የሕክምና ባለሙያዎቹ አብዮት

0
620

ክቡር የሆነው ሰው ልጅ ሕይወት በምድር ላይ በበርካታ እክሎች ሳቢያ መጓዝ ካለበት ርቀት ወይም መቆየት ካለበት ጊዜ አስቀድሞ ሊገታ ይችላል። ታዲያ ከእነዚህ እክሎች መካከል በሽታ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል – በተለይ ደግሞ በአዳጊ አገራት ላይ። በጤና ላይ በሚያጋጥም ሳንካ እንደየማኅበረሰቡ የንቃተ ሕሊና የመፍትሔ አመራረጡም ይለያያል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ግን ሁሉንም የሚያግባባው ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ የምናገኘው መፍትሔ ነው።

በኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ መፍትሔ እምብዛም አይስተዋልም። እንዲያውም በማኅበረሰቡ ውስጥ በጤና ተቋማት ላይ ያለው እምነትና ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጠው ከበሬታ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ለዚህ እንደማሳያ ደግሞ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ሕፃን በአጋጣሚ ሲያድግ ምን መሆን እንደሚፈልግ ቢጠየቅ ብዙወቹ የመጀመሪያ ምርጫው “ዶክተር” መሆን እንደሆነ አያጠራጥርም። ሕፃናት የመጀመሪያ ምርጫቸው እስኪሆን ድረስ ዶክተርነትን የመረጡበት ምክንያት በለጋ ዕድሜያቸው በቤተሰብ ከሚሰበክላቸው የዶክተርነት የተከበረ ሙያነት ባለፈ የተረዱት አይኖርም።

አሁን ግን ይህ የተከበረ ሙያ ነባር ክብሩን እያጣ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት እየሳሳ ይመስላል። ለዚህም እንደማሳያ የሚነሳው ከሰሞኑ በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች የሕክምና ባለሙያዎች ተበድለናል፣ ከዚህ በላይ መታገስ አንችልም ብለው ብሶታቸውን ሕዝብ እንዲሰማላቸው አደባባይ የወጡበት ሁኔታ ነው። የአደባባይ ሰልፎቹ መነሻ በጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥ አንዲት የሕክምና ባለሙያ በምታክመው ግለሰብ ዘመዶች ጥቃት ማድረሳቸው ከተሰማ በኋላ መሆኑን በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተቃውሞ ሰልፎቹን የሚያስተባብሩት ዶክተር ሔለን ቴዎድሮስ የገለጹልን ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ነገሮች ተቀጣጥለው እና ብሶቶች ገንፍለው ባለሙያዎቹ ሰልፍ ወጥተው አደባባይ ውለዋል።

የጅማው ጥቃት
መጋቢት 3/2011 እንደወትሮው ለ36 ሰዓታት በሥራ ላይ የነበረችው የጤና ባለሙያ፣ ሙያዊ ክትትል በምታደርግለትና ተኝቶ በሚታከመውን ግለሰብ ለመጎብኘት በመጡ ዘመዶች የአካላዊ ጥቃት ይደርስባታል። በጉዳዩ የተደናገጠችው ወጣት የሕክምና ባለሙያ ለቅርብ አለቆቿ ስለ ጉዳዩ ታሳውቃለች። ይሁን እንጂ ያገኘችው መልስ ከጠበቀችው በተቃራኒ የሆነ እና ተጨማሪ ቁጣን ከአለቆቿ አስከትሎባታል።

ይህንንም ተከትሎ በጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ሠራተኞችና የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ የተቃውሞ ሰልፍ አካሔዱ። ጉዳዩንም በተመለከተ የተበዳይ የሥራ ባለደረቦች በማኅበራዊ ድረ ገፆች ወሬው እንዲዳረስ በማድረግ በኹሉም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ። የወጣቷ የጤና ባለሙያ ጉዳይ መነሻ ሆነ እንጂ በተቃውሟቸው ወቅት ተጨማሪ ጥያቄዎችንም አንስተዋል፤ በተግባር ልምምድ ወቅት ጥርት ያለ የሥራ ድርሻቸውን እንዲያውቁ ጠይቀዋል፣ የሕክምና መሣሪያዎችም በተገቢው መንገድ እንዲከፋፈሉ ሌላው ጥያቄያቸው ነበር።

የአርሲው ተቃውሞ
የጅማው ጉዳይ በማኅበራዊ ድረ ገፆች መዳረሱን ተከትሎ ተቃውሞውን በፍጥነት በመቀላቀል የቀደመው አርሲ ዩንቨርስቲ አሰላ ካምፓስ ነው። በመጋቢት 9/2011 ከጥዋቱ 2፡30 ጀምሮ ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩት በተግባር ልምምድ ላይ የሚገኙት የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች በቁጥር የበዙ መፈክሮችን በጽሑፍና በቃል ሲያስተጋቡ ነበር።

