማምጣት የሚችልና በተመሣሣይ ዋና ሥጋቱ ተጠቃሚው ላይ ጫና እንዳይፈጥር በጣም ብዙ ሥራ እንሠራለን።

የዋጋው መናር እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ንረቱ ወደ ተጠቃሚዎች እንዳይወርድ ብዙ ሥራዎች እንሠራለን። ለምሣሌ መዝናኛው ላይ ትኩረት ሰጥተን እሠራለን። የንግድ ትርዒት ዋና ዓላማው የንግድ ልውውጥ ነው። አሁን ላይ ግን ከንግድ ትርዒቱ አልፎ ትልቅ ፌስቲቫል ሆኗል። ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን (features) በመጨመርና በስፖንሰር ኩባንያዎች ወጪዎች እንዲሸፈኑ የምናደርግበት አሠራሮች አሉ።

የንግድ ትርዒትና ባዛሩ ከሚዘጋጅበት ዓላማ አንጻር ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል?
አዎ! በጣም ስኬታማ ነው። እንዳልኩህ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን እንፈጥራለን። ለምሳሌ ቀን ተቀን የምንጠቀምባቸውን ምርቶች በሚይዙ ነጋዴዎች ላይ ጫና አናደርግም። እነሱ ላይ የዋጋ ጫና ከፈጠርን ወደ ኅብረተሰቡ በቀጥታ ስለሚሔድ አናደርገውም።

በብዛት ባንኮች፣ የቢራ ፍብሪካዎችና አምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና አገልግሎታቸውን ለመስተዋወቅ ጥሩ ዕድል ስለሚፈጥርላቸው በእነሱ ላይ ጫና እናደርጋለን፤ ከፍተኛ ክፍያም እንጠይቃቸዋለን።

ዋጋው ተጠቃሚዎችን እንዳይጎዳው የመግቢያውን ክፍያ በባንክ እንዲከፍሉ አማራጭ በማቅረብ ቅናሽ እንዲያገኙ አድርገናል። ኩባንያዎች ምርታቸውን በብዛት ስለሚሸጡ፤ ከሌላው ገበያ አንጻር የዋጋ ቅናሽ ያደርጋሉ። ይህ ጎብኚዎችን የምንጠቅምበት አንዱ መንገድ ነው።

ትልቁ የንግድ ትርዒትና ባዛር ዓላማ በአንድ መድረክ ላይ ብዙ ሥራዎች መሥራት በመሆኑ ዞሮ ዞሮ ጨረታው በዚህ ዓይነት የሚቀጥል ከሆነ ወደፊት በጣም አስጊ ነው የሚሆነው።

በዚህ ዓመት ባዘጋጃችሁት የንግድ ትርዒትና ባዛር መቀዛቀዝ አልገጠማችሁም?
በተቃራኒው በጣም ጥሩ ምላሽ እያገኘን ነው። በአጠቃላይ ግን እንደአገር ኢኮኖሚው በጣም ተቀዛቅዟል፤ የዶላርም እጥረት አለ። ከዚህ አንጻር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች ውስን ናቸው። በአገር ውስጥ የሚመረቱ እቃዎችም ለፋብሪካ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት ስላጋጠመ አምራቾችም ተቸግረዋል። ከዚህ ከዚህ አንጻር ሲታይ አቅርቦቱ ትንሽ ቀንሷል። ይሁንና የጎብኚዎች ቁጥር ግን አልቀነሰም። 21 ቀናት የመቆየቱንም ያክል፥ ጥሩ ሥራ ይሠራል። ይህ ማለት ግን ምንም ተጽዕኖ የለም ማለት አይደለም።

በዘንድሮው ንግድ ትርዒትና ባዛር ምን አዲስ ነገር አስተዋወቃችሁ?
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ጎብኚዎች ላይ ጫና ላለመፍጠር የገቢ ምንጫችንን የምንጨምርበት አማራጭ አዘጋጅተናል። በፋሲካ የንግድ ትርዒትና ባዛር ላይ የዳይኖሰር ትርዒት አካትተናል። ይህም በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ትርዒት ነው።
ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ውስጥ ብዙን ጊዜ አዲስ የቴከኖሎጂ ውጤት ሲመጣ እንደቅንጦት የማየት አዝማሚያ አለ። ይሁንና ሕፃናቱ፣ ወጣቱና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍል እንዲዝናኑበት ብለን ያመጣነው ሲሆን ብዙ ሰዎች ፍላጎት ያሳዩበትና ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘበት ሁኔታ ነው ያለው፤ በከፍተኛም ደረጃ ተጎብኝቷል።

የአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተወሰነ ድርሻ መግዛታችሁን አዲስ ማለዳ በቅርቡ ዘግባለች። እስቲ ስለግዢው ስምምነት ተጨማሪ መረጃ ስጠኝ።

ሀበሻ ዊክሊ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሚዲያ ላይ እየሠራ ይገኛል፤ ከፍተኛም ፍላጎትም አለን። የራሳችንን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት ረጅም ዓመት የሠራንበት ዕቅድ ነው። ወደፊት በሠፊው በመዝናኛው ዘርፍ እንመጣለን።

