አስገዳጅ የጠበቆች ማኅበር የሚያቋቁም አዋጅ ተረቀቀ

0
687

መንግሥት በሚያካሔዳቸው የሕግ ማሻሻያዎች ላይ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው የሕግ አማካሪው ጉባኤ ረቡዕ፣ ሚያዚያ 23 ቁጥራቸው 1 ሺሕ የሚጠጉ ጠበቆች በተገኙበት የጠበቆች ምዝገባ አዋጁን ለማሻሻል እንዲሁም በጠቅላላው በሞያው ላይ ስለሚነሱ ችግሮች ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ላይ መንግሥስት አስገዳጅ የጠበቆች ማኅበርን የሚያቋቋምውን የፖሊሲ ሐሳብ እንደሚደግፈው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ገልፀዋል። ምንም እንኳን የተረቀቀው አዋጅ ለውይይት ባይቀርብም ለአዋጁ መሰረት የሆነውን ጥናት እና ዋና ዋና የፖሊሲ ሐሳቦችን አማካሪ ጉባኤው ጠቅላይ ዐአቃቤ ሕጉ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቷ በተገኙበት አቅርበዋል።
በኹለት ዓይነት መንገድ ሊተገበር ይችላል ተብሎ የቀረበው የማኅበሩ አወቃቀር አንድ በፌደራል መንግሥት የሚቋቋም ማኅበር ኖሮ ወደ ክልሎች የሚወርድ ወይም ክልሎች በየራሳቸው ማኅበራቱን ካዋቀሩ በኋላ አንድ አገራዊ ኮንፌዴሬሽን ያቋቁሙ በሚል ኹለት ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። ለዚህም የካናዳ እና የጀርመን የጠበቆች ማኅበራት እንደ ምሳሌ እንደተወሰዱም ተገልጿል።

ማንኛውም ጠበቃ የሙያ ማኅበሩ አባል የመሆን ግዴታ የሚኖርበት ሲሆን መንግሥት በብቸኝነት እስከዛሬ ሲሰጥ የነበረውን የጥብቅና ፈቃድ መስጠት፣ የጠበቆችን ሥነ ምግባር መከታተል፣ ትምህርት እና ሥልጠና የመስጠት እንዲሁም የሕግ ትምርት ቤቶችን ብቃት የመከታተል ድርሻ በሚኖረው ማኅበር ውስጥ መንግሥትም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ይህም በጋራ የሚተዳደር የሙያ ስርዓት እንጂ ጠበቆች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ስርዓት እንዳልሆነ እና የጠበቆችን ብቸኛ የበላይነት (Monopoly) በመቀነስ ጠንካራ ማኅበር እንዲኖር ለማድረግ መሆኑም ተገልጿል።

የመንግሥት የፍትሕ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ፍርድ ቤት እና ዐቃቤ ሕግ በተጨማሪ የንግዱ ማኅበራት ውክልና እንዲኖራቸው ሊደረጉ እንደሚችሉም አማካሪ ጉባኤው ገልጿል።

በተለያዩ አገራት የሕግ ሞያን አገራዊ አስገዳጅ ማኅበር፣ በየክልሉ የሚገኙ አስገዳጅ ማኅበራት፣ ፍርድ ቤት፣ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ኤጅንሲ ወይም የመንግሥት ተቋማት የሚመሩት ሲሆን አሁን በቀረበው የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ማኅበራትን በማቋቋም በመንግሥት እጅ ያለውን የመቆጣጠር ሥልጣን በከፊል ወይም በሙሉ ለባለሞያዎች ይሰጣል።

በዓለም ላይ ባሉ 219 የሕግ ወሰኖች (Jurisdictions) ላይ በተሰራ ጥናት 94 በመቶ የሚሆኑት ቁጥጥሩ ከመንግሥት ውጪ እንዳለ የጠቀሰው የሥራ ቡድኑ ጥናት የሙያ ማኅበራቱ በባለሞያ የማስተዳደር ልምዱ ከ1980ዎቹ (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ በዓለም ላይ የተለመዱ እየሆኑ መምጣታቸውንም አውስቷል። በጎረቤት አገሮችም ጭምር እነዚህ የሕግ ማኅበራት ለሕግ ሞያ፣ ትምህርት እንዲሁም ምርምር መጎልበት ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን ከፍተኛ የአባለት ቁጥር እንዲሁም ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ያዳበሩ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜ የተደራጁ የሞያው ማኅበራት ቢኖሩም የአባሎቻቸውን መብት በመጠበቅ እንጂ የሞያውን ሥነ ምግባር በማስጠበቅ ላይ ያተኮሩ አይደሉም።