“የተግባር ልምምድ የሚያደርጉ ተማሪዎች ማሽኖች አይደሉም” የሚለው መፈክር ጎልቶ የተስተዋለ ሲሆን ለዚህ ደግሞ በተከታታይ ያለምንም እረፍት ለ36 ሰዓታት በሥራ ላይ እንዲቆዩ መገደዳቸውን የሚያመለክት ነው። በሥራ ቦታዎች የሚደርስባቸውን ጥቃት አስመልክተውም “ተገቢው ከለላ ይደረግልን” የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል። የተግባር ልምምድ ላይ ያሉ እና የመጨረሻ ዓመት የአርሲ ዩንቨርስቲ ጊቢ ተማሪዎች ካስተጋቧቸው ተቃውሞዎች በተጨማሪ እንዲሟሉላቸው የሚፈልጓቸውን ትምህርት ግብዓት በሰነድ አዘጋጅተውም ነበር። በዚህም ረገድ የቤተ መጽሐፍት ወንበሮች ለማጥናት ምቾት የሌላቸው በመሆኑ ረጅም ሰዓታት ተቀምጠው ለማጥናት በመቸገራቸው፣ ጣራውም ዝናብ በመጣ ጊዜ ስለሚያፈስ በመጽሐፍት ላይ ጉዳት እንደሚደርስ በተመለከተ የሚነሱት ነጥቦች ናቸው።

ይሁን እንጂ የተማሪዎች ተቃውሞ እንደታሰበው ሰላማዊ ሆኖ መቀጠል አልቻለም። የክልሉ ፖሊስ ኃይል ሰላማዊ ነበረውን ተቃውሞ በኃይል ለመበተን በወሰደው እርምጃ ተቃውሞው መልኩን ቀየረ። በርካቶች ተደበደቡ፣ ሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው። የዓይን እማኞች እንደሚሉት አንዲት ሴት የሕክምና ተማሪ ፖሊስ ሰላማዊውን ሰልፍ በኀይል በበተነበት ወቅት ቁጥራቸው ስድስት በሚደርሱ ፖሊሶች ስትደበደብ ተመልክተዋል።

አዲስ አበባ
በሌሎች ከተሞች የተከናወነው የሕክምና ባለሙያዎች ተቃውሞ ድምፅ አዲስ አበባንም ሳይነካ አላለፈም። ተመሳሳይ ምክንያቶችን የያዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ (ጥቁር አንበሳ) ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን በተመሳሳይም የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችም የጥቁር አንበሳ ተማሪዎችን ፈለግ ተከትለው፣ አለብን ያሉትን ችግር በኮሌጁ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።
በኹለቱም ኮሌጆች የሥራ ላይ ደኅንነት ይከበርልን፣ በተገቢው መንገድ እንስተናገድ እና ረጅም የሥራ ሰዓት ይቅር የሚሉ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው።

ለማሳያ እነዚህን ከተሞች አነሳን እንጂ በመላው አገሪቱ የተሰራጨው የጤና ባለሙያዎች ተቃውሞ ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልም ተዛምቶ በጎንደርና መቀሌ ከተሞችም ሰልፎች እንደተካሔዱ ታውቋል። በኹሉም ከተሞች የተማሪዎች ጥያቄ አንድ ዓይነት ይዘት እንዳለው በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተቃውሞ ሰልፉን የሚያስተባብሩት ዶክተር ሔለን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ዶክተር ሔለን እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር ከባርነት ምንም ልዩነት የሌለው ነው ሲሉ ጀምረው፣ በጣም ከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛም በሐኪሞች ላይ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

ሐኪሞችና የተግባር ተለማማጆች ለ36 ሰዓታት በሥራ ላይ እንዲቆዩ የሚደረግበት አግባብ እንዳለ ጠቁመው፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለተሠሩት ሥራዎች ተመጣጣኝ ክፍያ ማግኘት የማይታሰብ ነው ብለዋል። ሐኪሞች 36 ሰዓታት በሚሠሩበት ጊዜ የማረፊያ ክፍል (Duty Room) ያለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን የከፋ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሐኪሞች የትምህርት ጊዜያቸውን ጨርሰው እንደተመረቁ ወደ ሥራ ባለመመደባቸው ሥራ ማግኘት ደኅንነት ስጋት ውስጥ መግባታቸውንም የተቃውሞው አንዱ ምክንያት ነው። ለዚህ ደግሞ በተደጋጋሚ የሚመለከተው አካል በጀት የለም በሚል ያለሥራ እንዲቀመጡ እንደሚያደርጋቸው ታውቋል።

እንደ ዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት በፈረንጆች 2017 በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ዶክተር ለ17 ሽሕ ታካሚዎች የሚደርስ ሲሆን ይህም እ.ኤ.አ. 2014 ከነበረው 1ለ 20 ሺሕ ስሌት መሻሻል ቢያሳይም ከተቀመጠለት መለኪያ በታች እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ጥናቱ ይህን ይበል እንጂ አሁንም ከ5 መቶ በላይ በተለያዩ የሕክምና ዘርፍ የተመረቁ የህክምና ባለሙያወች አሁንም ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም።

ይህን እና መሰል ጉዳዮችን አንግበው ወደ አደባባይ የወጡት በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የሕክምና ተማሪዎች ጉዳያቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮን በማንኳኳቱ ዛሬ ቅዳሜ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ይወያያሉ።

አስተባባሪዋ ዶክተር ሔለን ከውይይቱ ተስፋ ብቻ ሳይሆን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው እንደሚጠብቁ ገልፀው “ለውጡ አሁን ይሁን” የሚል ድርድር ሊባል የሚችል ውይይት እንደሚጠብቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here