ነገር ግን አፍሮ ሔልዝ (አፍሪ) ቲቪን ስንቀላቀል የተመሰረተበትን ዓላማ ስለወደድነው ነው። የእኛ ቴሌቪዥን ጣቢያውን መቀላቀል ተጽዕኖ በማሳደር ሙሉ ለሙሉ ዓላማውን ለማስለወጥ አይደለም። የተነሳበትን ዓላማ ጤና ላይ መሆኑ በጣም ጥሩና ማኅበራዊ ኀላፊነት የምትወጣበት ጭምር ነው። ጤና ደግሞ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ወሳኝና ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍ ነው፤ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍልን የሚጠቀሙበት ሥራዎች መሥራት ያስችላል።

ስምምነታችንን በተመለከተ በዓይነትም በገንዘብም አስተዋጽዖ ማድረግ ነው። በተጨማሪም ሌሎች ውስጣዊ ስምምነቶች ተካትተዋል። ቲቪውን ሀበሻ ዊክሊ በመቀላቀሉ በመዝናኛው ዘርፍ ላይ ብዙ ስለሠራንና ዕውቅናም ስላለን፥ በቴሌቪዥን ፕሮግራማችን ላይም ብዙ ተከታታዮች ወይም ተመልካቾች አሉን። ስለዚህ ሀበሻ ዊክሊን ይዘን ገብተን እሁድ ሠፊ የመዝናኛ ዝግጅቶች እንሠራለን።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ትኩረት ግማሹ በጤና ላይ እንዲሁም ግማሹ ደግሞ በመዝናኛ ላይ እንዲሠራ ለመድረግ ነው። በመጪው ኹለት ወራት ውስጥ በአዲስ መልክ፣ በአዲስ ስቱዲዮ፣ በአዲስ አቀራረብ ዝግጅቶች ይቀርባሉ። በመሆኑም ጥሩ ተፎካካሪ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሚሆን ተስፋ እናደረጋልን።

የዝግጅት ይዘትን በተመለከተ ከቀድሞ የቴሌቪዥኑ ባለቤቶች ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ገብታችኋል ስለሚባለው ጉዳይስ ምን ምላሽ አለህ?
በርግጥ ሁል ጊዜ አዲስ ሐሳብ ሲመጣ ፍጭት ይኖራል እንጂ በመሰረታዊነት ቴሌቪዥን ጣቢያው የተነሳበት ዓላማ እንድንጠብቅ መሥራቾቹ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ጣቢያው መዝናኛ ከሌለው ጤና ላይ ብቻ ቢያተኩር ተመልካች ማግኘት ከባድ ነው የሚሆንበት። ከዚህ አንጻር አንዳንድ የሐሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። ይሔን ያክል ግን አሳሳቢ አይደሉም። ዞሮ ዞሮ ዋናው ዓላማ ቴሌቪዥን ጣቢያውን ታዋቂ ማደረግ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ ዝግጅቶች አሰናድቶ በማቅረብ ብዙ ተመልካች ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ከተሞች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳለችሁም ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ትላለህ?
ከተቋቋመ ሦስት ዓመት የሆነው ʻሀበሻ ዊክሊ ናይጄሪያ ሊሚትድʼ የሚባል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሌጎስ አለን። ይህንንም ያደረግነው በሚዲያና ሌሎች ዘርፎች አፍሪካ ውስጥ መሥራት ስለምንፈልግ ነው። ናይጄሪያን የመረጥንበት ዋናው ምክንያት የመገናኛ ብዙኀንና የመዝናኛ መናኸሪያ (hub) በመሆኗ ነው። ናይጄሪያ ውስጥ ብዙ አጋር ድርጅቶች አሉን። ከፊልም ጋር በተያያዘ በትብበር ሊሠሩ የሚችሉ ብዙ ሥራዎች (projects) አሉን፤ ተጀምረው ያላለቁ ጉዳዮች አሉን። ሌሎች በቋሚነት ለመሥራት ያሰብናቸውም ሥራዎች አሉ።

ዱባይ ላይ ከእህት ኩባንያዎቻችን ጋር በመጣመር የመሰረትነው ኩባንያ አለን። በአብዛኛው በኤግዚቢሽን ዝግጅቶች ላይና በንግድ (trading) ላይ የተሠማራ ኩባንያ ነው።

በቅርቡ ደግሞ ጣሊያን አገር የወጪ ንግድ ሥራ ላይ የሚሠማራ አዲስ ድርጅት አቋቁመናል። በቅርቡ ይፋ እናደርገዋለን። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ኩባንያ ነው።

ወጣት ባለሀብት እንደመሆንህ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለእንዳንተ ያሉ ወጣት ባለሀብቶች ያላቸው መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው?
መልካም አጋጣሚዎችን በተመለከተ ወጣት በመሆናችን በትጋትና በወኔ መሥራታችን እንዲሁም በአዳዲስ ፈጠራዎች በመታገዝ ያልተነኩና እምቅ አቅም ያላቸው ሥራዎች መሥራት መቻላችን ተጠቃሽ ናቸው። ተግዳሮትን በሚመለከት ዋነኛዎቹ የመንግሥት የተንዛዛ አሰራር (bureaucracy) እና የገንዘብ ድጋፍ አለማግኘት ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here