የጠበቆች ምድብ (Status) እንደ ባለሞያ ወይስ እንደ ነጋዴ የሚለው በዕለቱ ሰፊ ውይይት ከተደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኖ ከግብር ስርዓቱ ወጥ ያለመሆን እንዲሁም የተንዛዛው የገቢዎች ሚኒስቴር አሰራር ከተነሱት ነጥቦች መካከል ሲሆን አማካሪ ጉባኤውም እንደ ባለሞያ ተቆጥረው ነገር ግን ወጥ በሆነ መልኩ የሚፈለግባቸውን ግብር እንዲከፍሉ መደረግ አለበት ብሎ እንደሚያምን ገልጧል።

የዩኒቨርሲቲ መምህራን የጥብቅና ሥራ መሥራት መቻል ያለመቻል ጉዳይ በአዋጁ ውስጥ በግልጽ እንዲካተት የጠየቁት ጠበቆቹ ከፍተኛ የጥብቅና ሞያ የዕድሜ ጣሪያም ይቀመጥ ብለዋል። የአማካሪ ጉባኤውም ከሙያው ፀባይ አንፃር ሲታይ ጠበቆች ዕድሜአቸው እየገፋ ሲሔድ የበለጠ ልምድ እያዳበሩ እንደሚሔዱ ተናግረው በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች እስካሟሉ ድረስ የዕድሜ ገደብ መቀመጥ አለበት ብለው እንደማያምኑም አስረድተዋል።

የውጪ አገር ዜጎች በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት ውስጥ መግባት እንዳይችሉ ነገር ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን እንዲያሳትፍ ይደረጋል የተባለው አዋጅ አብዛኛውን ታዳሚ ሲያስማማ ጥቂቲች ግን ሉዓላዊነት እና የዓለም ዐቀፉ የንግድ ማኅበር አባል የመሆን (WTO accession) ጉዳይን ጠቅሰው ሐሳቡን ተቃውመዋል።

በአጠቃለይ ጠበቆችን እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላለትን ያስማማው የሕግ ኩባኒያዎችን መቋቋም የሚፈቅደው ድንጋጌ መካተት ሲሆን ይህም ምንም ዓይነት የፖሊሲ ውሳኔ ወይም ዝርዝር ሕግ ሳይፈለግ አዋጁ በቀጥታ ይህንን እንዲፈቅድ እንደሚደረግም ተገልጧል።

የትረስት አካውንት መቋቋም ሌላው አዋጁ ይዞት የሚመጣው አዲስ ጉዳይ ሲሆን ጠበቆች በልምድ ቅድሚያ ክፍያ እየተቀበሉ የሚሰሩበትን አካሔድ ያስቀራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልቷል። ትረስት አካውንት ደንበኞች ከጠበቆቻቸው ጋር የተስማሙበትን ክፍያ የሚያስቀምጡበት የባንክ አካውንት ሲሆን ክፍያውም በተሠራው ሥራ ልክ ለጠበቃው በተለያየ ጊዜ የሚለቀቅ ይሆናል። አንዳንድ ጠበቆች ይህ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን የቅልጥፍና ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲሉም ገልፀዋል። በተጨማሪም የጉዳት ካሳ ኢንሹራንስን (Indemnity Insurance) ያስተዋውቃል የተባለው አዋጅ ጠበቆች ያለባቸው ኀላፊነት የተወሰነ ሆኖ ከዛ በላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ግን እንደ ማካካሻ መቀመጡን አማካሪ ቡድኑ ገልፃል።

ዝቅተኛ የሙያውን መስፈርት በፌደራል ደረጃ ያቋቋማል የተባለው ይህ አዋጅ የቀረበው የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ከጸደቀ ለክሎችም አንድ ወጥ መገልገያ የሚሆን መሥፈርት ይሆናል። በተጨማሪም ማንኛውም ጠበቃ ከክልል ወደ ክልል ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም በተለይ ፌደራል ላይ ተከማችቶ ያለውን ከፍተኛ የጠበቆች ቁጥር እንዲሁም ብቃት የለውን ጠበቃ ለሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የማዳረስ ሚና እንደሚኖረው ተገልጸዋል።

እስከ አሁን በነበረው አሰራር የፌደራል ጠበቆች ለፌደራል ጉዳዮች ብቻ የሚቆሙ ሲሆን በአንድ ክልል ፈቃድ ያስገኛ ጠበቃም በሌላ ክልል ሔዶ ለመሥራት ባለመቻሉ ብዙ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

የህግ ኩባኒያዎችም ሲቋቋሙ አንዳንድ ኖተሪ ስዎችን እነዲከናውን እነዲሁም የህግ ባለሞያ ያልሆኑ ሰራተኞችን ጭምር መቅጠር እንዲችሉ ሊፈቅድ ይችላል የተባለው ይሄ አዋጅ ከረቀቀም በኋላ ተመሳሳይ የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here